Monday, October 12, 2015

በፍቼ ከተማ የኦሮምያ ፖሊስና የመከላከያ አባላት ተጋጩ

ባለፈው ቅዳሜ በተነሳው ግጭት ከፖሊስና ከመከላከያ አንዳንድ ወታደሮች ቆስለዋል። የግጭቱ መንስኤ ሁለት የመከላከያ ፖሊስ አባላት በፖሊሶች መደብደባቸው ነው። ከዚህ ቀደም አንድ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ፍቼ አካባቢ ሰፍሮ የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት አባል ከገደለው በሁዋላ፣ በመከላከያና በፖሊስ መካከል ለወራት የዘለቀ ቁርሾ እንዲፈጠር አድርጓል። ባለፈው ቅዳሜ ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከተማው እየተዝናኑ በነበረበት ወቅት፣ ፖሊሶቹ የደበደቡዋቸው ሲሆን፣ የመከላከያ አባላለቱ መደብደባቸውን ካፕም ለሚገኘው አዛዥ ሲደውሉ፣ አንድ ወታደራዊ አዛዥ በአንድ ኦራል መኪና የተጫኑ ወታደሮችን አስከትሎ ከተማ ከገባ በሁዋላ፣ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶችን በዱላ ደብድበዋል። ፖሊሶቹ በወሰዱት የአጸፋ ተኩስ አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባልና አንድ የልዩ ሃይል ፖሊስ አባል ቆስለዋል። ሌሎችም ፖሊሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ወታደራዊ አዛዦች ወታደሮችን ልከው ከአስደበደቡዋቸው በሁዋላ መልሰው ገላጋይ በመሆን መግባታቸውን የሚገልጹት የአይን እማኞች፣ በአካባቢው አሁንም ድረስ ውጥረት መኖሩን ገልጸዋል። ትናንት አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ከአዲስ አበባ ፍቼ ወደ ሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ በማምራት ከሰራዊት አባላት ጋር ተነጋግሯል። በከተማው ውስጥ አምሽቶ መጓዥ የተከለከለ ሲሆን፣ ሲያመሹ የተገኙ ወጣቶች ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። በወታደሮችና በኦሮምያ ፖሊሶች መካከል የተፈጠረው ግጭት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ በቀላሉ ይበርዳል ብለው እንደማያምኑ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን አስተዳደር ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሰካም።









No comments:

Post a Comment