![No automatic alt text available.](https://scontent-arn2-1.xx.fbcdn.net/v/t1.0-9/16265922_395662044119860_8035958476564007436_n.jpg?oh=6f988d20b30a617ea928665a6eedddc0&oe=5903819D)
በጥር ፳ ቀን፳፻፱ ዓም አዘጋጁ ያቀረበው የቀድሞ ሠራዊት ቤተሰብ ልጅ የባሻው ግርማ ልጅ አቶ ታደሠ በቃለ መጠይቁ ወቅት ይሰጥ የነበረው በሳግና በለቅሶ የታጀበ መልስ ግን የሚያዳምጠውን በሙሉ መንፈስ የሚረብሽ ስለመሆኑ ለአፍታ አልጠራጠርም ። ምንአልባትም በዓለማችን ማን ያውቃል በሬዲዮን የቃለ ምልልስ ወቅት በረዠሙ የፈሰሱ እንባዎችና ሳግ የተቀላቀለባቸው ሊሆኑ ይችላሉ ። መቼስ ሰው ነኝና እኔም ተከፋሁ ተረበሹኩኝ ። ቀጥታ ላፕ ቶፑን ከፈትኩና በደሉን በቃላት ልጋራው ብዬ ይህችን የግጥም ስንኝ በችኮላም ቢሆን ደረደርኩኝ። ገና ጆሮ አይሰማው የለ ! ስንት በደል ፤ስንት ግፍ ፤ ስንት ጭካኔ ! ዕድሜ ይስጠን ብቻ !
እንጉርጉሮ !
=======
ሳግም ሲቃ ይዞን ፤ ዛሬም እናለቅሳለን
ክብርና ማዕረጉን፤ በባለቀኖቹ ለተገፈፈብን
ለቀድሞው ሠራዊት ፤ ወድቆ ለቀረብን
ማንም ያልደፈረው ፤ መከላከያችን
ድንበሩን ጠብቆ ፤ አጥሩን አጥብቆ
ባዕድ ጠላቶቹን ፤ በንቃት ጠብቆ
የኖረው ሠራዊት ፤ ተከብሮ ተደንቆ
ምስቅልቅሉ ወጣ ፤ ጥላሸት ተቀብቶ
በአገር አፍራሾቹ ፤ በመሰሪዎቹ ፤እንዳይሆን ተንቆ ።
ሻምበል ሥራ በቃ ፤ ወቴ ብላ ጠጣ
ግዳጅ ሊፈጽም ነው ፤ ሠራዊቱ መጣ።
ብለን እንዳልጨፈርን ፤ በሜዳ ጨዋታ
ቀውሱን ተጋራነው ፤ ልጆቹም በተርታ።
ሃዘን አኮራምቶን፤ ተርበን ታርዘን
መኖሪያ ቤት አጥተን፤ ቀያችንን ትተን
በደል ሲበዛብን ፤ ኑሮው ምርር ሲለን
ተበታትነን ቀረን፤ ልጅነት ሳያምረን
ሥራ ሠርተን መኖር፤ መታገል ጀመርን
አሳዳጊ አጥተን ፤ የሚንከባከበን
ተስፋችን ጨልሞ ፤ በልጅነታችን
ኑሮውን ገፋነው ፤ እንዳይሆኑ ሆነን።
አይዟችሁ እደጉ ፤ ግቡ ትምህርታችሁ
የነገዋ ኢትዮጵያ ፤ ተስፋ ልጆች ናችሁ።
የሚለን ሰው ጠፍቶ ፤ የሚያበረታታን
ኖርናት ስናለቅስ ፤ የልጅ ዕንባ አፍሰን
ሳናየው በናፍቆት ፤ ፎቶ ብቻ እያየን
ወታደሩ አባባን ፤ የኛው መመኪያችን
ለሃገሩ ግዳጅ ፤ በሞት ለተለየን
የወደቀበትን ፤ መቃብሩን እንኳን
ሳናውቅ እ ን ኖ ራ ለ ን !
ወታደሩ አባባ ፤ እንወድሃለን፤ እንዘክርሃለን !
መታሰቢያነቱ ለሁሉም የቀድሞው መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ሠራዊት አባላትና ቤተሰቦቻቸው ይሁን !
ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ
ጥር ፳ ቀን ፳፻፱ ዓም
No comments:
Post a Comment