ዛሬም ሀብታሙ አያሌውን ጠይቀነው ነበር። ብዙ ለውጥ ያላየሁበትን የጤና ጉዳይ፣ በሀብታሙ ጉዳይ ለተጨነቁ ወገኖቻችን መረጃ ሳደርስ በሰብአዊነት ውስጤ እየተረበሸ ቢሆንም የሰማሁትንና ያየሁትን እናገራለሁ።
"ማታ 2:30 ሰዓት ገደማ፤ ሀብታሙ "መፀዳጃ ቤት ውሰደኝ" ብሎኝ ድግፌ ወሰድኩት። ሀመሙ ጠንቶበት ይመስለኛል ብዙ ደም ፈሰሰው። ተረበሽን። ...መልሰን ካስተኛነው በኃላ ማደንዝዣ ተወግቶ ተኛ። ሁላችንም እጅግ ተሰቀቅን..... ሀብታሙ ከሀገር ወጥቶ ይታከም ዘንድ ሳንሰላች መታገል ይኖርብናል" ሲል የገለፀው ከጎኑ ሆኖ እያስታመመው የሚገኘው ዳንኤል ሺበሺ ነበር።
እኔም ከሀብታሙ ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል ቃላቶች ተለዋውጠን ነበር። "አይዞህ ሀብትሽ ትድናለህ። ከሀገር ወጥተህ ህክምና የማግኘት ዕድሉ ሙሉ በሙሉ አልተዘጋም። እድናለሁ ብለህ በጎውን አስብ። ውስጥህ ጠንካራ ነው ሳይህ" አልኩት ተጠግቼ።
"እሺ....ማደንዘዣው በጣም ያማል። እንዲህ ብሰቃይም ከእኔ በላይ የሚሰቃዩ እንዳሉ አስባለሁ" ሲል ድምፁ እንዳነሰ መለሰልኝ። መናገር ከበደውና ወደእኔ ጠጋ በል አለኝ በምልክት። ተጠጋሁት። "መናገር ቢከብደኝም አንተ ዝም ብለህ እውራኝ እኔ እሰማሃለሁ" አለኝ። ውስጤ ተረበሽ። እሱን ትቼ ውጪውን ወደመስኮቱ አማተርኩ። "በሀገርም ሆነ ከሀገር ውጪ ያሉ በርካታ ሰዎች በአንተ መታመም ተጨንቀዋል። ስላንተ ዘወትር በጣም ያስባሉ ...." ስል በአዕምሮዬ የመጣልኝን ሀሳብ ነገርኩት። ድምፁ እንዳነሰ "አመ ...ሰግናለሁ በልልኝ" ብሎ በእጅ ምልክት አይዞን አለኝ።
ድክም አለውና ዓይኑን ጨፈነ። እንባዬ መጣ። ወዲያውም አይኖቹን ገለጥ አደረገ። ሀብትሽን በሰላሙ ቀን... ለረዥም ሰዓታት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን እንዳልተካፈልኩት ዛሬ የምናገረው ነገር ጠፋብኝ።
መረበሼን ፊቴ ላይ እንዳያውቅ "አይዞህ!" ብዬ እጁን አጥብቄ በመጨበጥ የተኛበትን ክፍል ለቅቄ ወጣሁ።
No comments:
Post a Comment