ንቅናቄው ይህንን እምነቱን የገለጸው ጥር 12 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት በእንግሊዘኛ ቋንቋ አዘጋጅቶ ባሰራጨው ርዕሰ አንቀጽ ነው።http://amharic.abbaymedia.com/%
ያሳለፍነው የፈረንጆች 2016 በአገራችን ታሪክ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከተመዘገበባቸው አንዱ ነበር በማለት የጀመረው የንቅናቄው ርዕሰ አንቀጽ ከሁለት አሥርተ ዓመት በላይ የዘለቀው ጨቋኝና አግላይ የሆነ የመንግሥት ሥርዓት እንዲቀየር በአራቱም ማዕዘን የሚገኘው በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ህዝባችን ፍጹም ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ተቃውሞውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥቶ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የተለመደው የህወሃት/ኢህአደግ ጨካኝ የጥቃት እርምጃ ሠለባ በመሆን በመቶዎች የሚቆጠሩት ለሞት የተዳረጉበት ከአሥር ሺዎች በላይ ደግሞ ወደ ተለያዩ የታወቁና ያልታወቁ እስር ቤቶች ተግዘው መከራና ሲቃይ በመቀበል ላይ የሚገኙበት ሁኔታ ፈጥሮአል ብሎአል።
በመቀጠልም በአገራችን ከሰፈነው የፖለቲካ አፈና በተጨማሪ ተጠናክሮ የቀጠለው ዜጎችን ከኑሮአቸውና ከቄያቸው የማፈናቀል እርምጃ እንዲሁም ዘረኝነትን መስፈርት ባደረገ አሠራር ሌላውን ማህበረሰብ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያማራቅ እርምጃ ችግሮቻችንን በማባባስ በመላው አገራችን ውስጥ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲነግስና አብዛኛው ህዝብ ሥልጣን ላይ ካለው አገዛዝ ምንም ነገር በተስፋ እንዳይጠብቅ አድርጎታል በማለት ገልጾአል። አንድ ህዝብ ለደህንነቱና ለጥቅሙ ዋስትና መስጠት በሚኖርበት በራሱ መንግሥት ሲዋረድ፤ ከኑሮው ሲፈናቀል፤ በጭካኔ ሲደበደብ፤ ሲታሰርና ሲገደል ነጻነቱን መልሶ ለመቀዳጀት ሲል ወደ ጠርዝ በመገፋት እራሱን ወደ መከላከል እርምጃ ከማምራት ውጪ ምንም ምርጫ አይኖረውም ያለው የንቅናቄው ርእሰ አንቀጽ በቅርቡ በባህርዳርና በጎንደር ከተሞች ደርሰዋል የተባሉ የፈንጅ አደጋዎች አይነት ጥቃቶች በመንግሥት ላይ ያለው የተስፋ መቁረጥ እርምጃዎች ከሚፈጥሩዋቸው ክስተቶች አንዱ እንደሆነ የተለያዩ አገሮች ልምዶች ማሳየቱን ጠቅሶአል። ሆኖም ግን ህወሃት ቀደም ባሉ አመታት ህዝብ በሚሰበሰብባቸውና በሚያዘወትራቸው ሠላማዊ ቦታዎች ፈንጅ በመጥመድና በማፈንዳት ህብረተሰባችን የሚያካሄደውን የመብት ትግል የሚመሩ ድርጅቶችን በሽብርተኝነት ለመክሰስና ደጋፊ የተባሉትን ለመምታት በተደጋጋሚ ሲጠቀምበት የታየ በመሆኑ በባህርዳርና በጎንደር የተከሰተው ፍንዳታ በህብረተሰቡ መካከል ስጋትና ጥርጣሬን ለመፍጠር በራሱ በህወሃት ሊቀነባበር እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው በማለት ድርጊቱን ማንም ይፈጸመው በሃላፊነት መጠየቅና መኮነን ያለበት ሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ አገዛዝ ነው ብሎአል አርበኞች ግንቦት 7 ።
አያይዞም የምናካሂደው የነጻነት ትግል በአገራችን ፍትህ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነበት ሥርዓት ለማምጣት በመሆኑ ሲቪሉ ህብረተሰባችን የሚሰበሰብባቸውና የሚገለገልባቸው ቦታዎችና የህዝብ ንብረቶች በሙሉ በምንም ዐይነት መንገድ የጥቃት ዕላማ እንዳይሆኑ ለነጻነት የሚታገሉ ሃይሎች ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማሳሰብ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቆአል።
በመጨረሻም የ25 አመታት አፈናና ጭቆና የፈጠረውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና እርሱን ተከትሎ እየተወሰደ ያለው የተጠናከረ የሃይል እርምጃ አገራችን ኢትዮጵያ የገባችበትን የፖለቲካ ውጥረት በማባባስ ለቀጠናው ጭምር የሚተርፍ የጸጥታ አደጋ ያዘለ መሆኑን የአለም አቀፍ ህብረተሰብ እንዲረዳ በዚህ ርዕሰ አንቀጽ ጥሪውን ያስተላለፈው አርበኞች ግንቦት 7፤ አስተማማኝ የሆነ ሠላምና መረጋጋትን በወታደራዊ ሃይል የተቀዳጁ የአለም አገሮች እንደሌሉ ሁሉ የአገራችን ኢትዮጵያም ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ ያልተለየ መሆኑን ተረድተው ለሠላም ያለው ጊዜ ሳይዘገይ በወዳጃቸው በህወሃት ላይ ተጽዕኖአቸውን እንዲያሳርፉና ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ከወዲሁ እንዲጥሩ አሳስቦአል።
No comments:
Post a Comment