አይ.ኤስ.አይ.ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለመቃወም መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም በጠራው ሰልፍ ሰበብ ታስረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እነ ማቲያስ መኩሪያ በፍርድ ቤት እየተጉላሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ጥቅምት 8/2008 ዓ.ም በመናገሻ ፍርድ ቤት የቀረቡት በእነ ማትያስ የክስ መዝገብ የሚገኙት አራቱ ተከሳሾች ክረምቱን በተረኛ ችሎት ይቀርቡበት ከነበረው አራዳ ፍርድ ቤት ተዛውረው እንደገና ወደቀደመው ችሎት መናገሻ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡
ተከሳሾች እስካሁን ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ ወቅት ‹‹የቪዲዮ ማስረጃም አለን›› በማለቱ ተከሳሾቹ ‹‹ቪዲዮው ይቅረብልን፡፡ የቪዲዮ ማስረጃው ለእኛ የመከላከያ ምስክርነት ይጠቅመናል›› ብለው በጠየቁት መሰረት ቪዲዮው ይቅረብ አይቅረብ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለወራ ተከታታይ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፤ እስካሁን ግን ብይኑ አልተሰጣቸውም፡፡
በዚህም ተከሳሾቹ ከታሰሩ ስድስት ወራት እንደሞላቸው በማውሳት ቤተሰቦቻቸው ለእንግልት፣ እነሱም ለእስር መዳረጋቸው አግባብ አለመሆኑን ለፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡ በዚህም አፋጣኝ ፍትህ እንደሚሹ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን አሁንም በዚሁ በቪዲዮ ማስረጃው ላይ ብይን ለመስጠት በሚል ለጥቅምት 15/2008 ዓ.ም ሌላ ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለዛሬው ቀጠሮ የሰጠበት ምክንያት ‹‹መዝገቡ ከእጄ ወጥቶ ስለነበር አልመረመርኩትም›› የሚል ሆኗል፡፡
በእነ ማቲያስ መኩሪያ መዝገብ የተከሰሱት 1ኛ ማቲያስ መኩሪያ፣ 2ኛ መሳይ ደጉሰው፣ 3ኛ ብሌን መስፍን፣ 4ኛ ተዋቸው ዳምጤ ሲሆኑ ከመሳይ ደጉሰው ውጭ ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment