ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ተሸላሚ ሆነ
በሽብርተኝነት ተከስሶ 18 አመት የተፈረደበትና በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት (PEN Canada’s One Humanity Award) ሽልማት ተሸላሚ መሆኑን ፔን ካናዳ ይፋ አድርጓል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በፈረንጆቹ ግንቦት 2012 የባርባር ጎልድ ስሚዝ ሽልማት እንዲሁም በሰኔ 2014 የጎልደን ፔን ሽልማትን ተሸላሚ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በካናዳ ቶሮንቶ እየተደረገ በሚገኘው 36ኛው ዓለም አቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲባል የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት ሽልማትን ተሸልሟል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 የአረብ አብዮትን ተከትሎ መንግስት ለውጥ የማያደርግ ከሆነ ተመሳሳይ ህዝባዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያም ሊከሰት ይችላል የሚል አስተያየቱን ማንጸባረቁን ተከትሎ ለእስር የተዳረገውና በፀረ ሽብር ህጉ ተከስሶ 18 አመት የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በበርካታ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ዓለማቀፍ መብቱን መጠቀሙን በማስታወስ እስክንድር የህሊና እስረኛ እንደሆነ በመግለፅ ከእስር እንዲለቀቅ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ከእስር እንዲለቅ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በእስር ቤቱ ከሚደረግበት ከፍተኛ ቁጥጥርና ጫና ባሻገር ከቤተሰብ ውጭ እንዳይጠየቅ ተከልክሎ ይገኛል፡፡
No comments:
Post a Comment