በቅርቡ ወደሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል ለሁለተኛ ሳምንት ከባድ ውጊያ ኣያካሄደ ኣንደሚገኝ የሶማሊያ ወታደራዊ ባለስልጣናት ትናንት ገለጹ። ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥሎ የሚገኘው ግጭት ልዩ ስሙ አልዩ ዲዮ በተባለ ደቡባዊ ምዕራብ የሶማሊያ አካባቢ እየተካሄደ እንደሚገኝ እነዚሁ ወታደራዊ ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ በአካባቢው እየተካሄደ ባለው ውጊያ፣ የኢትዮጵያ አየር ሃይልና የሶማልያ ብሄራዊ ጦር እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በአካባቢው ኣየተካሄደ ያለውን ግጭት በመሸሽም በርካታ ነዋሪዎች መሰደዳቸውን እና ውጊያው ከባድ መሆኑን የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአልሻባብ ታጣቂ ቡድን ላይ ከባድ ውድመት መድረሱን ቢገልጽም፣ በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ስለደረሰ ጥቃት የሰጠው መረጃ የለም። በምዕራባዊ ሶማሊያ በአልሻባብ ጠንካራ ይዞታዎች ላይ የሚካሄደውን ውጊያ ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ ተጨማሪ 1ሺ ወታደር ወደስፍራው መላኳ ይታወሳል። ይኸው ባለፈው ወር ወደ ሶማሊያ እንዲሰማራ የተደረገው ጦር ሰራዊት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከባድ ውጊያ ኣያካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል ስር አሰማርታ ብትገኝም በአልሻባብ ታጣቂ ሃይል ላይ በተናጥል ወታደራዊ እርምጃን እየወሰደች ትገኛለች። ይህ በእንዲህ እንዳለም የአፍሪካ የሰላም አስክባሪ ሃይል ሁለት የአልሻባብ ኮማንደሮችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ አስታውቋል። ሁለቱ የታጣቂ ሃይሉ ኮማንደሮች በቅርቡ በሰላም አስከባሪ ሃይሉ ላይ የተፈጸመን ጥቃት እንዳቀነበበሩ የሰላም ልዑክ ሃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ ኒውስ 24 የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል። ከአንድ ወር በፊት ታጣቂ ሃይሉ በሰላም ልዑኩ ላይ ፈጽሞት በነበረው ጥቃት 13 የዩጋንዳ ወታደሮች መገደላቸው ይታወሳል። ከተለያዩ ሃገራት የተውጣቱ ወደ 20 ሺ የሚጠጉ የሰላም አስከባሪዎች በሶማሊያ ተሰማርተው ቢገኙም ታጣቂ ሃይሉ አሁንም ድረስ የሶማሊያ የጸጥታ ስጋት ሆኖ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment