ዋዜማ ራዲዮ- ሰኞ ማምሻውን በኢህአዴግ የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት የተደረገ የከፍተኛና መካከለኛ ካድሬዎች ዉይይት ላይ ተጠያቂነት አለመኖር በሕዝብ ላይ እየፈጠረ ስላለው ቅሬታ ተወስቷል፡፡ በዚህ ዉይይት የልማት ባንክ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ለሕግ አለመቅረባቸው እንደ አንድ ጉልህ ማሳያ መነሳቱ የተነገረ ሲኾን ሕዝብ በጥልቅ ተሀድሷችን ላይ እምነት እንዲያጣ ከሚያደርጉ ተግባሮች አንዱ እንዲህ አይነቱ የተጠያቂነት አለመኖር እንደሆነም ተብራርቷል፡፡
ከፍተኛ የሚባል ምዝበራ እንደተካሄደበት በምርመራ የተጋለጠው የልማት ባንክና የሰፋፊ እርሻዎች ጉዳይ ባለፉት ሳምንታት በአገር ቤት ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን አግኝቷል፡፡ የአቶ ኢሳያስ ባህረ ከኃላፊነት የመነሳታቸው ምክንያት ግን ከመላምት ዉጭ አሁንም በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጄኔራል በኾኑት በአቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ፊርማ ከሥራ መሠናበታቸው የተገለጸላቸው አቶ ኢሳያስ “እኛን በወጣት ለመተካት ከሆነ እርምጃው ጥሩ ነው” በሚል ፌዝ የሚመስል ንግግር ተናግረው ነበር፡፡ በቀጣይ ምን መስራት እንደሚፈልጉ ሲጠየቁም “ለጊዜው እረፍት ማድረግ ነው የማስበው” ሲሉ ለቢዝነስ ጋዜጦች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ተሰናባቹ ፕሬዚደንት በሚመሩት መሥሪያ ቤት የተበላሸ ብድር ጋር በተያያዘ ሊጠየቁ የሚችሉት አግባብ እንደሚኖር ሲገመት ቢቆይም ይህ ሲኾን ግን አልታየም፡፡
በጋምቤላ የሰፋፊ እርሻዎችን ለማስኬድ ከ4.3 ቢሊየን ብር በላይ ለባለሀብቶች ፈሰስ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ዉስጥ 84 በመቶው ብቻ ለታሰበለት አላማ መዋሉ ሲረጋገጥ ቀሪው የት እንደደረሰ የሚያውቅ የለም፡፡ ያለፉትን ሦስት ወራት ሳይጨምር እስከ 2008 መጨረሻ 215 ሚሊየን ሄክታር መሬት 16ሺ ለሚኾኑ ባለሐብቶች ተላልፏል፡፡ ከዚህ ዉስጥ ለማ የተባለው 64ሺ ሄክታሩ ብቻ መኾኑ በመንግሥት በተቋቋመና በአቶ አለማየሁ ተገኑ በተመራ ልዩ ኮሚቴ ከተደረሰበት በኋላ በብዙዎች ዘንድ ግርምት ፈጥሯል፡፡ ኮሚቴው በባንኩ አመራሮችና በባለሐብቶች መካከል ጉዳይ በማስጻጸም የድለላ ሥራ የሚሠሩ 22 ሰዎችን ከነ ሙሉ ስም ዝርዝራቸውና አድራሻቸው ጭምር በሪፖርቱ ይፋ አድርጎ ነበር ተብሏል፡፡
“አቶ ኢሳያስ በብድር አሰጣጡ ሂደት አድልዎ ፈጽመዋል፤ ለተወሰኑ ባለሐብቶች ግዙፍ ብር እንዲተላለፍ አድርገዋል፤ ባለሐብቶቹ የተወሰኑት ብሩን አሸሽተዋል፤ ቀሪዎቹም ከእርሻ ሌላ ባለ ቢዝነስ ሲሰሩበት ነበር ተብሏል፡፡ በብድሩ ፎቅ የሰሩ ሰዎች እንዳሉ ሲነገረን ነበር፤ ይህ ሁሉ ሲባል እንሰማለን፣ የሚባለው እውነት ከሆነ ታዲያ ለምን አይጠየቁም?” ሲሉ ሁለት ሦስት ካድሬዎች ጥያቄ አንስተዋል፡፡
“መቼስ ይሄ ሁሉ ምዝበራ ሲካሄድ አንድ ተጠያቂ አካል መኖር አለበት፤ ኢሳያስንም የኾነ ቦታ ብትሾሙት ሕዝቡ የቱ ጋ ነው መታደሳችሁ እንደሚለን ማወቅ አለብን፣ ሕዝብ በተሀድሷችን እምነት ካጣ ሌላ ምን የሚቀረን ነገር ይኖራል ” ሲሉ የተናገሩም ነበሩ ተብሏል፡፡
ከተጠያቂነት ጋር በተያያዘ ከአቶ ኢሳያስ ባህረ ሌላ ስማቸው የተነሳው የቀድመው የአዲስ አበባ መስተዳደር የካቢኔ አባልና የጥቃቅናና አነስተኛ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ደስታ ፍጹም ናቸው፡፡ አቶ ደስታ መንግሥት የሰጣቸውን ሰፊ የቀበሌ ቤት አፍርሰው ዘመናዊ ቪላ በራሳቸው ወጪ መገንባታቸው የተነሳ ሲኾን ምንጩ ያልታወቀ ሀብታቸው እንዲጣራ ተጠይቋል፡፡ ይህን ብዙ ሰው ያውቃል፡፡ በግልጽ በሙስና የተጨማለቁ ሰዎች ካልተጠየቁ ጥልቅ ተሀድሶ እያደረግን መሆናችን ምኑ ላይ ነው የሚል ተመሳሳይ ሀሳብ ተሰንዝሯል፡፡
በካድሬዎች ስብሰባ የርስበርስ መገማገም ካልሆነ እምብዛምም ስም እያነሱ በግልጽ መወቃቀስ የተለመደ እንዳልነበረ የተናገረ አንድ ወጣት ካድሬ፣ ለኔ ይሄን እንደ በጎ ለወጥ እመለከተዋለሁ ሲል ለዋዜማ ተናግሯል፡፡
በስብሰባው ምላሽ የሰጡ ኃላፊዎች የተጠያቂነት ጉዳይ በዘመቻ ለማካሄድ ፍላጎት እንደሌለ፣ ይህን ማድረግ አባላትን ሊያስደነብር እንደሚችልና በሂደት ግን የሚጠየቁ እንደሚኖሩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ለዋዜማ የደረሰ ግርድፍ መረጃ እንደሚያስረዳው በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት በየክፍለ ከተሞች ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፋፊ ዉይይቶች ይካሄዳሉ፡፡ የበታች ሀላፊዎችም በሕዝብ በአውጫጪኝ መልክ ሂስና ትችት ፊትለፊት እንዲቀርብባቸው ይደረጋል፡፡ በርከት ያለ ወቀሳ የሚቀርብበት ኃላፊ ከስልጣኑ ሊነሳ እንዲሁም ሊታሰር ይችላል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ምናልባት ከሰሞኑ በርከት ያሉ መካከለኛና ዝቅተኛ ኃላፊዎች ለእስር ሊዳረጉ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ በካድሬዎች የሰኞ ምሽት ዉይይት የተንጸባረቁ ሀሳቦች እንደሚያመላክቱት ከሆነ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፍ ኅብረተሰቡን ሲያጉላሉ ነበር የተባሉ፣ በሙስና የሚጠረጠሩ፣ በሕዝብ ጥቆማ ጭምር በመታገዝ በስፋት ለሕግ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ህዝቡ የመታደሱ ሂደት የምር እንደሆነ እንዲረዳ ፍላጎት በመኖሩ ለዚህ መስዋእት የሚደረጉ መካከለኛ አመራሮች መኖራቸው አይቀርም ተብሏል፡፡ ይህ የዘመቻ እስር ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ባያካትት እንኳ በመጠኑ በርከት ያሉ ዝቅተኛና መካከለኛ ቢሮክራቶችን እንደሚያካትት ተገምቷል፡፡
No comments:
Post a Comment