በሰሜን ጎንደር ዞን በአጅሬ ጃኖራ አወቀ ካሴ የተባለ ወጣት ከአርበኛ ማሳፍንት ጋር በተያያዘ ታስሮ ስቃይ ሲደርስበት ከቆየ በሁዋላ፣ ወደ ዋና ከተማው ዳባት ሲመጡት “ ድልድልዬ” ከተባለ ቦታ ላይ፣ ኮማንደር መሰለ ጥጋቡ የሚባለውን ሚሊሺያ መሳሪያ በመቀማት እና በ3 ጥይቶች በመግደል የራሱንና የአባቱን መሳሪያ ይዞ በማምለጥ የነጻነት ሃይሎችን ተቀላቅሏል።
ወጣቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የአጋዚ ወታደሮች በዋልድባ የቅርናምባ ኪዳነምህረት ገዳም ውስጥ በመግባት አስጸያፊ ስራ መስራታቸውን ለወራት አርበኞችን በመምራት ከህወሃት/ኢህአዴግ ሰራዊት ጋር እየተዋጉ ያሉት አርበኛው አቶ መሳፍንት ተናግረዋል። የአጋዚ ወታደሮች በዳባት አውርጃ በዋልድባ ቅርናምባ ኪዳነምህረት ከደናግላት በስተቀር ሌሎች ሰዎች የማይገቡበትን ቅዱስ ገዳም በመድፈር፣ እነ አቶ መሳፍንት የማረኩዋቸው መትረጊሶችና ሽጉጦች እዚህ ተደብቀዋልና እንፈልጋለን በማለት ከገዳሙ መቅደስ ውስጥ ገብተው በፅላቱና ጥንታዊ መጽሐፍት ላይ አሳፋሪ ስራ መስራታቸውን አቶ መሳፍንት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋሞች እንዲያውቁትና ይህንን ግፍ ጸሎት እንዲያድርጉም አቶ መሳፍንት ጥሪ አቅርበዋል። ወታደሮች ተደብቀዋል የተባሉ የተማረኩትን የጦር መሳሪያዎች እንዳላገኙዋቸው አቶ መሳፍንት ገልጸዋል። አቶ መሳፍንት በጃኖራ አካባቢ ለወራት ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት የመሩ ናቸው። ገዢው ፓርቲ ሁለት ቤታቸውንና ሌሎችንም ድርጅቶቻቸውን በእሳት አቃጥሎባቸዋል። እርሳቸውን ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም አልተሳካም።
በአማራ ክልል ህዝባዊ አመጽ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የብአዴን አባላት ህይወታቸው አልፏል።
በአዊ ብሄረሰብ አሰተዳደር ዞን የዚገም ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፒከተር ሀብታሙ መኮንን ከቻግኒ ወጣ ብሎ መጠለያ በተሰኝው ጫካ ውስጥ ከሳምንት በፊት ሞተው ተገኝተዋል ፡፡ ከቀናት በፊት በዳንግላ ከተማ አገዛዙን ለመቃወም በወጡ ነዋሪዎች ላይ በመተኮሱ በህዝብ ይፈለግ የነበረው ኢንስፔክተር ያረጋል አበጀም እንዲሁ ሞቶ ተገኝቷል። ከአንድ ወር በፊት በቻግኒ ከሰፈረው መከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል ሶስት ወታደሮች በሴተኛ አዳሪዎች ቤት ተገድለው ተገኝተዋል። እስካሁን ድረስም ያለምንም ማጣራት አምስት ተጠርጣዎች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ከቀናት በፊት በቡሬ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ቦምብ ተጥሎ የሁለት ሰዎች ህይዎት አልፏል፡፡
በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 16 የብአዴን አመራር የሆነች ወጣትም በጩቤ ተወግታ በከፋ አደጋ ውስጥ መሆኗን ምጮች ተናግረዋል፡፡
በጎንደር እና በባህርዳር ሁለት ሆቴሎች ላይ ቦንቦች ፈንድተው፣ በጎንደሩ ፍንዳታ አንድ ሰው መሞቱና 19 ሰዎች መቁሰላቸው ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment