እነ በቀለ ገርባ ላቀረቡት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ ማ/ቤት አስተዳደር መልስ ሰጥቷል
በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት እነ በቀለ ገርባ (22 ሰዎች) የእስር ቤቱ አስተዳደር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሰባቸው መሆኑን ሰኔ 15/2008 ዓ.ም ለፍርድ ቤት ላቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ መልስ ሰጥቷል፡፡
ዛሬ ሰኔ 27/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች በጠበቆቻቸው በኩል የማረሚያ ቤቱ መልስ ደርሷቸዋል፡፡ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሰኔ 24/2008 ዓ.ም በጻፈው ሦስት ገጽ መልስ ላይ እንደተመለከተው፣ ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ የተቋሙን ስም ለማጥፋት የቀረበ ነው ብሏል፡፡
ተከሳሾች ግንቦት 26/2008 ዓ.ም የፍ/ቤት ቀጠሯቸው ‹ከሌሎች እስረኞች በተለየና ተጽዕኖ በሚፈጥር መልኩ ጥቁር ልብስ በመልበስ እስረኞች ውስጥ ብጥብጥ እንዲፈጠር› ለማድረግ ጥቁር አትለብሱም ሲባሉም በፓክአውት እና በቁምጣ ፍ/ቤት መቅረባቸው ሆን ብሎ የተደረገና የተቋሙንና የመንግስትን ስም እያጠፋ ስለሆነ ‹‹ፍ/ቤቱ አደብ እንዲያሲዛቸው›› ማረሚያ ቤቱ መጠየቁን በምክትል ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ አብርሃ የተጻፈው የማረሚያ ቤቱ መልስ ያመለክታል፡፡
ተከሳሾች ጨለማ ቤት ስለመታሰራቸው ያቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ጨለማ ቤት የለውም፣ አቤቱታው የተቋሙን ስም ለማጥፋት የቀረበ ነው ሲል ማረሚያ ቤቱ በመልሱ ላይ ገልጹዋል፡፡ እንዲያውም፣ ‹‹ሙሉ ቀን በሩን ክፍት አድርጎ እስረኞችን ሲያዝናና የሚውል መሆኑን ፍ/ቤቱ ይወቅልን›› ብሏል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ተከሳሾች በቤተሰቦቻቸው እንዳይጎበኙ ገደብ ተጥሎባቸዋል የተባለውም ሀሰት መሆኑን መልስ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም ‹‹ለጥበቃና ደህንነት በሚያመች መልኩ›› መስራታቸውን ወደፊትም እንደሚቀጥሉበት በመልሱ ላይ ተመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾች ‹‹እውነት በሌለው አቤቱታ ከሚያጨናንቁትና ጊዜ ከሚያጠፉ ፍ/ቤቱ አመልካቾችን ተቋም የመወንጀል ተግባር እንያቆሙ ህጋዊ እርምት እንዲሰጥልን›› ሲል ማረሚያ ቤቱ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ በሀኪም የታዘዘላቸውን መድሃኒት እንዳያገኙ መደረጋቸውን ለችሎት አመልክተዋል፡፡ ይህን በተመለከተ በዕለቱ የተገኙት የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ምክትል ኦፊሰር አብርሃም በርሄ መልስ እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ ኦፊሰሩ እንደሚሉት ‹‹ማንም ተከሳሽ መድሃኒት አልተከለከለም፡፡ የታዘዘላቸው መድሃኒት ካለ በተቋሙ ባለሙያዎች ታይቶ ይደርሳቸዋል›› ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ እና ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት በሚል ከመደበኛ ቀጠሮው በፊት፣ ማለትም ሐምሌ 8/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በቀጠሮው ዕለት ማረሚያ ቤቱ ሁሉንም ተከሳሾች እንዲያቀርብም ታዝዟል፡፡
No comments:
Post a Comment