Saturday, October 3, 2015

በዋሽንግተን ዲሲ በትግራይ ኮሚኒቲ ሽፋን በጥቂት የትግራይ ተወላጆች መካከል ትልቅ ውዝግብ ተፈጥሯል -

ህወሓት የትግራይ ህዝብን እንደ ከለላ በመጠቀም በህዝቡ ስምና ደም እየነገደ እስከ መቼ ይኖራል? የሚለው አንገብጋቢና የህልውና ጥያቄ በሚሊዮኖች ኢትዮ}ያውያን በተለይም በየዋሁ ፣ ጨዋውና ሀገር ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ዘንድ በይፋ የማይነገር የአጀንት ቁስል ሆኖ ቆይቷል:: አሁንም የህዝቡን ብሶት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ሊፈነዳ እንደተቃረበ የሚያሳዩ ጭብጥ ምልክቶች እያየን ነው:: በቅርቡ አቶ ዳዊት ገብረእግዚኣብሄርን ጨምሮ በተለያየ መልኩ በህወሓት የይስሙላ ጉባኤም ሳይቀር በይፋ ሲስተጋባ የነበረው የህዝቡን እሮሮ “ ጆሮ ያለው ይስማ ” የሚያሰኝ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው:: ነገር ግን ስልጣንና ገንዘብን ደመ ነብሳቸውና የዓይን ብሌናቸው የሆነውን የህወሓት መሪዎች በተለይም የመለስ ዜናዊ ራእይ ጠባቂዎች ነን የሚሉና ከሻዕቢያ ጋር የጥቅምና የዘር ሐረግ ንክክ ያላቸው የህወሓት መሪዎች በመካከላቸው የጤፍን ያህል ክፍተት እንዳይፈጠር በመፍራት “ስልጣን እስከ መቃብር ” በሚል የጋራ መፈክር የህዝቡን ጥያቄ ጆሮ ዳባ በማለት በጉባኤ ስም በህዝቡ ፊት የውሸት ድራማ ሲሰሩ አይተናል:: ለዚህም ነው የህወሓት መሪዎች ቀኑንና ጊዜውን እየመሸባቸው መሆኑን ፣ በአንፃሩ ደግሞ የህዝቡን ተቃውሞና ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለና እየገነፈለ መሄዱን በውል ስለተገነዘቡ ዛሬ አልሞት ባይ ተጋዳይ በመሆን ከማንም ጊዜ በላይ የትግራይ ተወላጆችን የስልጣናቸውን መሳሪያና ማስረዘሚያ አድርገው ለመጠቀም ሲባል ሌሎች ሞላ አስገደሞች በሰሜን አሜሪካ እየተደራጁ ነው:: ከገብረተንሳይ ወልደዓብዝጊ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የህወሓት አንድ ለአምስት አደረጃጀት ፓሊሲ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ከተጀመረ ቆይቷል:: ዛሬም ህወሓት የራሱ የሆኑትን ሰላዩችን እያሰማራ በስደት ዓለም የሚኖሩትን የትግራይ ተወላጆች በአውራጃ ! በዘር ሐረግና በሀይማኖት እየከፋፈለ መበተንና እርስ በርስ የማናቆር ተግባር ስራዬ ብሎ ተያይዞታል::
ሰሞኑን የህወሓት ደጋፊዎች ማንም ሳያማክሩ የትግራይ ኮሚኒቲ በዋሽንግተን ዲሲ እናቋቁማለን በሚል ሽፋን የራሳቸው ሕገ ደንብን ይዘው በመምጣት ህዝቡን እያተራመሱት ይገኛሉ:: የህወሓት አረሜናዊ አገዛዝ አንገሽግሾት ሀገሩን ጥሎ በመሰደድ በባህር ማዶ የሚኖረውን ትግራዋይ ሳይቀር አንድ ለአምስት ለማደራጀት በብዙ ሚሊዮን የሚገመት የሀገሪትዋን አንጡራ ሀብት (ገንዘብ) በመርጨት በከፍተኛ ደረጃ እየተሯሯጡ የሚገኙት:: በዋሽንግተን ዲሲ ሰሞኑን የተነሳው ውዝግብም መነሻው ይኽው ነው:: የህወሓት 12ኛው ጉባኤ በመቀሌ ከተማ ለማካሄድ አንድ ሁለት ሳምንት ሲቀረው የህወሓት ፓሊት ቢሮ አባልና የአቶ አባይ ወሉ ሚስት ወይዘሮ ትርፉ ሶስት አባላት ያለው ከፍተኛ ሉኡክ በመምራት በሲያትል የጀመሩትን ጉብኝት በተለያዩ ከተሞች የሚገኙትን የትግራይ ተወላጆች ሰብስበው ለማነጋገር ሙኮራ አድርገው እንደ ነበር የሚታወቅ ነው:: የጉብኝታቸው አላማም አንዱ የአባይ ወሉ ቡድን በ12ኛው የህወሓት ጉባኤ በአሸናፊነት ለመውጣት ድጋፍ ለማሰባሰብ ነበር:: ሁለተኛው የጉብኝቱ አላማቸው ደግሞ በስደት ዓለም የሚገኘው የትግራይ ተወላጅ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ በሚደረገው ህዝባዊና ሀገራዊ እንቅስቃሴ በመሳተፍ የለውጥ አጋር እንዳይሆን ለብቻው ነጥሎ አንድ ለአምስት በማደራጀት የልጅ ልጆቹንም ጭምር ለህወሓት ዘላለማዊ ስልጣን መሳሪያ ሆኖ እንዲኖር ለማድረግ በውጭ ለሚገኙት ደጋፊዎቻቸው መመሪያ ለመስጠት ነው:: ነገር ግን የጉብኝታቸውን ሰሞን አቶ ዳዊት ገብረእግዚኣብሄር የትግራይ ህዝብ ሰቆቃን አስመልክቶ ያደረገውን ቃለ ምልልስ የህዝቡን ቀልብንና ልብ ትርታን የሚነካ ንግግር አየሩን ተቆጣጥሮት ስለነበር ለወይዘሮ ትርፉ ጥሩ አጋጣሚ አልነበረም:: የወይዘሮ ትርፉን ጉብኝት በዚሁ ፅሑፍ ለመጥቀስ የፈለግኩበት ምክንያት ሰሞኑን በዋሽንግተን ዲሲ በተነሳው ውዝግብ ጋር ተያያዝነትና ትስስር ስላለው ነው:: ወይዘሮ ትርፉ በዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮ}ያ ኤምባሲ አዳራሽ የተወሰኑት የትግራይ ተወላጆችን ጠርተው ባደረጉት ሰብሰባው ላይ ካሰሙት ንግግር ውስጥ እንዲህ ብለው ነበር:: “ባለፈው ጊዜ ወደ ጋምቤላ ክልል ለስራ ጉዳይ ሂጀ ነበር:: በጉብኝቴ ወቅትም እግረ መንገዴን በጋምቤላ ክልል የሚኖሩ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆችን አግኝቼ አነጋግሬ ነበር:: አብዛኞቹ ማን መሆኔን አያውቁም ነበርና እንዴት እዚህ ድረስ መጣችሁ ብዬ በተራ አነጋገር ስጠይቃቸው የሰጡኝ መልስ እንዲህ የሚል ነበር:: “እኛ ወደዚህ ክልል ተሰደን የመጣንበት ዋና ምክንያት ሀገራችንን ጠልተን አይደለም:: ነገር ግን በትግራይ አካባቢ ያለው የአገዛዝ ስርዓት ፈርተን ነው ሳንወድ በግድ ቤት ንብረታችንን ጥለን እዚህ የወጣነው:: ሌሎቹ ከኛ ጋር የወጡ ጓደኞቻችን ወደ ሱዳንና ሌሎች አጓራባቸው ሀገሮች ተሻግሯል:: እኛ ግን እንደ ዕድል ሆኖ እዚህ እንኖራለን” በማለት በምሬት ሲገልፁልኝ በውስጤ ሳቄን መቆጣጠር አልቻልኩትም ነበር:: እነዚህ ሰዎች እንዲህ ብለው የገለፁልኝ ምክንያት ህወሓት ወደ ማይቆጣጠረው ወደ ሩቅ ቦታ የሄዱትና ከህወሓት እጅ ያመለጡ መስሏቸው ነው:: እኔም በንግግራቸው በመገረም በሉ እንተያያለን!! ህወሓት በጓዳችሁ ውስጥ እንዳለ እናሳያችሗለን ብዬ በሆዴ እየሳቅኩኝ ተሰናበትኳቸው::” በማለት ንቀት! ትእቢት! ፌዝና ድንቁርና የተቀላቀለበት ንግግር አቅርቧል:: የወይዘሮ ትርፉ ንግግር ለደጋፊዎቻቸውና ታማኞቻቸው እንደ ጀግንነት የሚቆጥሩት ቢሆንም ሌሎቹ ግን ፀያፍ አነጋገር ሲሉ ትዕዝብታቸውን ገልፀዋል:: ቀደም ብለው ራሳቸው እንደገለፁትም የወይዘሮ ትርፉ ንግግር በተግባር ሲታይ “ ትግራዋይ የህወሓት አገልጋይና ታማኝ ካልሆንክ የትም ብትሄድ ከእጃችን አታመልጥም:: ስለዚህ ያለህ አማራጭ የኛ አገልጋይ መሆን ወይም የቁም እስረኛ ሆነህ አርፈህ መቀመጥ ነው:: አሊያም ትመታለህ“ የሚል የማስፈራሪያ መልእክት ለማስተላለፍ የተጠራ ስብሰባ እንደነበር የሚያሳይ ነው:: ዛሬ በዚሁ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በትግራይ ተወላጆች መካከል የተነሳው ውዝግብም ከወይዘሮ ትርፉ ዕቅድ የቀጠለ መሆኑን ሳይታለም የተፈታ ነው:: መንግስት በቅርቡ ከሞላ አስገዶም ጋር በተያያዘ የሰጠው መግለጫም ከወይዘሮ ትርፉ ንግግር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው:: ዋናው ቁም ነገር ሞላ አስገዶም ለምን ወደ ሀገሩ ተመለሰ ወይም ለምን ወደ ኤርትራ ሄደ የሚል አስተያየት ለመስጠት አይደለም:: መሄድም መመለሰም የራሱ ጉዳይ ነው:: ነገር ግን ሆን ተብሎ ከህወሓት መሪዎች ጋር በመመሳጠር ለጋ የትግራይ ወጣቶችን እየመለመለ በመውሰድ የእሳት ራት እንዲሆኑ በማድረግ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀሙትን በደል ግን ታሪክ ይቅር የማይለው አሳፋሪና ወራዳ ተግባር ነው:: ከላይ ወይዘሮ ትርፉ እንደገለፁት የሞላ አስገደምና የህወሓት መሪዎች ድራማም ዋና መልእክቱ “የትም ብትሄዱ ከኛ አታመልጡም:: እጃችን ረጅም ነው በውስጣችሁ መልምለን ያስገባናቸው የህወሓት ሰላዮች አሉ” የሚል ነው:: ሰሞኑን በዋሽንግተን ዲሲ በጥቂት የትግራይ ተወላጆች መካከል የተነሳው ውዝግብም መነሻና መድረሻው የሞላ አስገዶም ዓይነት ባህርይና ተልእኮ የተላበሱት ጥቂት ሰዎች የጠነሰሱት ሴራ ነው:: በነገራችን ላይ በጥቅም ተደልለው በህዝባዊ ትግል ላይ ጥቁር ታሪክ እየጣሉ እጃቸውን ለህወሓት መሪዎች እየሰጡ ያሉት እነ ሞላ አስገዶም ብቻ አይደሉም:: ሌሎቹ ሞላዎችም በየጊዜው የትግል ጎራውን ጥቅርሻ እየቀቡ ወደ ህወሓት እጃቸውን ለመስጠት እንደ እጅ መንሻ የተጠቀሙበት ብዙዎች ናቸው:: ቀደም ሲል ስብሓት ነጋ የቀየሰውን ከህወሓት ያፈነገጡትን የቀድሞ ታጋዮች ወደ ቀድሞ እናት ድርጅታቸውን የማስመለስ ፕሮጀክት ነው ዛሬ ስራ ላይ እየዋለ ያለው:: በዚሁ የስብሓት ነጋ ፕሮጀክት ምክንያት ጥቂት ጀነራሎችንና ኰለኔሎችን ጨምሮ ከትግል ሜዳ እየፈረጠጡ ለነ አባይ ወሉ እጃቸውን የሰጡት ህወሓት ነበር ታጋዮች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም:: ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ በትግራይ ኮሚኒቲ ስም እየተሰራ ያለው ድራማም የአቶ ስብሓት ነጋ ፕሮጀክት ነው ተግባር ላይ እዋለ ያለው:: ከዚህ ሁሉ ድራማ የምንረዳው ቁም ነገር በአንድ በኩል የህወሓት ስርዓት በተዳከመና አደጋ ላይ በወደቀ ቁጥር የትግራይ ህዝብም አብሮ አጥፍቶ ለመጥፋት መፍጨርጨር የተለመደ ስራቸው መሆኑን ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ተወላጆችን እርስ በራሳቸው አናቆሮና በታትኖ በማዳከም በአንፃሩ በትግራይ ምድር ለነፃነቱ፣ ለመብቱና ለሀገሩ ቀና ብሎ የማያይ ፣ የደነቆረና የደነዘዘ ትግራዋይ እንዲኖር በማድረግ ፀጥ ረጭ ብሎ የሚገዛ ትውልድ ለማፍራት ነው:: ስለዚህ ህወሓት በሀገር ቤትም ሆነ በስደት ዓለም ያለው ትግራዋይ ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳይወጣ በመካከሉ ሰርገው በመግባት በታኝ ተልእኮ የሚፈፅሙለትን አስመሳይ ምልምሎችን አስቀምጧል:: የዋሽንግተኑ የትግራይ ተወላጆች ውዝግብም ከላይ ላዩ ሲታይ የኪሚኒቲ ጥያቄ ይምሰል እንጂ በስተጀርባው ያለው አላማ ግን ሌላ ነው:: አላማውም ትግራዋይ ለመብቱና ለነፃነቱ እንዳይነሳ በታትነህ፣ አናቁረህ፣ አሸብረህና አደንቁረህ ግዛ የሚል ለአርባ ዓመት የቆየ መሰሪ የህወሓት ፓሊሲ ውጤት ነው:: ጉዳዩን አስመልክተን በሌላ ነጥብ እመለሳለሁ ደህና ሰንብቱልኝ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47096#sthash.hvOTff97.dpuf

No comments:

Post a Comment