አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ
ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የእሳት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ አቃቤ ህግ በበርካታ ግለሰቦች ላይ ክስ እንደመሰረተ ይታወሳል።
ከ500,000 ብር በላይ አገዛዙን በትግል ለመገርሰስ ከሚሰሩ ድርጅቶች በመቀበል በማረሚያ ቤቱ ሁከትን በማነሳሳት ከ120 በላይ ግለሰቦችን አቃቤ ህጉ መወንጀሉም ይታወቃል።
በማረሚያ ቤቱ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለጠፋው ህይወትና ንብረት ተጠያቂ የስዊድን ዜግነት ባለው በዶክተር ፍቅሩ ማሩ የሚመራው የእስረኛ ቡድን እንደሆነም በክስ መዝገቡ ሰፍሯል።
በጥር 8 ቀን 2009ዓም በዋለው የፊደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ በአቃቤ ህጉ ለቀረበባቸው ክስ ያዘጋጁትን የጽሁፍ መቃወሚያ በጠበቆቻቸው በኩል ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።
ተከሳሾች በጽሁፍ ባቀረቡት መቃወሚያ ክሱ ግልጽነት እንደሚጎድለው አስታውቀዋል። በተጨማሪም አቃቤ ህጉ በነፍስና በንብረት ማጥፋት ወንጀል ክስ ሲመሰርት ያቀረባቸው መረጃዎች የተሟሉ እንዳልሆኑ በጽሁፉ ተጠቅሷል።
ተከሳሾች አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ ድርጅቶች በመመሳጠር ፣ አባል በመሆንና ተልእኮ በመቀበል በነሐሴ 28 ቀን 2009ዓ.ም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለደረሰው አደጋ ተጠያቂ ናቸው በማለት አቃቤ ህጉ መክሰሱ ይታወሳል።
ተከሳሾች ባቀረቡት የጽሁፍ ተቃውሞ አሸባሪ የተባሉት ድርጅቶች በማን እንደተፈረጁ አቃቤ ህጉ በዝርዝር እንዳላቀረበም ገልጸዋል።
ዶክተር ፍቅሩ ማሩም በጥር 9 ቀን 2009ዓም በዋለው የፊደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በመገኘት ለቀረበባቸው ክስ መቃወሚያቸውን በጠባቃቸው በኩል በጽሁፍ አቅርበዋል።
አቃቤ ህግ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በማረሚያ ቤቱ እስረኞችን በቡድን በማደራጀትና በመምራት ለ22 ሰዎች ህይወት ማለፍና ወደ15 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት መጥፋት ተጠያቂ ናቸው በማለት ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
ይህንን ክስ በጽሁፍ የተቃወሙት ዶክተሩ አቃቤ ህጉ በምርመራ ወቅት ሰብስቤ ያዝኩዋቸው ያላቸውን መረጃዎች በዝርዝር እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
በተያያዘ ዜናም ማረሚያ ቤቱ ከመቃጠሉ በፊት የተለያዩ የመገናኛ ስልኮችንና ገንዘብን በማስገባት ሲተባበሩ ነበሩ በተባሉ አምስት ተጠርጣሪ የማረሚያ ቤቱ ጥበቆች ላይም ክስ ሊመሰረት እንደሆነም ተሰምቷል።
በአጠቃላይ አቃቤ ህጉ ተከሳሾቹ ላቀረቡት ተቃውሞ መልስ በጽሁፍ እንዲያቀርብ ለጥር 24 ቀን 2009ዓም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል። የእነ ዶክተር ፍቅሩ ማሩን የፍርድ ሂደት በዝግ ችሎት እንዲታይ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ጥያቄም በዚሁ ተለዋጭ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ምላሽ እንደሚጸጥም ታውቋል።
No comments:
Post a Comment