Friday, October 2, 2015

በሽብርተኝነት የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለጥቅምት 3 ተቀጠረባቸው • አቶ ዳንኤል ሽበሽ ጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝ ታውቋል በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

በሽብርተኝነት የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለጥቅምት 3 ተቀጠረባቸው
• አቶ ዳንኤል ሽበሽ ጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝ ታውቋል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ሀምሌ 14/2007 ዓ.ም የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲለቀቁ ወስኖላቸው የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሽበሽና አቶ አብርሃም ሰለሞን ላይ ተጠይቆባቸው የነበረው ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱ ለጥቅምት 3/2008 ዓ.ም ለቃል ክርክር ተቀጥረዋል፡፡
አምስቱ ተከሳሾች የተጠየቀባቸው ይግባኝ ተቀባይነት ይኖረዋል አይኖረውም የሚለውን ጉዳይ ለመወሰን ዛሬ መስከረም 21/2008 ዓ.ም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቀጥረው የነበር ሲሆን አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብርሃም ሰለሞን ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲቀርቡ አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ ዳንኤል ሽበሽ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ ዳንኤል ሽበሽ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሳይቀርቡ በውስጥ ይግባኙ ተቀባይነት አግኝቶ ቀጠሮ እንደተሰጠባቸው ከመዝገብ ቤት የታወቀ ሲሆን ሶስቱ መቀጠራቸው ከታወቀ በኋላ ዘግይተው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሱት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብርሃም ሰለሞን በቢሮ ተመሳሳይ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ እነ ሀብታሙ በቀረቡበት ወቅት አቃቤ ህግ ያልተገኘ ሲሆን ስለ ቀጠሮው ምንም አይነት ምክንያት እንዳልተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ከተከሳሾቹ መካከል በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኘው አቶ ዳንኤል ሽበሽ በጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና ከቤተሰቦቹም ጋር መገናኘት እንደማይችል ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment