Monday, October 12, 2015

በሶማሊያ የተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የሰላም አስከባሪዎች በኬንያ ሆስፒታል ተረስተዋል (Dawit Solomon) በሶማሊያ የተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የሰላም አስከባሪዎች በኬንያ ሆስፒታል ተረስተዋል (Dawit Solomon)

12108995_896253477126254_1678758653615688345_nአስታማሚ ባለማግኘታቸው ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል
--115 ዶላር ብቻ ሲከፈላቸው መቆየታቸውንም ይናገራሉ
(በዛብህና በየነ እውነተኛ ስማቸው ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ተለውጧል) ሁለቱም በሐያዎቹ አጋማሽ የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፤አገራቸውን በወታደርነት ለማገልገል ቅጥር የፈጸሙት ከዛሬ ስድስትና አራት አመታት በፊት ነው፡፡የትውልድ አካባቢያቸው የነበሩትን ዲላና ሆሳህናን ለቅቀው በተለያዩ ግዳጆች አገራቸውን እንደተመኙት ሲያገለግሉ ቆይተው የዛሬ አንድ አመት አካባቢ የተባበሩት መንግስታትን የሰላም አስከባሪ ሐይል በመቀላቀል በሽብርተኛው አልሻባብ ወደ ምትታመሰው ሶማሊያ አቅንተዋል፡፡
በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተግባራቸውን እየፈጸሙ በነበረበት አንድ መጥፎ ቀን በዛብህ በተተኮሰበት ሁለት ጥይት ሆዱ አካባቢ ተመትቷል፡፡ራሱን በህይወት ያገኘው ግን በሌላኛዋ ጎረቤት አገር ኬንያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡በየነ የተቀበሩ ፈንጂዎችን የመፈተሸ ግዳጅ ተሰጥቶት የያዘው የፈንጂ መጠቆሚያ መሳሪያና የተቀበረው ፈንጂ በመሳሳባቸው በተፈጠረ ፍንዳታ ሁለት እግሩንና የአንድ እጁን አንድ ጣት ለማጣት ተገድዷል የአንድ አይኑ የማየት አቅምም ክፉኛ መጎዳቱን ይናገራል፡፡
በዛብህና በየነ አደጋውን ካስተናገዱ በኋላ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲተኙ በመደረጋቸው ለመተዋወቅ በቅተዋል፡፡በየነ የተሰጠው ዊልቼይር ላይ ተቀምጦ በዛብህ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበለት ልጎበኛቸው በሄድኩበት ሰዓት አግኝቻቸዋለሁ፡፡ሰው የተራቡት ሁለቱ የአገሬ ልጆች የቅርብ የቤተሰቡን አካል እንዳገኘ ሰው እቅፍ አድርገውኝ ስመውኛል፡፡
‹‹የቋንቋ ችግር አለብን፣ካለንበት ሆስፒታል ሰዎች ጋር መግባባት አልቻልንም››፡፡በየነ እንባ አቅርሮ ይናገራል ‹‹እርሱን አጠገቤ ማግኘት ባልችል ኖሮ እንዴት አድርጌ ሁኔታውን እንደምለምደው አላውቅም፡፡ፈንጂው በፈነዳበት ወቅት አንድ እግሬ ተቆርጦ ሲቃጠል ተመልክቼው ነበር፡፡ አንደኛው እግሬ ቢቆስልም ሊድን ይችል እንደነበር አምናለሁ፡፡ነገር ግን እዚህ ከመጣሁ በኋላ ቆረጡት፡፡ለምን እንደቆረጡት እንኳን እስካሁን ለእኔ ግልጽ አይደለም››ብሏል ፡፡
ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ በኋላ ዲላና ሆሳህና ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ለመገናኘት ቢያስቡም በየነ በፈንጂው አደጋ ወቅት ተንቀሳቃሽ ስልኩ በመጥፋቷና የበዛብህ ደግሞ ለብልሽት በመጋለጧ ምንም ማድረግ ሳይችሉ መቅረታቸውን በሐዘን ተውጠው ይናገራሉ፡፡
‹‹የተባበሩት መንግስታትን ተልእኮ ተቀብላችሁ የዘመታችሁ በመሆናችሁ እንዴት እንዲህ ያሉ ጥቃቅን ነገሮችን እንኳን ሊያሟሉላችሁ አይችሉም ?›› በአግራሞት ተሞልቼ የወረወርኩት ጥያቄ ነበር፡፡
‹‹ወደ ሆስፒታሉ እንደመጣን አንድ ኮሎኔል የእኛን ሁኔታ እንደሚከታተል ተነግሮን የነበረ ቢሆንም ሰውዬው የሚመጣው በጣም እየዘገየ ነው፡፡የሚያደርግልን ምንም የተለየ ነገር የለም፣ እነርሱ ከህክምናችን ውጪ የሚያደርጉልን ምንም የለም››፡፡ለጥያቄዬ የሰጡኝ ምላሽ ነበር፡፡
ከሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች አጠገብ አንድ እግሩን በአደጋ ያጣ ጎልማሳ ኬንያዊ ተኝቷል፡፡በዛብህ ጣቱን ወደ ኬንያዊው እየቀሰረ ‹‹እባክህ ስለእኛ ሆነህ ይህንን ኬንያዊ አመስግንልን ፤ የእርሱ ቤተሰቦች ሊጠይቁት ሲመጡ አትክልት፣ምግብና ወተት ሁልግዜም ያመጡልናል››አለኝ፡፡
ወታደሮቹ በሆስፒታሉ ከሚያገኙት የህክምና፣የምግብና የአልጋ አገልግሎት ውጪ ምንም አይነት እርዳታ አያገኙም፡፡በየነ ሁለት እግሮቹን በማጣቱ መጸዳጃ ቤት የሚወስደው፣አልጋው ላይ የሚያወጣውና የሚያወርደው ረዳት ያስፈልገዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ይህንን አገልግሎት እየሰጠው የሚገኘው በሁለት የሆዱ ክፍሎች ላይ ቀዶ ጥገና ያደረገውና ቁስሉ ያልደረቀለት በዛብህ ነው፡፡
‹‹በየነ በጣም ሰው ያስፈልገዋል፡፡እኔ ደግሞ እንደምታየኝ ቀዶ ጥገና ያደረግኩት በቅርቡ ነው፡፡ግን እርሱ ከእኔ በሚብስ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኝና ከእኔ ውጪ ሊረዳው የሚችል ሰው ባለመኖሩ እያመመኝም ቢሆን እረዳዋለሁ››ብሎኛል፡፡
በየነ አሁን ከሁሉም በላይ አገሩ መግባትን ናፍቋል፡፡‹‹በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማልችል ወደ አገሬ እንዲወስዱኝ እፈልጋለሁ ቢያንስ ቤተሰቦቼ አጠገቤ ሆነው ሊያስታምሙኝ ይችላሉ››ይላል፡፡
ሁለቱ ወታደሮች በሶማሊያ ቆይታቸው በወር 115 የአሜሪካ ዶላር አበል እየተባለ ሲከፈላቸው መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡በየነ በፈንጂው ወዲያውኑ በተቆረጠው እግሩ ባጠለቀው ሱሪ ኪስ ውስጥ የተቀበለውን ዶላር አስቀምጦ እንደነበር በማስታወስ ፈገግ ይላል፡፡
ወታደሮቹ ምንም እንኳን ስለሚገኙበት ሆስፒታል የህክምና አሰጣጥ ባያማርሩም መረሳታቸው ግን ያበሳጫቸዋል፡፡ከአገራችን አልፈን ለአህጉሪቱ ችግር መፍትሄ ለመስጠት በተሰማራንበት ግዳጅ ጉዳት አስተናግደን የምንፈልጋቸውን ጥቃቅን ነገሮች ሊያሟልልን የሚችል ረዳት ከአጠገባችን ማጣታችን ቅስማችንን ሰብሮታል ይላሉ፡፡
በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ግዳጅን በመወጣት ላይ የሚገኙ 5000 ያህል ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡በኬንያ በተለይም በዋና ከተማይቱ ናይሮቢ የምትገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጉዳተኞቹ ወደሚገኙበት ሆስፒታል በማምራት እንድትጎበኟቸው ትጠየቃላችሁ፡፡
-----------

No comments:

Post a Comment