Friday, October 9, 2015


እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆነ ራሽያ ከጦር መርከቦቿ ላይ የምትተኩሳቸው ሚሳኤሎች ኢላማቸውን ከመሳት አልፈው ሀገር አቋርጠው ኢራን ሀገር እየፈነዱ ነው። ይሁንና ራሽያ ዘገባውን አጣጥላዋለች። ራሽያ እንደምትለው ከሆን የሚወነጨፉት ሚሳኬሎች (Laser-Guided) ናቸው። ራሽያ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ እንደ አሜሪካ በተለያዩ ጦር ግንባሮች ተሰልፋ ዘመናዊ መሳሪያዎቿን ሳትፈትሽ ኖራለች እናም ይህ ሶርያ ውስጥ በማከናወን ላይ ያለችው የጦር ድግስ ብርታቷን ለማሳየትም ጭምር እንደሆነ ይታመናል።
ከራሽያ ጋር አብራ የተሰለፈችው ሌላኛይቱ ሃገር ኢራን ናት፣ ኢራን በሺዓ እስልምና ህግ የምትተዳደር ሃገር እንደመሆኗ መጠን እግረኛ ጦሯን ወደ ሶርያ ልካ ሺዓ መራሹን የአሳድ መንግስት ለመታደግ በመጣር ላይ ናት፣ በዚህም ምክንያት በትላንትናው እለት አንድ የኢራን ከፍተኛ ጀነራል ሶርያ ውስጥ መገደሉ ተሰምቷል።
አሜሪካኖቹ የፑቲን መንግስት ሶርያ ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶ ሳር ቅጠሉን በቦምብ ማጋየቱን አልወደዱትም፣ ክፉኛ የመበለጥ ስሜት ውስጥ ያሉ ይመስላል። በአይኤስአይኤስ ድርጊት የበገኑ የራሽያን ድርጊት በደስታ ተቀብለውታል፣ ይሁንና የአሳድ መንግስት ተቃዋሚዎችና እነርሱን የሚደግፉ የሱኒ አረቦች በሁኔታው ደስተኛ አይደሉም፣ ፑቲን እያጠቃ ያለው አይኤስአይኤስን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የአሳድ ተቃዋሚዎችን ነው ባይ ናቸው።
የራሺያ እና የአሜሪካ የጦር ጀቶችም እንደተጠበቀው ቦምቦቻቸውን የሚጥሉበት ቦታ በማሰስ ላይ እያሉ በሶርያ አየር ላይ መተያየታቸው አልቀረም፣ ሁኔታው ያላማራቸው የአሜሪካ ፓይለቶች ጎመን በጤና ብለው በፍጥነት ወደ ጠቅላይ ሰፈራቸው ተመልሰዋል።

No comments:

Post a Comment