ፓርላማው ከእረፍት የተጠራው ከ3 አዋጆች በተጨማሪ የተወሰኑ ሚኒስተሮችን ሹምሽር ለማጽደቅም ጭምር ነው ተባለ
ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስታወቀው ከ እረፍት በአስቸኳይ የተጠራው ፓርላማ የተወሰኑ ሚኒስተሮችን ሹምሽር ለማጽደቅም ጭምር መሆኑን ዘገበ::
እንደ ሪፖርተር ዘገባ የፊታችን ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2008 እንዲሰበሰቡ ጥሪ የቀረበላቸው የፓርላማ አባላት የገቢ ግብር አዋጅ፣ የግብር አስተዳደር ሕግና የጂኦተርማል ሀብት ልማት አዋጆችን ለማጽደቅ ሲሆን በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሳለኝም የሚኒስተሮችን ሹም ሽር በዚሁ ዕለት ያጸድቃሉ ብሏል::
ከላይ የተጠቀሱት 3 “አዋጆች ለምክር ቤቱ የቀረቡት ፓርላማው ለዕረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ቢሆንም፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ማፅደቅ ባለመቻሉ ለዕረፍት ተበትኗል፡፡ የገቢ ግብር አዋጁ ግብር የማያርፍበት የደመወዝ መጠን አሁን ካለበት 150 ብር ወደ 600 ብር ከፍ እንዲል የሚፈቅድ፣ እንዲሁም 35 በመቶ ግብር የሚያርፍበት አምስት ሺሕና ከዚያ በላይ የሆነ የደመወዝ ገቢ ወደ 10,900 ብር ከፍ እንዲል የሚያደርግ ነው፡፡” ያለው ሪፖርተር “ይህ ማሻሻያ በተቀጣሪዎች ወርኃዊ ገቢ ላይ መጠነኛ ጭማሪ የሚያሳይ በመሆኑና ይህም ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ መፈጸም ያለበት በመሆኑ፣ አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቱን ምንጮቹ ይገልጻሉ፡፡የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ በቅርቡ እንደገለጹት፣ መንግሥት በገቢ ግብር አዋጁ ውስጥ በተካተተው የቅጥር ገቢ ላይ ብቻ ባደረገው ማሻሻያ ሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ በዓመት ያጣል፡፡” ሲል ዘግቧል::
ሪፖርተር ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው “ከተጠቀሱት ሕጐች በተጨማሪ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በተጓደሉ ዳኞች ምትክ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ዕጩ ዳኞች እንደሚሾሙ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር በሌላ በኩል እንደሰማው ከሆነ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስቸኳይ ስብሰባው በተጠራበት ዕለት በምክር ቤቱ ተገኝተው፣ በተወሰኑ ሚኒስትሮች ላይ ያደረጉትን ሹምሽር እንዲፀድቅላቸው ያስደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ዓይነቱ አስቸኳይ ስብሰባ ፓርላማው በቅርብ ጊዜ የጠራው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት ወቅት መሆኑ ይታወሳል፡፡ ” ብሏል::
No comments:
Post a Comment