Saturday, October 31, 2015

ሌ/ኮ መንግስቱ ኃይለማሪያም በ‹‹ኑዛዜያቸው›› በርካቶችን ለኢትዮጵያ ውድቀት ተጠያቂ አደረጉ -

 ‹‹ስለ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ መናገር ቀርቶ ስሙንም ማንሳት በጣም ያሳፍረኛል›› • ‹‹ጀኔራል መርዕድ ንጉሴ የውጊያ መሰናዶዎቼን ለጠላት አሳልገው ሰጥተዋል • የሀገር ደህንነት መስሪያ ቤት ፈላሻዎችን በህገ ወጥ መንገድ ሲያስተላልፍ ነበር • ፕሮፌሰር መስፍንና ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ ተጠያቂ ከተደረጉት ታላላቅ ሰዎች መካከል ናቸው • እነ ፍስሃ ደስታ፣ እነ ኮሎኔል ተስፋዬ፣ እነ ጀኔራል ስዩም ሊያስገድሏቸው እንደነበር አውስተዋል     ኢትዮ-ምህዳር ጥቅምት 20/2008 (አ.አ)፡- የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ‹‹ኑዛዜ›› ብለው ለህዝብ እንዲደርስላቸው በካሴት ካሰራጩት ድምፅ ተዘጋጅቶ ለንባብ በበቃ ‹‹ከኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም አንደበት›› የተሰኘ መፅሃፍ በርካታ ምሁራንንና የቀድሞ ባልደረቦቻውን በኢትዮጵያ ላይ በማሴርና ለውድቀቱም ተጠያቂ ናቸው ማለታቸውን አስነብቧል፡፡ ኮ/ል መንግስቱ አብዛኛውን ይሸረብባቸው የነበረውን ሴራ የተረዱት ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ እንደሆነ በቁጭት ተናግረዋል፡፡ በተለይ በመፈንቅለ መንግስቱ ወቅት የተገደሉት ጀኔራሎች ለውድቀቱ ዋነኛዎቹ ተጠያቂ ተደርገዋል፡፡ ከጀኔራሎቹ መካከል እነ መርዕድ ንጉሴ፣ ፋንታ በላይ በስፋት የተጠቀሱ ሲሆን የጀኔራል መርዕድ ንጉሴ ሁለተኛዋ ሚስት ለሻዕቢያ ትሰራ እንደነበር ተግልፆአል፡፡ በተጨማሪም ጀነራል መርዕድ ንጉሴ የውጊያ ስትራቴጅ መሰናዶዎችን ለጠላት አሰልፎ ሰጥቷል ሲሉ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡
በመፅሃፉ እነ ፍስሃ ደስታ፣ እነ ኮሎኔል ተስፋዬ፣ እነ ጁኔራል ስዩም ኮ/ል መንግስቱን ጦርነት ውስጥ በማጋፈጥ በህይወታቸው ላይ አደጋ እንዲደርስባቸው ለማድረግ ሙከራ ማድረጋቸው ገልፀው በጓዶቻቸው ሴራ ይሸረብባቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በተቋም ደረጃም የኢትዮጵያ ሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ፈላሻዎችን ወደ እስራኤል በመላክ ሴራ ውስጥ መሳተፉን፣ በዚህ ንግድም በርካታ ግለሰቦች ትርፋማ መሆናቸውን በቁጭት ገልፀዋል፡፡ ኮሎኔሉ በስፋት ከተቿቸው ግለሰቦች መካከል ዳዊት ወልደጊወርጊስ ግንባር ቀደሙ ሲሆኑ ‹‹ስለ ዳዊት ገ/ጊዮርጊስ መናገር ቀርቶ ስሙንም ማንሳት በጣም ያሳፍረኛል፡፡›› ብለዋል፡፡ ኮ/ል መንግስቱ በተለያዩ የጦር አውድማዎች የተደረጉት ፍልሚያዎችና የ17 አመቱ ጉዞ ለምን እንደተሰናከለ፣ መንግስታቸው ለምን ችግር ውስጥ እንደገባ፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ሴራዎችን፣ ኢትዮጵያውያን ሰሩት ያሉትን ስህተት በስፋት ዘርዝረዋል፡፡ በተጨማሪም ለምን እንደወጡና እንዳይመለሱ የተሸረበባቻን ሴራ፣ ቤተሰባቸው የገጠመውን ችግርና ለወደፊት መፍትሄ ያሉትንም በመጽሃፉ ሰፍሯል፡፡ ኮ/ል መንግስቱ ከሀገር ከወጡ በኋላ በኑዛዜ መልክ ለህዝብ እንዲደርስ በሲዲ ከቀረፁፁትን ድምፅ በሶስት ግለሰቦች የተዘጋጀው ‹‹ከኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም አንደበት›› የተሰኘው መፅሃፍ ለንባብ የበቃው ከሳምንት በፊት ነው፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47873#sthash.zGPkjc2g.dpuf

No comments:

Post a Comment