Monday, October 12, 2015

በቴፒ አንድ የፖሊስ አባል ሲገደል አምስት ፖሊሶች መታገታቸው ተሰማ

 :-ለአመት የዘለቀው የቴፒ ግጭት በአካባቢው ለሰፈረው የፌደራል ፖሊስ እና ለፌደራል ባለስልጣናት እንቆቅልሽ ሆነ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ ባለፈው ቅዳሜ ከሌሊቱ 6 ሰአት ከ45 ደቂቃ ላይ ሚሊኒየም ጎዳና ላይ ወይም ሚካኤል አካባቢ ካሳሁን የተባለ የከተማው ፖሊስ አባል ተገድሏል። ፖሊሱ በቅርቡ ለከተማው ተመድቦ የመጣ ነበር። እርምጃውን የወሰዱት ራሳቸውን የቴፒ ወጣቶች ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ናቸው። ታጣቂዎቹ 5 የፌደራል ፖሊስ አባላትን አግተው ወደ አልታወቀ ስፍራ መውሰዳቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በእስር ላይ የሚገኙ ጓደኞቻቸው ካልተፈቱ ያገቱዋቸውን ፖሊሶች እንደማይለቁ ታጣቂዎቹ አስታውቀዋል። ኢሳት ስለታገቱት ፖሊሶች ከመንግስት በኩል ለማረጋገጥ አልቻለም። ይሁን እንጅ ወጣቶቹ ያገቱዋቸውን ፖሊሶች ፎቶ ግራፍ ለመንግስት ባለስልጣናት መላካቸውን ምንጮች ገልጸዋል። በአካባቢው ያለው ውጥረት እንዳለ ቢሆንም፣ መንግስት ነዋሪው ህዝብ ለታጣቂዎቹ ድጋፍ ይሰጣል በሚል ፖሊስ ህዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ወከባ ቀጥሎበታል። የፖሊስን ጫና በመፍራት በርካታ ወጣቶች እየተሰደዱ ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በከተማዋ ሁለት የኢህአዴግ ካድሬዎችና 1 የፖሊስ አባል ሲገደሉ፣ ፖሊሶች ደግሞ አንድ ሰላማዊ ሰው ገድለዋል።










No comments:

Post a Comment