Friday, July 29, 2016

በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠይቅ ህዝባዊ ትዕይንት በጎንደር እንደሚካሄድ አስተባባሪዎቹ ገለጹ ኢሳት (ሃምሌ 21 ፥ 2008)


የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ያነሱ የኮሜቴ አባላት እንዲፈቱና የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠይቅ ህዝባዊ ትዕይት የፊታችን እሁን በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድ አስተባባሪዎቹ ለኢሳት ገለጹ። ለሚመለከተው አካል ከ72 ሰዓታት በፊት ማሳወቃቸውንም ገልጸዋል።
ሰልፉ በማናቸውም ሁኔታ እንዳማይቀር አረጋግጠው፣ “አትወጡም ብለው ቢተኩሱብን፣ እኛም በተኩስ ምላሽ እንሰጣለን በማለት ከሰልፉ ምድራዊ ሃይል እንደማይገታቸው አሳውቀዋል።
Gondar
ሃምሌ 5 ቀን 2008 የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ባነሱ የኮሚቴ አባላት ላይ የተከተለው እስራት ጎንደር ውስጥ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ቁጣ መንግስት እንዳመነው ከ10 በላይ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ አባላት ሲገደሉ፣ የቆሰሉት ደግሞ ከ15 በላይ ናቸው። አሁንም ዘግይተው እየወጡ ያሉ መረጃዎች ከመከላከያ ሰራዊት የተገደሉት ብቻ 19 እንደሆኑ ያስረዳሉ።
ከሃምሌ 5 ቀን 2008 ጀምሮ በጎንደር ውስጥ የሰፈነውን ውጥረት ለማርገብና ችግሩ ወደ ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች እንዳይዛመት አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ የብአዴን አመራር የነበሩት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
አቶ በረከት ስምዖን የወልቃይት ህዝብ ጥያቄን መፍትሄ ለመስጠት የሶስት ወራት ጊዜ ስጡን በማለት በስብሰባ ላይ የጠየቁ ሲሆን፣ ከተሰብሳቢዎች የታሰሩትን ፍቱ በሚል ለተነሳው ጥያቄም ጥቂት ጊዜያት ስጡን በማለት ተማፅነዋል።
ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ “አንተ ስልጣን የለህም ፥ ምንም ልታደርግ አትችልም፣ እነ ስብሃት ነጋና አቦይ ጸሃዬ አረጋጋ ስላሉ ነው የመጣኸው” በማለት ቃላቸውን ለማመን እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።
እሁድ የሚካሄደው ሰልፍ ባይካሄድ እንደሚመርጡ የተናገሩት በረከት ስምዖን፣ ከተካሄደ ሰላማዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።
የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ያነሱ የኮሚቴ አባላት በታሰሩና ጎንደር ውስጥ ግጭት በተፈጠረ ማግስት የትግራይ ክልል ወልቃይት የትግሬ ነው የሚል ሰልፍ መጥራቱ ጎንደር ውስጥ ይበልጥ ቁጣ መቀስቀሱ የታወቀ ሲሆን፣ የዕሁድ ሰልፍ ለዚህ ምላሽ ጭምር እንደሆነም ተመልክቷል

No comments:

Post a Comment