Tuesday, January 17, 2017
የአጋዚ ጦር አባላት መከላከያን በብዛት እየለቀቁ ነው ጥር ፱ ( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አገዛዙ ወደ ሶማሊያና ሱዳን በሰላም አስከባሪ ስም በሚልካቸው ወታደሮች ላይ የማእረግ ማጭበርበር እየፈጸመ ገንዘብ እንደሚያገኝ የአጋዚ የህግ ክፍል ኤክስፐርት አስታውቋል። የአጋዚ ኮማንዶ እና ልዩ ሃይሎች ጠቅላይ መምሪያ የህግ ሰነድ እና ዝግጅት ኤክስፐርት የነበረው ሃምሳ አለቃ ወደ ሶማሊያ ሰላም አስከባሪ አባል ሆኖ ሲሄድ ሻለቃ ተብሎ የተሰየመው ሃምሳ አለቃ ኃ/ሚካኤል በእውቀቱ ጋሻዬ በአጋዚ ውስጥ ያለውን የህወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ዘረኝነት፣ ሙስና፣ ብልሹ አሰራር እና ጭካኔ በመቃወም ክፍለጦሩን መክዳቱን ከኢሳት ጋር ባደረገው ቆይታ አረጋግጧል። ሃምሳ አለቃ ኃ/ሚካኤል በተለይም ሰላም ለማስከበር በሚል በተባበሩት መንግስታት እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ወይም አሚሶም በሶማሊያ ሴክተር ሶስት በባይደዋ ከመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ ወር 2008 ዓ.ም በቆየበት ወቅት የህወሃት ወታደራዊ አዛዦች በሰራዊቱ ላይ የፈፀሙት ወንጀል እጅግ ዘግናኝ እንደነበር አስታውቋል። በገለጻውም በተለይ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ባይደዋ በሚገኘው ከቡራካባ 27 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚገኘው ጁባ በተባለ ስፍራ በኮሎኔል የማነ ገ/ሚካኤል ቸልተኝነት እና ዕውቀት ማነስ 42 የአጋዚ አባላት በፈንጂ እና በሌሎች መሳሪያዎች ተገለው አስከሬናቸው በየቦታው ወድቆ ያየበት ሁኔታ በቁጭት እንደሚያስታውሰው አውስቷል። ያለምንም ወታደራዊ ጥናት እና ክትትል ባልተደረገበት ተጠያቂ የሆነው ኮሎኔል የማነ ገ/ሚካኤል በሃላፊነት ሳይጠየቅ ለተሻለ እድገት የታጨበት መንገድ በሰራዊቱ እልቂት ባሳየው ንቀት እና ትእቢት የተቆጡ ወታደሮች አግተውት በምልጃ መትረፉን ይናገራል። አያይዞም የህወሃት አባል የሆኑት የክፍሉ አዛዦች ለገንዘብ ያላቸው ፍቅር እና ስግብግብነት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ እንዴት እንዳዋረዱ እራሱን በምስክርነት ያስቀምጣል። እንደ ምሳሌም ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል በማእረግ አሰጣጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የሚያጭበረብሩበት ስልት በጣም አስደንጋጭ ነው ይላል። ከሰራዊቱ ተመርጦ በሕግ ኤክስፐርትነት እንዲሄድ ሲነገረው ሃምሳ አለቃ ነበረ። በሰላም አስከባሪ አባል ሆኖ ወደ ሶማሊያ ሲሄድ ሻለቃ በእንግሊዝኛው (Major) አደረጉት። በአጋዚ ክፍለጦር በሃምሳ አለቅነት ሲያገለግል የነበረው ኃ/ሚካኤል በአንድ ጀንበር ከስድስት በላይ እርከኖችን አልፎ ሻለቃ ሲሆን መገረምም መደናገጥም ፈጥሮበት ነበር። የእውነትም መስሎት እንደነበረ ያወሳል። ይሁንና ከተመደበበት ቦታና ስፍራ በስተቀር ደመወዝ የሚከፈለው በሃምሳ አለቃነቱ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግስታት በሻለቅነት የሚከፍለውን የህወሃት ከፍተኛ መኮንኖች የሃምሳ አለቃውን 40% ብቻ እንደሆነ መስክሯል። በተለይ በሶማሊያ የነበሩት የጦር አዛዦች ብርጋዴር ጄነራል መሀመድ አይዘኑ፣ ብርጋዴር ጄነራል ገ/መድኅን ፍቃዱ በቅጽል ስሙ ወዲ ነጮ፣ ብርጋዴር ጄነራል ዮሃንስ እና ኮሎኔል የማነ ገ/ሚካኤል ከመንግስታቱ የሚመጣውን ዶላር ከሰራዊቱ በመዝረፍ ሰንሰለት በተበጀለት መዋቅር እነዚህን ወታደራዊ አዛዦች ማበልፀጊያ መሆናቸው ያንገበግበዋል። በሶማሊያ የሰራዊቱ አባላት አስከሬን በየጉድባው ተሽንቁሯል። አስታዋሽ ማጣቱን በሃዘኔታ ያስታውሰዋል። አክሎም በሰላም አስከባሪነት የሄደው የሰራዊቱ አባላት ሲገደሉ የተባበሩት መንግስታት የሚከፍለው በአንድ ሰው ወደ አንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚጠጋ የደም ካሳ ለአንዳቸውም የሟች ቤተሰቦች ሳይደርስ በእነ ኮሎኔል የማነ ገ/ሚካኤል አስተላላፊነት የህወሃት ጄኔራሎች ቅምጥል ሕይወት ይመሩበታል። ልጆቻቸውንም በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚያስተምሩበት ዶላር ይሰበስቡበታል ሲል አማሯል። አጋዚ በአገር ቤት የስርዓቱ ቀኝ እጅ ሆኖ የስልጣኑ ዋስትና እንደሆነ ይነገራል። በሶማሌ ደግሞ እየተማገደ የማይነጥፍ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ በደሙ ይነገራል በማለት በቁጭት ይተርካል። በአገር ቤት ሃምሳ አለቃ በሶማሌ ሻለቃ ኃ/ሚካኤል ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ከስልጠናው ጀምሮ እስከ ምደባው ያለውን አስፈሪ እና አስከፊነት ሂደቶችን በተመለከተ አብራርቷል። በሁርሶ ሁለት ወር የፖለቲካ ትምህርት፣ ስድስት ወር ወታደራዊ ስልጠና ከዛም ማጣሪያ ወይም ፍሊተሬሽን፣ አስከትሎም በብላቴን 12 ወራት ወታደራዊ የኮማንዶ ስልጠና ወስዶ ይወጣል። በሁርሶ የሁለት ወሩ የፖለቲካ ስልጠና በተመለከተ በሰጠው ምስክርነት ተመልምለው ሰልጥነው የሚወጡት የስርዓቱ ዋነኛ ጠላቶች ተብሎ የሚነገራቸው ”የአማራ ትምክተኝነት፣ የኦሮሞ ጠባብነት” እንደሆነ በመግለጽ ”በቋንቋችሁ እንዳትናገሩ፣ በማንነታችሁ እንዳትከበሩ የሚያደጉት ኃይሎች ዋነኛ ጠላቶች በመሆናቸው እነዚህን አንታገስም!” በማለት ተናዘው፤ በፖለቲካ ራሳቸውን ክደው፣ ስብዓዊነታቸውን አንጠፍጥፈው ወደ አውሬነት የሚቀየሩበት የጨካኞች ማዕከል እንደሆነ ብላቴ እና ሁርሶን በዋቢነት ጠቅሷል። ይህም በመሆኑ ከትግራይ ተወላጆች ውጪ ያሉት የሌላ ብሄር አባላት ክፍለጦሩን በመክዳት የነጻነት ኃይሎችን ለመቀላቀል እንደሚፈልጉ አስታውቋል። በየዓመቱም ከስድሳ በላይ የሰለጠኑ ወታደሮች እየከዱ እና የአጋዚ ክፍለጦር እየፈራረሰ መሆኑን ጠቁሟል። በመጨረሻም ሰራዊቱ ሕዝባዊ አጋርነቱን በማሳየት ”ጥቂት የህወሃት ከፍተኛ መኮንኖች እና ባለስልጣናቱን የተንደላቀቀ ሕይወት ብላችሁ የንጽሁሃንን ወገኖቻችሁን ደም አታፍስሱ” በማለት ጥሪ አቅርቧል። ከዚሁም ጋር አያይዞ በአጋዚ ክፍለጦር ውስጥ ሰራዊቱን በመበደል ሕዝብ ላይም እንዲተኩስ ምክንያት የሆኑትን የህወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን በተለይ ብርጋዴር ጄነራል ገ/መድኅን ፍቃዱ ወዲ ነጮ፣ ብርጋዴር ጄነራል መሀመድ አይዘኑ፣ ብርጋዴር ጄነራል ዮሃንስ እና ኮሎኔል የማነ ገ/ሚካኤል ነገ ከሕዝብ ፍርድ እንዲሁም ከሰራዊቱ የበቀል ሰይፍ እንደማያመልጡ አስጠንቅቋል።ESAT Daily News Amsterdam January 17,2017
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment