Friday, October 16, 2015

አቡነ መቃሪዮስ – የዘመናችን አቡነ ጴጥሮስ

Abune Mekariwosእኛ ኢትዮጵያውያን በቁም መመሰጋገን ወይንም መወዳደስ ብዙውን ጊዜ ያቅተናል – ምክንያቱን በውል አላውቅም፡፡ ምናልባት ውዳሤ ከንቱ እንዳይመስልብን ከመፍራት አኳያ ይመስለኛል ሰውን በሕይወት ዘመኑ – እንደፈረንጆቹ – የማወደስ ባህላችን እስከዚህም የሆነው – ይህን የይሉኝታ እሥረኛ የሆነ ልማዳችንን ቅድስና ለመስጠት ታዲያ “ሆድ ያመስግን”፤ “ሙያ በልብ” የመሳሰሉ አባባሎች አሉን፡፡ ምናልባት “አመስጋኝ አማሳኝ” እንደሚባለው ተመስጋኙ የልብ ልብ እንዳይሰማውና እንዳይታበይ ታብዮም እንዳይበላሽብን ከመሥጋት አንጻርም ሊሆን ከቻለ የማናመሰግነው ይህንንም አላውቅም፡፡ ግን አንድ ሰው ከሞተ በኋላ የምሥጋናና የሙገሣ ዶፍ ከማዝነብ – ላያየው – በቁም እያለም አክብሮትንና ፍቅርን መግለጽ መልካም አጋጣሚ ይመስለኛል፡፡ ይህን በጎ ምግባር ብንለምደው አንድ ሰው ከዚህች ምድር ሲሰናበት ወይም ከተሰናበተ በኋላ በውዳሤ ለማንበሽበሽም ሆነ በዕንባ ጎርፍ ለመዘከር ከመጣደፍ የተሻለ አግባብነትና ጠቀሜታ አለው፡፡

አባ መቃሪዮስን በሚዲያ በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ ትናንት ማታ በኢሣት ቴሌቪዥን ከሎንዶኑ ጀግናችን ከወንድማገኝ ጋሹ ጋ ያደረጉትን መሳጭ ቃለ መጠይቅ አፌን ከፍቼ ስከታተል በአነጋገራቸው ዕንባየ ተንቆረዘዘ፡፡ በነገረ ሁኔታቸው ደግሞ ቁርጥ አቡነ ጴጥሮስን ሆኑብኝ፤ “ለካንስ ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም” ብዬም ተጽናናሁ፡፡ ከሁሉም ግን የአንደበታቸው ቅላጼ እኚህ አባቴ ከወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንደሆኑ ምልክቶችን ሲሰጠኝ በሕይወት የመቆየትና የሀገሬን መጨረሻ የማየት ተስፋየ ይበልጥ ለመለመ፡፡ ስለሳቸው እርግጡን ለማወቅ ደግሞ ጓጓሁ፡፡ ወያኔ በየዘር ከረጪታችን ገብተን እንድንዳክር ያልቆፈረው ጉድጓድ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጉድጓድ መውጣት እንደብርቅ በሚታይበት የፈተና ወቅት (ዘመነ መንሱት) እኚህ አባቴ የወያኔን ቀመር በጣጥሰው ራቁቱን ማውጣታቸውን ስታዘብ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት ሀገር፣ ኢትዮጳያ ያልተፈጸሙ የብዙ ድንቅ ትንቢቶች ሀገር፣ ኢትዮጵያ ወደፊት የዓለምን ስደተኞች ተቀባይ ሀገር መሆኗን ካለመጠራጠር አመንኩ፡፡ ሳይደግስ የማይጣላው ቸሩ እግዚኣብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ በነገራችን ላይ በርግጥም ሰሜነኛ መሆናቸውን ለማወቅ ለኢሣት ወዲያውኑ ኢሜል በማድረግ – ጥያቄየ መናኛ መሆኑን እየተረዳሁት ቢሆንም – እውነቱን ለመረዳት ሞከርኩ – እነሱም ቅጽበታዊ መልስ ሰጡኝና እውነቱን ዐወቅሁ – ሰሜነኛነታቸውን፤ ምን ዙሪያ ጥምትም አስኬደኝ – ትግሬ ናቸው፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ ስለነበር መልእክቱን ያነበብኩት ወዲያው ተነስቼ ይህችን አጭር ማስታወሻ ጻፍኩ – ወያኔዎች እንቅልፍንም ህልምንም ኑሮንም ከነሱን 25 ዓመታትን ሊደፍኑ ጥቂት ወራት ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡ ለማንኛውም ስንከፋ ብቻ ሣይሆን ስንደሰትም መጻፍ ይኖርብናል ብዬ አስባለሁና ስለ አባቴ ስለ አባ መቃሪዮስ ይህን ጽሑፍ አሰናዳሁ – ላመሰግን፡፡(ስሜታዊ ደስታየን ለመግለጽ ያህል እንጂ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላንዱ የግዴታ ለሌላው የውዴታ እንደሆነ ቆጥሬ አለመሆኔን ወቀሳ ለሚሰነዝሩብኝ አንዳንድ ወገኖቼ በትህትና መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡)
አንድ ሰው የዘር፣ የሃማይኖት፣ የቀለም፣ የነገድና የጎሣ ድንበሮችን ጥሶ ሲሄድና ለሁሉም የሰው ዘር ጥብቅና ሲቆም ይህ ሰው በፈረንጅኛው አጠራር enlightened ሆነ እንላለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው በማስሎው ቲየሪ ሲለካ የመጨረሻውን የ self-actualization ደረጃ እንደተጎናጸፈ ይነገርለታል፡፡ ከቡድሂዝም፣ ሂንዱይዝምና ጃይኒዝም እምነቶች አንጻር ካየነው ደግሞ ይህ ዓይነቱ ሰው የዳግም ልደቱን የመማሪያ ዑደት ጨርሶ ወደ ኒርቫና ደረጃ የደረሰና የነፍስ ብፅዓቱን የጨረሰ ማለት ነው – ሰውም ሆኖ ይሁን ዐይጥ ሁለተኛ ወደዚህች ምድር ተመልሶ አይመጣም – የእምነት ጉዳይ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ዓለማችን የምታፈራው በጣም በጥቂቱ ነው፤ በዚህ ረገድ ቀብቃባ/ስስታም ናት፡፡ አብዛኛው ዜጋ ሰውነት ደረጃ ለመድረስ ብዙ የሚቀረው ገና የሀሁ ተማሪ ነው፡፡ በመሠረቱ ዘረኝነትን፣ አድሎኣዊነትን፣ ፍርደ ገምድልነትን፣ ጎሠኝነትን፣ የሀገር ልጅነትን፣ ወንዘኝነትን/ጎጠኝነትን፣ የዝምድና ትስስርን፣ ወዘተ. በጣጥሶ የትክክለኛ ፍትህና የነፃ ኅሊና ባለቤት ለመሆን ብዙ ትግልን ይጠይቃል፡፡ ትግሉም እልህ አስጨራሽና ራስን እስመካድ የሚያደርስ ነው፡፡ ለአብነት አንተ ሥራ አሥኪያጅ በሆንክበት የግልም ይሁን የመንግሥት ድርጅት እኩል የትምህርት ደረጃ ያላቸው ልጅህና ጓደኛው ሥራ ለመቀጠር ቢያመለክቱ ለየትኛው ታዘነብላለህ? በተቀመጠው መሥፈርት በሃቅ አወዳድረህ ትቀጥራለህ ወይንስ እምዬ ማርያም ለበላዔሰብ አደረገች እንደተባለው አንተም ጥላህን ወዳንተው ልጅ ትጥላለህ? ቀልብህ የማይወደውን ተማሪህን ወይም አያድርግብህና ባለጌ ሆነህ ለሆነ ጉዳይ የፈለግሃትን ሴት ተማሪ አለምክንያት ወይም በቀጭን ሰበብ ትጥላለህ/ታሣልፋለህ? … ራሳችንን የምንለካባቸው ብዙና ብዙ የሕይወት ፈተናዎች(temptations)አሉ – እኔ ስላንተ የማውቃቸው አንተም ስለኔ የምታውቃቸው፡፡ አንድ የዐማርኛ ብሂል ላስታውስ፡- “ያንቺ ልጅ የኔን ልጅ መትቶት ከሆነ ምች ይምታው፤ የኔ ልጅ ያንቺን ልጅ መትቶት ከሆነ ግን መቼም፡፡” አለች ይባላል አንዷ ፍርደ ገምድል፡፡ አዎ፣ ፍርድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ የምንለውም ይህን ሁኔታ በሚገባ ይገልጸዋል፡፡
እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ አቡነ ጳውሎስ(አባ ገብረ መድኅን) እነዚህን የሰይጣን ደቀ መዛሙርት ገስጸውና መክረው በመመለስ ኢትዮጵያን ከማጥፋት እንዲመለሱ ማድረግ ሲችሉ እሳቸው ራሳቸው ከክርስቶስ ቃል ወጥተው የጥፋት መንገድን ይከተሉ ነበርን? “ግም ልግም አብረህ አዝግም” እንዲሉ ምትካቸው አቡነ ናትናኤልስ (ስማቸውን ልክ እሆን? ማትያስ ነው ናትናኤል?) አባ ጳውሎስ በጀመሩት መንገድ ይጓዙ ነበርን? በነገራችን ላይ ስለሀገርህ ግድ ሳይኖርህ ሲቀር የባለሥልጣኖቹን ስም ሳይቀር አታውቅም፤ ለማወቅም አትጓጓም፡፡ የሚገርም ነገር ነው፡፡ ከምህዋር ትወጣና በገዛ ሀገርህ ባዕድ ትሆናለህ፤ የባዕድነት ስሜት ይጠናወትህና የትነትህ ጠፍቶህ እንደመፃተኛ ትሆናለህ – ከሰማይ እንደወረድህ ወይም ከመሬት እንደፈለቅህ ግዑዝ ነገር፡፡ ሲሰቀልና ሲወርድ የምትንቆራጠጥለት ባንዴራ የለህ፤ ብሔራዊ መዝሙር የለህ፤ ብሔራዊ ስሜት የለህ፤ የኔም ብለህ የምትቀበለውና በስስት የምትወደው ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ኃይል የለህ፤ በስሜት የምትናበበውና እንዳስፈላጊነቱም የምትተባበረው የደኅንነትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም የፍትህ አካል የለህ … በገዛ ሀገርህ የማንምነት ስሜት ሳይኖርህ ለመኖር ያህል ብቻ ምድራዊ ኮንትራትህ አልቆ ወደማይቀረው የወዲያኛው ዓለም እስክትጠራ ትንጠራወዛለህ፤ ጠግበህ ይርብሃል፤ ለብሰህ ይበርድሃል፤ በወገንህ መካከል እያለህ ሰው ይናፍቅሃል … ርሁቅ ብዕሲ፡፡ የኛስ ከሁሉም ባሰ!! አመክሮም የለንም እንዴ?
እኚህ አባታችን እንዲህ በሀገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ እየተብከነከኑ ሕዝብን ለነፃነቱ እንዲነሣ ሲቀሰቅሱ ሳይ የታወሱኝ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው ብያችኋለሁ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ እፊታቸው መትረየስ ተደግኖ እንኳን፣ ለሥጋቸው ሳይሳሱ የሀገራቸውን ነፃነት ነው የሰበኩት፡፡ ሕዝቡ ለጣሊያን እንዲገዛ ስበኩ ሲባሉ በተቃራኒው ለጣሊያን እንዳይገዛ በድፍረት ሰበኩ፤ ለጣሊያን የሚያድር ውጉዝ ከመአሪዮስ ይሁን አሉ፡፡ በዚያም ጽናታቸው ከሕይወት ይልቅ ሞትን መረጡ፡፡ ከውሸት ይልቅ እውነትን አከበሯት፡፡ ከማስመሰል ይልቅ ሃቅን ወደዱ፡፡ ከብልጭልጯ ዓለም ይልቅ የነፍሳቸውን መንገድ አስቀደሙ፡፡ ለኩነኔ ከሚዳርግ ምድራዊ ድሎትና ምቾት ይልቅ ለሰማያዊ ጽድቅ የሚያበቃቸውን መከራና ስቃይ መረጡ፡፡ አባት ማለት እንዲህ ነው፡፡ ሰው ማለት እንዲህ ነው፡፡ እነ ማህተመ ጋንዲና እነፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ያሳዩን ፈለግ ይህንን ነው፡፡ ሺህ ዓመት ቀርቶ መቶ ዓመት እንኳን በቅጡ ለማይኖርባት ምድር ብለን በውሸት ተጀቡነን እውነትን እንዳንረጋግጣት ይህ የነማህተመ ጋንዲ ፍኖት በግልጽ ያስተምረናል፡፡ ለዚህ መብቃት መታደል ነው፡፡ ለዚህ አለመብቃት ደግሞ እንስሳነት ነው፡፡
እንስሳት ስለማያስቡ፣ ስለማይጠበቡ ኑሯቸው የፊት የፊቱን ነው፡፡ ብዙዎቹ እንስሳት ስለነገ ማሰብ መቻላቸውን አናውቅም፤ ያስባሉ ብንል እንኳን ደመ ነፍሳዊ እንጂ እንደኛ ምጡቅነት የላቸውም፡፡ የነሱ ማሰብ ብዙውን ጊዜ ከሆድ ጋር – ከምግብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከሆድ ጋር በተያያዘ ማሰብ እንግዲህ የእንስሳነት እንጂ የሰውነት መለኪያ ሊሆን እንደማይችል መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሰውን ሊያስጨንቀው የሚገባው ምን ታሪክ ጥሎ ማለፍ እንደሚኖርበት እንጂ ምን በልቶና ምን ለብሶ ምን ዓይነት ቤትስ ውስጥ ኖሮ ስንት ሀብትና ንብረት አፍርቶ ማለፉ ሊሆን አይገባም – ከዕዳሪነት ለማያልፍ ምግብና መጠጥና በብል ከመበላት ለማይድን ንዋይ እንዲሁም በጎርፍና በወጀብ ድራሹ ለሚጠፋ ቤትና ሕንፃ ሲባል እውነትን በሀሰት መለወጥ መጨረሻው ደይን ነው – መከራ፡፡ እነዚህን የምድር ፈተናዎች ያለፈ ሰው በርግጥም ሰው ነው፡፡በነዚህ ምድራዊ ፈተናዎች የተሰናከለ ሰው ግን ሰውነቱን አበላሽቷል – ሰውነቱን አማሰነው፡፡ ብዙዎቻችን የወደቅንበት ፈተና እንግዲህ ይህ የሆድና የዓለም የሥጋ ፈተና ነው፡፡ አዘውትረን እንደምንለው ለመኖር ይበላል እንጂ ለመብላት አይኖርም፡፡ እጅግ ብዙው የዓለም ዜጋ ግን ነፍሱን ስቶ ሲራወጥ የምናየው ለመብላት ሲኖር ነው፡፡ ይህ ሞኝነት ነው፡፡ ለነፍስ ሣይሆን ምሥጥን ለማወፈር ዘመቻ ይዘናል፡፡
የክርስትና እምነት የማዕዘን ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለዚህ ወይ ለዚያ ዘር አይደለም፡፡ ለነጭ ወይ ለጥቁርም አይደለም፤ ለሴት ወይ ለወንድ አይደለም፤ ለአውሮፓ ወይ ለአፍሪካ አይደለም፡፡ ያስተማረውም “ወንድምህን እንደራስህ ውደድ” እንጂ በዘርና በጎሣ የምትመሳሰለውን አፍቅረህ ሌላውን ገደል ክተት ወይም ባገኘኸው መሣሪያ እንደዐይጥ ጨፍጭፍ የሚል አይደለም፡፡ ነገር ግን ክርስቶስን በቅንዋተ መስቀል የቸነከረው የጨለማው ንጉሥ ሊቀ ሣጥናኤል ይህችን ምድር ከረጂም ዘመናት ጀምሮ በወኪሎቹ አማካይነት ይገዛት ስለነበርና አሁንም አንቀጥቅጦ እየገዛት ስለሆነ – ጊዜው መቃረቡንም በዚህ አጋጣሚ መጠቆም ይገባል – ሰዎች ከዋናው የሃይማኖት ጫፍ እስከ ዝቅተኛው ተራ ምዕመን ድረስ በግልጽ ከህገ-ልቦናና ከህገ-እግዚአብሔር ሲወጡ እናስተውላለን፡፡
ከታሪክ መዛግብት እንዳነበብነው ስሙን የማላስታውሰው የሮማው ሊቀ ጳጳስ የጣሊያን ወራሪ ኃይል የምሥኪን ሕዝብ ሀገር ኢትዮጵያን ቅኝ እንዲገዛ ባርኮና ቀድሶ ልኮታል – የጣሊያን ዘመናዊ ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ የእሳት ድኝ እንደሚያዘንብና የእግዚአብሔር ፍጡርና የጽላቱ ማደሪያ የሆነው ቅዱስ ገላ አላበሳው እንደሚረግፍ ጳጳሱ እያወቀ፡፡ ያ ድርጊት ከአንድ ሊቀ ጳጳስ አይደለም ከተራ ዲያቆን እንኳን አይጠበቅም፡፡ ኃጥዕ ወአባሲ አባ ገብረ መድኅንም በዘረኝነት ደዌ የተለበጠ የተኩላ ለምድ ለብሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ የሠሩትን ደባና ተንኮል እንዲሁም ሃይማኖታዊ ህፀፅ አንረሳውም፡፡ ስለሆነም ሃይማቱኖና ሊቃነ ጳጳሣቱ በፍጹም አልተዋሃዱም ማለት እንችላለን – የሰይጣን ሠርጎ ገቦች እንጂ እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዳልነበሩ ተግባራቸው አፍ አውጥቶ ይመሰክራልና፡፡ እነሱ የሚመሯቸው ሃይማኖታዊ ተቋማት ደግሞ ቁልቁል እየወረዱ ለመንፈሣዊ ግሽበት መስፋፋት በርትተው ይሠራሉ እንጂ የመለኮትን ፀጋና ቸርነት የሚያበዛ አንድም የቅድስና በረከት አያስገኙም፡፡
ፍቅርን ለዓለም የሰበከው ክርስቶስ፣ “እጀ ጠባብህን ለሚፈልግ መጎናጸፊያህን ድገምለት” ብሎ ያስተማረው ክርስቶስ፣ “ቀኝ ጉንጭህን ቢጠፋህ ግራህን አዙርለት”” ብሎ በመስበኩ በድንጋይ የተወገረው ክርስቶስ፣ “ውኃ አጠጪኝ ያለሽን ሰው ብታውቂው አንቺ ነበርሽ ዳግም የማያስጠማውን ውኃ ከርሱ የምትጠይቂው” ብሎ ለሣምራዊቷ ውኃ ቀጂ በመንገር የተጻራሪ ጎሣዎችን ቅራኔ ለማስታረቅ የሞከረው ክርስቶስ፣ በዚህ የሮማ ጳጳስና በአቡነ ጳውሎስ ዘረኛ “ክርስቲያኖች” ምድር ላይ ሲወከል ማየት በእጅጉ ያምማል፤ የኅሊና ዕረፍትም ይነሣል፡፡ በዚህ የሃይማኖት አባት ድርቀት በሚያሰቃየን አሳሳቢና አስደንጋጭ ወቅት አቡነ መቃሪዮስን የመሰለ የክርስቶስና የፍጡራኑ እውነተኛ አገልጋይ ሲገኝ ውኃ እንዳገኘች ጽጌረዳ ሕይወትን ያለመልማል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ በቁሙ ካልተዘመረና ካልተወደሰ መዝሙርና ውዳሤ ከናካቴው ባይኖሩ ይሻላል እላለሁ፡፡ እናም አባቴን አባ መቃሪዮስን ከልቤ አወድሳለሁ፤ ብችል በግዕዝ ቅኔ በተቀኘሁላቸው፡፡ ሰው በወደደው ይቆርባል ወገኖቼ፡፡
ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃሪዮስ ሆይ!

እግዚአብሔር የዕድሜ ፀጋ ሰጥቶዎት ይህችን የሚወዷትን ሀገር በነፃነት ዘመኗ ለማየት ያብቃዎ፡፡ ኢትዮጵያ ያጣችው እንደርስዎ ያለ እውነትን ምርኩዝ ያደረገ አባት ነውና እርስዎን መሰሉን ያብዛልን፡፡ እኔ ኃጢያተኛ ልጅዎ በሀገር ውስጥ አዲስ አበባ ላይ የምኖር የምሥኪኗ ኢትዮጵያ ልጅ ነኝ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀምሮ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቁሜያለሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያን እጇ ተጠምዞ ለወያኔው መንግሥት ካደረችና እነ አለቃ አያሌውን የመሰሉ አባቶች ሲያርፉ እንኳን እንደውሻ ሞት አልባሌ ቦታ ከጣለች ወዲህ፣ አባ ፈቃደ ሥላሤን የመሰሉ አባት በዐውደ ምሕረት በጥይት ከገደለች/ካስገደለች ወዲህ ፈጣሪ እስኪያድሳት ድረስ ደጇን ላለመርገጥ ተጸይፌያለሁ – ስህተተኛ ልሆን እችላለሁ፡፡ ግን ሰው ነኝና ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ሳስብ በዚያ የሚደረገው መልካም ያልሆነ ነገር ሁሉ ከፊቴ እየተደቀነ ይፈታተነኛልና አልሄድም – መናገር ብጀምር የማልጨርሰው ጉድ በየቤተክርስቲያኑ ይፈጸማል – ሕዝቡ ግን አማራጭ ስለሚያጣ ይሄዳል – አንዳንዱም መፍትሔ የሚያመጣ እየመሰለው ሃይማኖቱን ይቀይራል፤ ግን አላወቀውም እንጂ አለቃ ገ/ሃና “እዚያም ቤት እሳት አለ” እንዳሉት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈጥኖ ካልደረሰልን ልንጠፋ ነው ብቻ ሣይሆን ከጠፋን ቆየን – በአካል መንከላወስ በመጥፋት ሂደት እንደዋና ምልክት ካልተቆጠረ፡፡
ይሁንና አምላኬን ባለሁበት ቦታ ሁሉ አመልከዋለሁ – ስተኛም ስነሣም፣ ስበላም ስጠጣም ዘወትር ስሙን እየጠራሁ አመሰግነዋለሁ፤ መሓሪ መሆኑንም አምናለሁ፡፡ እንደኔ የሆነ ደግሞ ብዙ ሰው አለ፡፡ የእርስዎን ጸሎት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰምቶ ከነዚህ የጠፉ ገዢዎች በቅርቡ ነፃ እንዲያወጣንና ትክክለኛ አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ተረክበው ምዕመናንን በእውነተኛው የእግዚአብሔር መንገድ እንዲመሩት እመኛለሁ – ያኔ የጠፉ በጎች ይሰበሰባሉ፡፡ ያኔ ደስታና ሃሤት በመላዋ ሀገራችን ይናኛል፡፡ ያኔ ኢትዮጵያዊነት ብቻውን ይበቃናል፡፡ ያኔ “ ብሔርህ/ነገድህ ምንድነው?” ተብሎ የማይጠየቅበት ለሁሉም ዜጎች እኩል የሚሠራ ህግና ሥርዓት ይተከላል፡፡ ያም ቀን የቀረበ ይመስለኛል፤ ምልክቶቹ ሁሉ ተፈጽመዋልና፡፡
ከአናት የተበላሸ ነገር ከሥር ይጠራል ማለት ዘበት ነው፡፡ ዕውርን ዕውር ቢመራው ተያይዞ ገደል እንጂ ድኅነት የለም፡፡ እኛም የሆንነው እንደዚህ ነው፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፉ “ከእናንተ አንዱስ እንኳ ያለ ኃጢኣት የለም፡፡” ቢልም ኃጢኣት እንደብርቅ የሚታይበት ዘመን አልፎ በአሁኑ ወቅት ኃጢኣት የጽድቅ ያህል እየተቆጠረች ስለምትገኝ ለይቶለት ያልጠፋ ሰው ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የፖለቲካውን ክንፍ ትተን የሥጋን ፈተና መወጣት ባቃታቸው አባቶች እየተመራን ጽድቅን እናገኛለን ማለት ደግሞ በጣም በተለመደው አገላለጽ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ብሎ እንደመጠበቅ የሚቆጠር የዋህነት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ክርስቶስ ቀርቶ ገንዘብ የቤተ ክርስቲያናችን የማዕዘን ራስ ሆናለች፡፡ መልካም ሥራ ሣይሆን ኃጢኣት የጽድቅ መንገድ ከሆነች ሰነበተች፡፡ የሚጸየፋት ሰው አጥታ ከሞላ ጎደል የሁሉም ሰው ሞልቃቃ ልጅ ሆነች፡፡
ለማጠቃለል ያህል ውድ ኣባቴ አቡነ መቃሪዎስ! እግዚአብሔር የመረጠዎት መሆንዎን ከተግባርዎ መረዳት አያቅትምና በረከቱን ያብዛልዎ፡፡ በዚህ አብዛኛው ሰው በጎጥና በወንዝ ተከፋፍሎ ለወያኔ ዕድሜ መርዘም የድርሻውን አስተዋፅዖ እያበረከተ በሚገኝበት ክፉ ዘመን እርስዎን ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ማግኘት ለኢትዮጵያ ታላቅ መለኮታዊ ቡራኬ ነው፡፡ ይህን የምለው እዚህ ያለውን ሁኔታ በግልጽ ስለምረዳ ነው፡፡ ፖለቲካውና ሃይማኖቱ ተቀላቅለው አንድም ሁለትም እየሆኑ የዘረኝነቱ ጠረን አገር ምድሩን አግምቶታል፡፡ ይህን አደገኛ የታሪክ አንጓ በጤናማ አሠራርና በፍትሃዊ አስተዳደር ለመተካት በሚደረገው ሁለገብ ጥረት የእርስዎ ድርሻ ምትክ እንደሌለው ሁሉም ሀገር ወዳድ ይገነዘባል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ የተቀደሰ ሥራዎ ገና የሰማዕትነትን ግዳጅ ባይወጡም ጅምር ሰማዕትነትዎ ለኢትዮጵያ ሀገራችን የምሕረት ዝናብን እንዲያዘንብላት የዘወትር ጸሎቴ መሆኑን በታላቅ ትህትና መግለጽ እፈልጋለሁ – ደግሞም ሰማዕትነት በግድ የአንገት በሠይፍ መቀላትን ወይም የደረት በጦር መወጋትን የሚጠይቅ አይመስለኝም፤ የሞቀ የአውሮፓና አሜሪካ ኑሮውን ትቶ ለትግል በረሃ መውረድም አንዱ የሰማዕትነት መገለጫ እንደሆነ በበኩሌ ይገባኛል፡፡ ቸሩ ፈጣሪያችን እርስዎን ስለሰጠን ለዘላለሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡ በጅምርዎ ሁሉ ኃያሉ አምላክ አጠገብዎ ሆኖ ይራዳዎት፡፡ ሌሎችም የእርስዎን ፈለግ እንዲከተሉና የጠፋውን ትውልድ እንዲታደጉ ፈጣሪ ያነሳሳልን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
ይሄይስ አእምሮ
yiheyisaemro@gmail.com

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47458#sthash.lnbrilLP.dpuf

1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete