Monday, January 2, 2017

የተባበሩት መንግስታት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ለተሰማሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በየወሩ በዶላር የሚከፍለው ደመወዝ በህወሃት የጦር ጀነራሎች መመዝበሩን የሠራዊቱ አባላት አጥብቀው በመቃወም ላይ እንደሚገኙ ታወቀ

በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ስራ ላይ የህወሃት አገዛዝ አሥራ አንድ ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን በተራ ወታደርነት ወይም ሚሊታሪ ኮንትንጀንት (Military Contingent)፣ ስታፍ ኦፊሰርነት (staff officer)፣ ሚሊታሪ ኦቭዘርቨር (Military Observer) እና የፓሊስ አባልነት በማሰማራት ከማህበራቱ ድርጅት በየወሩ ከፍተኛ የሆነ ዶላር እየሰበሰበ እንደሚገኝ ከመከላኪያ ሠራዊት የውስጥ ምንጮቻችን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሎአል። የተባበሩት መንግሥታት በዚህ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ለተሰማሩት ተራ ወታደሮች በወር በነፍሰወከፍ 1400 /አንድ ሺህ አራት መቶ /የአሜራካ ዶላር እንደሚከፍል ያረጋገጡት ምንጮች በአሁኑ ሰዓት በተልዕኮው ላይ ላሉት አስራ አንድ ሺህ ወታደሮች በሳሞራ የኑስ የሚመራው መከላኪያ ሚንስቴር በአመት  184,800, 000 /አንድ መቶ ሰማኒያ አራት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ/ የአሜራካ ዶላር እንደሚቀበል ገልጸዋል። ይህ ገንዘብ ዝቅተኛ በሆነ የ22 ብር ሚንዛሪ ሂሳብ እንኳ ቢሰላ በአመት አራት ቢሊዮን ስልሳ አምስት ሚይሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ብር እንደሆነና በአበል ስም ለህወሃት መከላከያ ከሚሰጠው ከዚህ ገንዘብ በተጨማሪ ለመሳረያና ለሄሊኮፕተር ክራይ እየተባለ በየወሩ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፈል ምንጮች አክለው አረጋግጠዋል።

በየወሩ ይህን ያህል ትልቅ መጠን ያለውን ገንዘብ በውጪ ምንዛሪ በወታደሮቹ ስም የሚሰበስበው የህወሃት አገዛዝ በግዳጅ ላይ ለተሰማሩ ለነዚህ ወታደሮች የምግብ ለቤት ኪራይና ለተለያዩ ወጪዎች በወር 136 አንድ መቶ ሠላሳ ስድስት የአሜሪካን ዶላር በየተሰማሩበት ግንባር ከመክፈል ውጪ የተቀረውን ወደ አገር ቤት ስትመለሱ ይከፈላችኋል እያለ በመደለል እንደኖረ ታውቆአል። በዚህም የተነሳ በሠላም ማስከበሩ ተግባር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የአገራችን ወታደሮች በሙሉ እንደነርሱ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ከሄዱት  በአኗኗር ዝቅተኘ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለተልዕኮው ቅርበት ካላቸው ምንጮች ለማወቅ ተችሎአል። በተልዕኮው ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ወታደሮ ዝቅተኛ የአኗኗር ደረጃና አካላዊ ብቃት ጉድለት የሚመለከቱ ከሌላ አፍሪካ አገራት የተሰባሰቡ መሰሎቻቸው እንዚህ ናቸው ወይ አባቶቻቸው ጣሊያንን ተዋግተው ያሸነፉ፣ በኮረያና በኮንጎ በመዝመት ታሪክ ያስመዘገቡ እያሉ እንደሚሳለቁባቸው ታውቋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተባበሩት መንግሥታት በስማቸው የሚሰበሰበው ገንዘብ እንዲከፈላቸው እየጠየቁ ያሉ እነዚህ በተልዕኮ ላይ ያሉ ወታደሮች፣ የከፈላቸዋል ተብሎ ቃል የተገባላቸው ወርሃዊ ክፍያ፣ ከፈቃዳቸው ውጪ ያለምንም ምክንያት መከላከያና የፌደራል ፓሊስ ባለስልጣናት አካውንት ውስጥ እየገባ እንደሆነ መረጃ እንዳላቸውና ይህ አሠራር በምን አግባብ ተግባራዊ ሊሆን እንደቻለ ተጣርቶ እንዲገለጽላቸው በቅርብ አዛዦቻቸው አማካይነት አቤቱታ እያቀረቡ ነው ተብሎአል። በሙስናና በዘረፋ እየተጨማለቁ ያሉ የህወሃት የጦር ጀነራሎች እየፈጸሙባቸው ያለውን ይህንን ዘረፋ ፓሪቲያቸው ህወሃት ጥልቅ ተሃድሶ አካሂዳለሁ እያለ ለተቃውሞ የተነሳሳውን ህዝባችንን ለማባበል ጥረት እያደረገ በሚገኝበት በዚህን ሰዓት ቅድሚያና ትኩረት ሰጥቶት እንዲመረምርላቸውና የገንዘብ ሚንስቴር ባለበት አገር ውስጥ እንዴትና ለምን የጦር አዛዦች በሚያስተዳድሩት አካውንት ውስጥ ገንዘባቸው እንደገባ የሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን እንዲያጣራላቸው እንዲደረገግ እያሳሰቡ ነው።
የመከላኪያ ሚንስቴርና ፖሊስ አንዳንድ ለስረአቱ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች በግል ለመጥቀም ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ እየላኩ ከፍተኛ ደመወዝና የቀን አበል እንዲከፈላቸውም እንደሚያስደርጉም እነዚሁ ምንጮች አረጋግጠዋል። ቀደም ሲል ወደ ላይቤረያ፣ ሩዋንዳ እና ብሩንዲ ተልከው የተመለሱ  800 ወታደሮች ከተባበሩት መንግስታት የተከፈላቸውን ገንዘብ አለማግኘታቸውን አስመልከተው ባሰሙት ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ወደጎጃም የሚወስደውን መንገድ  ፍቼ ላይ ዘግተው እንደነበረ በተለያዩ ሚዲያዎች ከተዘገበ በኋላ ሳሞራ ዩኑስና ሌሎች የህወሃት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያልተከፈለውን ገንዘብ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ በማግባባት ትጥቅ እንዳስፈቱዋቸውና ከመቀሌ ከተማ 10 ኪሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ቁሃ (Quiha) የተባለ ቦታ በአውቶብሶች አጓጉዘው እንደረሸኑዋቸው ለመከላኪያ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ይናገራሉ።  የልፋታቸውን ዋጋ በመጠየቃቸው በጭካኔ የተጨፈጨፉ እነዚያ 800 ወታደሮች በወቅቱ ያነሱትን የክፍያ ጥያቄ አስመልክቶ የAFP ጋዜጠኛ ያናገራው ጄነራል አለሙ አየለ የተባለ የህወሃት ጦር መኮንን  ችግሩ እንደተፈታና ለወታደሮቹ በዚያን ወቅት የተባበሩት መንግስታት በነፍሰወከፍ በየወር የከፈለው  1200 የአሜሪካን ዶላር በካሽ ወይም በቼክ እንደሚከፈላቸው  እንደሚደረግ የተሳሳተ መረጃ ሰጥቶ እንደነበረና በዚያን ወቅት የኮሚኒኬሽን ጉዳይ ሚንስቴር የነበረው በረከት  ስምኦን ችግሩ የማነጅመት ችግር እንደሆነና የተጠየቀው ገንዘብ እንደሚከፈላቸው ጄነራሉ የሰጠውን ቃል አረጋግጦ ለውጪ ሚዲያ ተናግሮ እንደነበረ የሚታወስ ነው።
የሰላም ማስከበሩን ተልዕኮ ለማሳካት በአሁኑ ሰዓት ግዳጅ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአገራችን ወታደሮች እያሰሙት ያለውን ቅሬታ የተባበሩት መንግስታት እንዲያውቅላቸውና በስማቸው እየነገደ ያለው አገዛዝ የወሰደባቸውን ገንዘብ መልሶ እንዲከፍላቸው እንዲያደርግ አቤቱታቸው እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment