Wednesday, October 21, 2015

የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ



‪#‎የህወሓት‬ አገዛዝ ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚከዱ አባላትን ጨርሶ መቆጣጠር ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተረጋገጠ፡፡
‪#‎በጎንደር‬ ወገራ ወረዳ በአራት ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ ደርሶ ነዋሪዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው እና የቤት እንስሶቻቸውም በማለቅ ላይ መሆናቸውም ተሰማ፡፡
#የህወሓት አገዛዝ የላይ አርማጭሆ ሙሴ ባንብ ነዋሪ የሆኑ 50 ወጣቶችን በስብሰባ ስም በኃይል ጠርንፎ ይዞ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ እያለ በምርመራ እያስጨነቃቸው እንደሚገኝ የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች የላኩት መረጃ አጋለጠ፡፡
#በጎንደር ከተማ ወላጆች ልጆቻቸውን በአገዛዙ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማስመዝገብ ለደላሎች በአንድ ሰው ከ500-1000 ብር እንዲከፍሉ በመገደዳቸው ከፍተኛ ምሬት ውስጥ ናቸው፡፡
====================================================
የህወሓት አገዛዝ ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚከዱ አባላትን ጨርሶ መቆጣጠር ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተረጋገጠ፡፡
የህወሓት አባላት በሆኑ የይስሙላህ የጦር መኮንኖች ከታች እስከላይ ተጠርንፎ በጉልበት ተይዞ በአገር መከላከያ ስም እየተጠራ ነገር ግን በፀረ-ህዝብነት ሳይወድ በግድ እንዲሰለፍ እየተደረገ የሚገኘው ሰራዊት ስርዓቱን መክዳቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ፈፅሞ ከአገዛዙ ቁጥጥር ውጭ ሆኗል፡፡
በተለይም ደግሞ ማዕከላዊ ዕዝ እና ምዕራብ ዕዝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት የከዳባቸው መሆናቸው ታውቋል፡፡
በማዕከላዊ ዕዝ እና በምዕራብ ዕዝ ውስጥ የሰራዊቱ አባላት ስርዓቱን ጥሎ መክዳት ተባብሶ የቀጠለ በመሆኑ የሰራዊቱ አባላት የትምህርት ማስረጃቸውንና ሌሎችን ሰነዶች ለመያዣነት እየተነጠቁ ይገኛሉ፡፡
በማዕከላዊ ዕዝ እና በምዕራብ ዕዝ በሰፊው እየተተገበረ የሚገኘው ይህ የትምህርት ማስረጃ እና ሌሎችም የግል ሰነዶች ንጥቂያ በተለይም የሙያተኛ መኮንኖችን መክዳት ለመግታት ታስቦ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ድርጊቱ በሰራዊቱ ውስጥ እልህና ቁጣን ቀስቅሶ ይገኛል፡፡ ከጫፍ የደረሰ ኩርፊያም ጭምር አስከትሏል፡፡
በማዕከላዊ ዕዝ ዕና በምዕራብ ዕዝ ውስጥ ሲከዱ ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሰራዊቱ አባላት እንዳሉ የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የታጠቁ የነፃነት ድርጅቶች ባልተጠበቀ ሰዓት ጥቃት ሊከፍቱ ይችላሉ ተብሎ በመስጋቱ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን ታዞ በአካባቢው ከፍተኛ ጥበቃ አየተደረገ ይገኛል፡፡
በጎንደር ወገራ ወረዳ በአራት ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ ደርሶ ነዋሪዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው እና የቤት እንስሶቻቸውም በማለቅ ላይ መሆናቸውም ተሰማ፡፡
ከፉኛ በድርቅ የተመቱት አራቱ ቀበሌዎች ሶምያ፣ ጓሪ፣ ግጭሆ እና ቧግሽ ሲሆኑ ከብቶቹ እንደ ቅጠል እየረገፉበት እና ጠኔ ፀንቶበት የሚገኘው የእነዚህ ቀበሌዎች ህዝብ የአድኑን ተማፅኖ ጥሪውን ድምፅ በተደጋጋሚ ለአገዛዙ ቢያሰማም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልተሰጠውም፡፡
በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተከሰተው ከባድ ድርቅ ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በትንሹ ከ10 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በምግብ እጥረት ለርሃብ አደጋ ተጋልጦ በሞትና በህይወት መካከል ይገኛል፡፡
መጠነሰፊና ተከታታይ ድግሶችን በማሰናዳት የአገሪቱን ከፍተኛ ሃብት በማውደም ተግባር ላይ ተጠምዶ የከረመው የህወሓት አገዛዝ ምንም እንኳን መጀመሪያ የሌሎች አካላት ድጋፍ አያስፈልገኝም ሲል በአደባባይ ቢደመጥም አሁን ደግሞ እንደገና በድርቁ የተጠቁ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በመመገብ ነብሳቸውን ለመታደግ 596 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልገው ለለጋሽ አገሮች እየተናገረ ነው፡፡
የህወሓት አገዛዝ የላይ አርማጭሆ ሙሴ ባንብ ነዋሪ የሆኑ 50 ወጣቶችን በስብሰባ ስም በኃይል ጠርንፎ ይዞ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ እያለ በምርመራ እያስጨነቃቸው እንደሚገኝ የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች የላኩት መረጃ አጋለጠ፡፡
የአርማጭሆ እና የወልቃይት ህዝብ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የተባለውን ዘረኛ ቡድን መቃወም የጀመረው ገና ከሽፍትነት ዘመኑ አንስቶ ሲሆን አሁንም ለነፃነቱ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ተነግሮ የማያልቅ መሰዋዕትነት መክፈሉን ቀጥሏል፡፡
"እምቢ በኃይል አልገዛም!" "ግፍና በደልን ዝም ብዬ አልጋትም!" በማለት ያልተቋረጠ የነፃነት ትግል እያደረገ የሚገኘውን የአርማጭሆ ህዝብ በመሳሪያ ጉልበት አንገቱን ለማስደፋት በማለም የህወሓት አገዛዝ በአካባቢው ከፌደራል ፖሊስ፣ ከልዩ ኃይልና ከሚሊሻ ታጣቂዎች በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ጦር ሰራዊት አስፍሮ ይገኛል፡፡
ህዝቡ ደግሞ በበኩሉ ተወልዶ ባደገበት ቀዬ በሰላም መኖር ስላልቻለ ጠብመንጃውን እየወለወለ በየቀኑ ወደ በረሃ መውረዱን እና ጠብመንጃ ነካሽ የሆነውን የህወሓት ዘረኛ ቡድን በጠብመንጃ መፋለሙን ቀጥሏል፡፡
በመሆኑም በአርማጭሆ ምድር ከያቅጣጫው ፍንዳታ ሳይደመጥ እና ግድያ ሳይፈፀም ውሎ አድሮ አያውቅም፡፡ የሞት መርዶም ያልተሰማበት ዕለት በስህተት እንኳ አይገኝም፡፡
ይህ የአርማጭሆ ህዝብ በአንድነት ተነስቶ እያደረገው የሚገኘው በነፍጥ የተቃኘ የነፃነት ትግል ለስልጣን ህልውናው በዕጅጉ ያሰጋው የህወሓት አገዛዝ በትንሹ 50 የሚሆኑ የሙሴ ባንብ ወጣቶችን በስብሰባ ስም በአንድ ቦታ ላይ አጉሮ "ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ፤ ወጣቶችን እየመለመላችሁ ትልካላችሁ፤ ነገ ከነገ ወዲያ እናንተም ሄዳችሁ መቀላቀላችሁ አይቀርም..." የሚል በዛቻና ማስፈራራት የታጀበ አስጨናቂ ምርመራ አድርጎ ምንም ጠብ ሚል ነገር ሊያገኝ ባለመቻሉ በኃይማኖት አባቶች ጭምር እየተማፀነ ነው፡፡
መስቀል የያዙ የአካባቢው ካህናት ወጣቶች በታጎሩበት ቦታ በግዴታ እንዲገኙ ተደርገው ወጣቶች ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ከሌላቸው እንዲምሉ እየተጠየቁ ይገኛሉ፡፡ ካህናቱም ወጣቶቹ ወደፊት ወደ በረሃ ወርደው አርበኞች ግንቦት ሰባትን እንዳይቀላቀሉ በግዝት እንዲያስሯቸው በአገዛዙ ካድሪዎችና የታጠቁ ቡድኞች እየተገደዱ መሆናቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
በጎንደር ከተማ ወላጆች ልጆቻቸውን በአገዛዙ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማስመዝገብ ለደላሎች በአንድ ሰው ከ500-1000 ብር እንዲከፍሉ በመገደዳቸው ከፍተኛ ምሬት ውስጥ ናቸው፡፡
በአገሪቱ ላይ የአስተሳሰብ ዕድገትን ሳይሆን የአስተሳሰብ መቀጨጭን የሚያመጣ እና ማንነትን በማጥፋት ዜጎች የስርዓቱ ባሪያ ሆነው እንዲፈበረኩ በማድረግ አገዛዙን በስልጣን መንበር ላይ አስቀምጦ ለማሰንበት ብቻ ተቀዳሚ አላማ ግቡ ያደረገ የትምህርት ስርዓት ፖሊሲ በመኖሩ እና የህወሓት ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንጂ በዘርፉ ምንም ዕውቀት የሌላቸው ተራ ካድሬዎች በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በአመራርነት በመሰግሰጋቸው ትምህርትን በተመለከተ ኢትዮጵያ በዘመኗ ፈፅሞ አታይው ከማታውቀው ውድቀት ላይ ደርሳለች፡፡
ህወሓት ህፃናትን ሳይቀር ከታች ክፍል እስከ ላይ እስከ ዮኒቨርሲቲዎች ድረስ በዚህ አገርና ህዝብን በሚያበላሽ የትምህርት ፖሊሲና አሰራር የሚያልፉ ተማሪዎችን አንድ ለአምስት ጠርንፎ ነፃነታቸውን አፍኖ አስተሳሰባቸውን በመግደል ባሪያ አድርጎ ሊገዛቸው በሰፊው እየሰራ ይገኛል፡፡
ይባስ ብሎ ደግሞ በጎንደር ከተማ በሚገኙ የዕሱ የግል ንብረቶች በሆኑት ትምህርት ቤቶች ላይ ደላሎችን አሰማርቶ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ የሚመጡ ወላጆችን ከ500-1000 ብር በማስከፈል ዘረፋውን ጎን ለጎን ተያይዞታል፡፡ 
ህወሓት አገሪቱን ከተቆጣጠረበት ከ1983 ዓ.ም እስካሁን እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በጎንደር ከተማ ከአንድ ህዳር 11 እየተባለ ከሚጠራ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በስተቀር ምንም አይነት ትምህርት ቤት አልገነባም፤ በመሆኑም በጎንደር ከተማ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የሆነ የክፍል ጥበትና እጥረት መኖሩን ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment