አዲስ የድርቅ አደጋ በተከሰቱባቸው አራት ክልሎች ወደ 24 ሺ አካባቢ የሚደርሱ ቤተሰቦች በድርቁ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አደረገ።
ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በአፋር ኦሮሚያ፣ ደቡብና የሶማሊ ክልሎች ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።
ይህንኑ የድርቅ አደጋ መባባስ ተከትሎ 23ሺ 764 ቤተሰቦች ከመኖሪ8ያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለአስቸኳይ የምግብና ምግብ ነክ ላልሆኑ ዕርዳታዎች መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርቁን አስመልክቶ ባወጣው ሳምንታዊ ሪፖርቱ አመልክቷል።
በአራቱ ክልሎች በመዛመት ላይ ባለው የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ርብርብ ካላደረገ የከፋ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ተተንብዮአል።
የድርቁ ሁኔታ መባባስን ተከትሎ በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዞኖች ቆዳን በሚያሳክክ ወረርሽን እየተጠቁ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የድርቁ ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መቀጠሉን የገለጸው ድርጅቱ ተመሳሳይ የበሽታው ምልክቶች በአማራና ትግራይ ክልሎች በመታየት ላይ እንደሚገኝ በሪፖርቱ አስፍሯል።
በደቡብ ክልል ካሉ 148 ወረዳዎች መካከል 82ቱ በወረርሽኙ የተጠቁ ሲሆን፣ በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ ዞኖች ስር የሚገኙ 10 ወረዳዎችም ቆዳን በሚያሳክከው በሽታ እየተጠቁ መሆኑ ተመልክቷል።
አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ተላላፊ ነው የተባለውን ይህንኑ የበሽታ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ታውቋል። አዲስ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በምግብ እጥረት ላይ ካስከተለው ችግር በተጨማሪ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ስጋት ማሳደሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።
ባለፈው ሁለትና ሶስት ወራቶች ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በድርቁ ምክንያት የሞቱ ሲሆን፣ ባልተለመደ ነው በተባለ መልኩ በአፋር ክልል ድርቅ ጉዳት እያደረሰባቸው ያሉ እንስሳት ወደ አማራና ትግራይ ክልሎች በመሰደድ ላይ መሆናቸውንም የድርጅቱ ሪፖርት አመልክቷል።
በተያዘው የፈረንጆች 2017 አም በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታን ለማቅረብ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግም ጥሪ መቅረቡ የሚታወስ ነው።
በተያያዘ ዜናም በኢትዮጵያ የተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ በተለይ በአርብቶ አደር ማህበረሰብ ዘንድ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ሲሉ አለም አቀፍ ተቋማት ማሳሰባቸውን ሮይተርስ ማክሰኞ ዘግቧል።
በሺዎች ለሚቆጠሩ እንስሶች ሞት ምክንያት የሆነው ይኸው የድርቅ አደጋ በተያዘው 2017 የፈረንጆች አም ከባለፈው አመት በተለየ መልኩ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ስጋት መኖሩን የአለም ምግብ ፕሮግራም ዋቢ በማድረግ የዜና አውታሩ አመልክቷል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርቁ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የአለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ለድርቁ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በተፈለገው ሰዓትና መጠን መድረስ ካልተቻለ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል በማሳሰብ ላይ ናቸው። ከአንድ አመት በፊት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ በቂ ትኩረትና ጥሪ እንዳልተደረገለት የተለያዩ ድርጊቶች ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment