Monday, October 12, 2015

ተመስገን ደሳለኝ በግፍ ከታሰረ አንድ አመት ሞላው!

temesgen desalegnፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች ባሉበት ሁሉ የጀግና ማደሪያው እስር ቤት ነው። ተመስገን ደሳለኝም የአዕምሮው የበላይነት በቀሰቀሰው ፍርሀት ሳቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስትነት በተሰየመው ሽፍታ ቡድን በግፍ ከታሰረ ይሄው አንድ አመት ሞላው። በመሰረቱ የወያኔ ፖለቲካ የጀግኖች የአዕምሮ የበላይነት የቀሰቀሰው ፍርሀትና ጥላቻ ነው። በመንግስትነት የተሰየሙት እነዚህ ሽፍቶች የአዕምሮ የበላይነት ያለውን ሰው ሁሉ መታሰቢያው ከምድር እንዲጠፋና በዓለም እንዳይኖር በማድረግ ድምፅ ያልነበረው ህዝብ ድምጹ እንዲጠፋ በማድረግ ከብርሃን ወደ ጨለማ ይመልሱታል። ለወያኔዎች ፖለቲካ ማለት ከተቻለ ሁሉን ወደ ዞምቢነት መቀየር፤ካልተቻለ ደግሞ አሳዶ ማሳደድ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የእድገት ተስፋቸውን ያቆራኙት የአዕምሮ የበላይነት ካላቸው ሰዎች ውድቀት ጋር ነውና! ስለ ተመስገን ደሳለኝ ስጽፍ ውዬ ስጽፍ ባድር ተመስገንን በሚገባው መጠን የገለጽሁት መስሎ አይሰማኝም። ተመስገንን ሳስበው ሁልጊዜ አስቀድሞ ወደ ህሊናየ የመሚጣው ግን እንደ ሰው ተፈጥሮ፣ እንደ ሰው ማሰብና እንደ ሰው መኖር ያልተሳነው የዘመናችን ጀግና መሆኑ፤በቁሳዊ አለም ውስጥ እየኖረ በጎ ሰውነቱ ግን ሞልቶ የተትረፈረፈ አይበገሬና ቆስቋሽ ብዕረኛቱ ነው
። እንደ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ ተሜ ለአገሩ የሚጠበቅበትን በማድረጉና ለህሊናው ተገዢ በመሆኑ ያልተደሰቱበት ዞምቢዎቹ ወያኔዎች በግፍ ዘብጥያ አውርደውት ሰቆቃ እየፈጸሙበት የጭካኔያቸው ማርኪያ ማድረጋቸው ሳይበቃ፤ እነሱ በየእለቱ በሚፈጽሙበት ጭካኔ እየተደሰቱ በፍቅር የሚሳሱለት አሮጌ እናቱ ግን በወር አንዴ እንኳ አይኑን አይተውት የልጅ ናፍቆታቸውን እንዳይወጡ አርቀው ማሰራቸው ሳያንስ በደካማ ጉልበታቸው ክህመም ጋር እየታገሉ የልጅ ነገር ሆኖባቸው በታሰረበት የዝዋይ እስር ቤት ሊጠይቁት ሲሄዱ እንኳ እንዳይጠይቁት በመከልክል ሁለት ትውልድ ሰዎችን የደም እንባ እያስለቀሱ ይገኛሉ። ተመስገን ደሳለኝን በቅርብ የማውቀው ወንድሜ ነው፤ እንደ ጽሁፉ አንባቢም አብሮት እንደሰራም ሰው የማደንቀው ጎልማሳ ነው። ተሜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን አሰልፎ «ተራሮችን በነፍጥ እንዳንቀጠቀጠ» የሚደሰኩረውን የወያኔ ቡድን ብቻውን በብዕሩ ያንቀጠቀጠ የዘመናችን ትንታግ ጋዜጠኛ ነው። ተመስገን ደሳለኝ ከምርጫ 97 በኋላ በተፈጠረው የለውጥ ስሜት መጨናገፍ ሳቢያ «ተስፋ ቆርጦ አንድ ላይ ከመቆም፡ ይሻላል በተስፋ ሲጓዙ መክረም» የሚል መንፈስ በሰላማዊ ትግሉ ጎራ እንዲያንሰራራ ታላቅ ስራ የሰራ የህዝብ ልጅ ነው ብዬ አምናለሁ። ተመስገን ደሳላኝ ዘርፈ ብዙ ስብዕና የተላበሰ የቀለም ቀንዲል ነው። ተመስገንን በወዳጅነት ለመጎዳኘት ለቀረበው ሰው፡ እሱ ግንኙነቱን ወደ ወንድማዊ/ እህታዊ መተሳሰር ለውጦት ያገኘዋል። እኔ ግን ከተሜ ወንድማዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊና ሞያዊ በረከትም የተቋደስሁ ሰው ነኝ። ይህንንም እሱ ያሳትማት በነበረች መጽሄት ለመጀመሪያ ጊዜ ባሳተምሁት ጽሁፌ ገልጨዋለሁ። ተሜን አንድ ሰው አዲሳባ ለሆነ ጉዳይ ማግኘት ፈልጎ ለቀጠረውም ሆነ በእንግድነት ሊጎበኝ ወጣ ባለባቸው ያገራችን ክፍሎች ሁሉ፤ በእግድነት የሚያስተናግደውን ሰው እንግዳ ያደርገውና ራሱን እንግዳ ተቀባይ አድርጎ የሚያስተናግድ ሰው ነው። ከዚህም አልፎ ተመስገን፣ ሌሎች ጓደኞቹም እንደሚመሰክሩለት፣ እጁን ዘርሮ የማይታክትና የማይነጥፍ ምንጭ ነው። ተመስገን ከዘመን ተጋሪዎቹ አልፎ በመሄድ፣ በተባ ብዕሩ፣ ባዲስ አቀራረብ፣ የፖለቲካና የሲቪል ነጻነት ሐሳቦችን ለወገኖቹ ኢትዮጵያውያን ለማሳወቅ የተጋ፣ ሌት ተቀን ታግሎ ያገሩ ልጆች የመንፈስ ግዛታቸውን ለማስፋት የጣረ ምርጥ ሰው ነው። እንደ ተሳለ ካራ በምታበራው ብዕሩ ሀሳብ አፍልቆ የወቅቱን አስገባሪ ቡድን ድብቅ ድርጊት ባደባባይ ለህብረተሰባችን እያጋለጠ ለኋላ ቀር ገዢዎቻችን የእግር እሳት፣ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የንቃተ ህሊና መብራት የሆነ የእናት አገሩ የስለት ልጅ ነው። ለተሜ ፖላቲካ በእውቀት የተሻሉ ሰዎች ህዝብን ለማገልገል ያስተሳሰብና የተግባር ፉክክር የሚያደርጉበት እንጂ ልክበር፣ ልሰር፣ ልግደል፣ ልበድል፣ ባይ ልቦናን ድል ሳያደርግ ዳግማዊ ሚኒልክ ቤተ መንግስትን መቆጣጠር ስላልሆነ፤ የመንግስትነት ጠባይ ሳያሳይ 24 ዓመታትን አገባድዶ 25ተኛውን የግፍ ዘመን ለማክበር ተፍ ተፍ እያለ ያለውን ቡድንም ፣ «መለስ ሆይ፡―ክልምኖም ይስምዑኒ» እያለ አደብ እንዲገዛ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። ፍርሀትና ጥላቻ ሆደ ጠባብ እንዲሆን ያደረገውን ይህን በመንግስትነት የተሰየመ የባሪያ አሳዳሪዎች ቡድን፤ ከሩብ ክፍለ ዘመን የመንግስትነት ቆይታ በኋላም በዕውቀትና በጥበብ ከፍ ያለ አእምሮ ያላቸውን ሰዎች እያሳደደ፣ ከሰውነት ጠባይ ወጥተው ሲሰሩ ያገኛቸው ይመስል የሃጢያት ክስ እየደረደረ፣ እልቆ መሳፍርት ምርጦችን አሳጥቶ ዛሬ ራቁታችንን አቁሞን ይገኛል። የተሜ የሀጢያት ክስ ሲገለጥ እንደ ሌሎች የህሊና እስረኞች ሁሉ «ጥፋቶቹ» ተመሳሳዮች ናቸው። ከጥፋቶቹ መካከል እንደ ገዢው ቡድን የተወለዱበትን አካባቢና የተዛመዳቸውን ብቻ አገሬና ወገኖቼ ብሎ አለመለየቱ፤ በሰፊው አስተያየት ገምቶ የሰውን ዘር ሁሉ እንደ ወንድም ባለማስተዋል ወገኔ ዘሬ ባለማለቱ፤ልቦናውንና አእምሮውን በጥበብና በስልጣኔ ያለሰለሰ ሰው ሆኖ መገኘቱ፤ አገሩን በጠባቡ ክልላዊ ጠረፍ ወስኖ ሰው ያለበትንና ተሰርቶ የሚታደርበትን ሁሉ አገሬ ነው በማለቱ የተነሳ እና ሌሎች ዝባዝንኪ ሰበቦችም ተደርድረውበታል። እውነቱ ግን ተመስገን፡ ሁሌ በሚጽፋቸው ጽሁፎቹ ለጆሮ የሚቀርቡ ጉዳዮችን እያነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ከገዢዎቹ ተላቆ በህሊናው መሪነት የገዛ ራሱ አስተዳዳሪ ወደሚሆንበት ምድረ ርስት ለማድረስ የታተረ ጀግና ነው። ይህ ጠቢብ ባሁኑ ወቅት ያለው አገዛዝ እጅግ አጥቦት ካለው የህይወት መስክ ኢትዮጵያውያን ወጥተው፡ እውቀት ከሚያስገኘው የነጻነት ሰፊ ሜዳ ገብተው እንደልባቸው ተዝናንተው እንዲራመዱ፡ ብርቱ የሆነ የሰለጠነ ትግል እንደሚያስፈልግ በመምከሩ እንደ ጨካኝ ነፍሰ ገዳይ በጨለማ እስር ሆኖ በተፈጸመበት ግፍ ምክንያት ጀርባው አብጦ፤ግራ ጆሮው ሙሉ ለሙሉ መስማት አቁሞ ስለእኛ እጅግ ብዙ መስዕዋትነትን እየከፈለ ይገኛል። በዘመነኞች ተዓብዮ እንዲህ የህዝብ ልጆች ስቃይና ግፍ ሞልቶ ሲፈስ ሰሚ ቢጠፋም መጪው ትውልድ ይፋረድበት ዘንድ የነተሜን ስቃይና ግፍ የኢትዮጵያ አፈርና ቅጠል ሰምቶ በታሪክ መዝገብነት ቀርጾ አስቀምጦታል። ተሜ የዘመናችን አቤ ጉበኛ ነው። በችሎታው ስለሚመካ፣ ስለሚጽፈው ጽሁፍ ብዙ አይጨነቅም፤ ለሱ እንደማንኛውም ነገር የሚሰራው ስራ ለህትመት ሲበቃ ብዙ አንባቢን ያነጋግራል። ተመስገን፡ የብእር ትሩፋትን፡ እንደ ቅኔ መምህሩ ስብረ አብ፡ ሁለት ቤት ቅኔ፡ እንዲነበብ አድርጎ ያስተዋወቀ ታላቅ ብእረኛ ነው። ተሜ በteam work የሚያምን፣ ፈገግታ የማይለየው፣ ሞያውን የሚያከብር፣ በስሩ አብረውት የሚሰሩትን የሞያ ጓደኞቹን ችሎታ የማይጋፋ፡ይልቁንም የሚያከብር፣አድናቆትና ምስጋናውን ያላንዳች ስስት የሚቸር፣ መታበይና ትክሻን መስበቅ የማያውቅ፣ መስሪያ ቢሮውና መኖሪያ ቤቱ ሳይቀር ለሁሉም ክፍት የሆኑ፣ በህትመት መገናኛ ብዙሀን አዲስ አሰራር ፈር የቀደደ የህዝብ ድምጽ ነው። ይህንን አንደበት እስር ቤት ቆልፎ እንዲሰቃይ ማድረግ የሚያም ትልቅ አገራዊ ጉዳት ቢሆንም ቅሉ፤ የእርሱ መታሰርና መሰቃየት ለሀገሩ የሚገባውን ሰርቶ ነውና እኛ ያልታሰርነውና ከእስር ያመለጥነው እርም አንልም! ተሜ ሆይ ተመልሰን የምንገናኝበት ቀን ግን ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። እስከዚያው ባለህበት ሰላም ሁን! - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47344#sthash.usCeONM5.dpuf

No comments:

Post a Comment