★የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ጥፋተኛ ተብለው በተግሳፅ ታልፈዋል።
★አቃቤ ህጉ ጨጓራ ስላለብኝ ምሳ ካልበላሁ መቀጠል አልችልም ብሎ መስቀለኛ ጥያቄ ሳይጨርስ የጠዋቱ ችሎት ተቋልጧል።
★ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ በምስክርነት የተመዘገቡ ባለስልጣናት በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ታዟል።
ነሃሴ 12/2009 የእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብን ለማየት የተያዘ የአመቱ የመጨረሻ ቀን ነበር። ችሎቱ በቅድሚያ ከማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ጋር በተያያዘ ይሰጣል ያለውን ትእዛዝ ከተገለፀ በኋላ ነው መከላከያ ምስክሮችን መስማት የቀጠለው።
ከማረሚያ ቤት እንዲቀርቡ የተደረጉት ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ እንዲሁም በ9/12/2009 ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ከቤተሰብ የመጣ ምግብ እንዲበሉ ካዘዘ በኋላ ትእዛዙን አልፈፅምም ያሉት ኃላፊ ዋና ኦፊሰር ገብሬ አለማ በችሎት እንዲቆሙ ተደርጎ የተሰጠው ትእዛዝ ተነቧል። "ጉዳዩን ስንመረምረው ዋና ኦፊሰር ገብሬ አለማ የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ሳያከብሩ ቀርተዋል። ይህም የሆነው በኃላፊያቸው ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ ትእዛዝ መሆኑን ገልፀዋል። በሁለቱ ሰዎች የፍርድ ቤት ትእዛዝ አልተከበረም። ስለዚህ ጥፋት ተፈፅሟል። ጥፋት እንደሆነም ታምኖ ይቅርታ ተጠይቆበታል። የማረሚያ ቤት ደንብ ተብሎ በኃላፊው የተነበበው ማረሚያ ቤቱ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ እንዳለበት ይገልፃል። በእለቱ የቀረበላቸው ግን ተመጣጣኝ ምግብ አይደለም። ደረቅ ዳቦ ያለምንም ማወራረጃ ነው የተሰጣቸው። ያቀረቡት ምክንያት የሚያዋጣ የሚያወላዳ አይደለም። ስለሆነም ለተፈፀመው ጥፋት ይቅርታም ስለተባለበት አስተማሪ ይሆናል በሚልም የወሰነው ቅጣት አለ። ቅጣቱም ተግሳፅ እንዲሆን ተስማምተናል። ወደፊት ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ።" በማለት ትእዛዙን ያነበቡት የግራ ዳኛ አቶ ግርማ ደባሱ ፤ ከዚህ በኋላም በዚህ ችሎትም በሌላ ችሎትም ፍርድ ቤት የሰጠውን ትእዛዝ ባይጥማቸውም እየመረራቸውም ቢሆን መውሰድ እንዳለባቸው፤ በተለይ ደግሞ ኦፊሰር ገብሬ አለማ በተደጋጋሚ ለችሎቱ የሚሰጡት ምላሽ የፍ/ቤቱን ክብር በሚመጥን መልኩ አለመሆኑን ስለሆነም እንዲያስተካክሉ ወይም ደግሞ ይሄን ተረድቶ የሚሰራ ሰው እንዲላክ እንዲደረግ ለዋና ሱፐር ኢንቴንዳንት አሰፋ ኪዳኔ ገልፀውላቸዋል። የተነበበው የቅጣት ትእዛዝም ለማረሚያ ቤቱ እንዲደርስ እንደሚደረግ ተገልፇ ኃላፊዎቹ ተሰናብተዋል።
በዛሬው ችሎት 3ት መከላከያ ምስክሮችን ማቅረባቸውን ለችሎት ያሳወቁት ጠበቆች [አቶ አመሃ መኮንን እና አቶ አብዱልጀባር ሁሴን] 1ዱ ምስክር ለ1ኛ ተከሳሽ አቶ ጉርሜሳ አያና እንዲሁም 2ቱ ተከሳሾች ለ4ኛ ተከሳሽ አቶ በቀለ ገርባ የሚመሰክሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በቅድሚያ እንዲመሰክሩ የተደረገው ለአቶ በቀለ ገርባ የሚመሰክሩት በመዝገቡም አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ጉርሜሳ አያና ናቸው። የሚመሰክሩበትም ጭብጥ አቶ በቀለ በኦፌኮ አመራርታቸውም ሆነ ከዛ ውጪ አመፅ ቀስቅሰው እንደማያውቁ እንዲሁም ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ ንግግር አድረገው እንደማያውቁ የሚያስረዱላቸው መሆኑን በጠበቆች ተገልፇል።
አቶ ጉርሜሳ ዳኞች ስራቸው ምን እንደሆነ ሲጠይቋቸው "እስረኛ" የሚል ምላሽ ከሰጡ በኋላ ከጠበቆች ለሚቀርብላቸው ዋና ጥያቄ የሚከተለውን መልሰዋል። አቶ በቀለን በኦፌኮ ፓርቲ ውስጥ እንደሚያቋቸው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አቶ በቀለን ያዩአቸው መስከረም 30/2008 የነበረ ስብሰባ ላይ መሆኑን፣ ከዛ በፊት ግን በሚዲያ ስለሳቸው ይከታተሉ እንዱሁም የሚሰጡትን ቃለመጠይቅም ሆነ ንግግር ይከታተሉ እንደነበረ፣ በኦፌኮ ፓርቲ ውስጥ ሁለቱም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል መሆናቸውን፣ አቶ በቀለ የፓርቲው ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር መሆናቸውን፣ ኮሚቴው 24 አባላት እንዳሉት ኮረም ሞላ የሚባለውም 12 እና ከዛ በላይ አባል ሲገኝ መሆኑ፣ ኮረም ሳይሞላ ኮሚቴው እንደማይሰበሰብ እና ምንም ነገር እንደማይወስን፣ አቶ በቀለን በሁለት ስብሰባ ወቅት ብቻ እንዳዩአቸው (መስከረም 30/2008 እና ህዳር 25/2008) እንዲሁም አቶ በቀለ ከእስር ከተፈቱ በኋላ የምርጫ ወቅት ስለነበረ ወደ ምርጫ ጉዳይ እንደገቡ ከዛም ወደ ውጪ እንደሄዱ ከዛ ሲመለሱ ደግሞ ወደ መደበኛ ስራቸው እና ያቋረጡትን ትምህርት ለመቀጠል ፕሮሰስ ሲያደርጉ የነበረ በመሆኑ ምክንያት ብዙ ስብሰባዎች ላይ እንዳልተገኙ በስብሰባ የተባለውን ነገር እና አዲስ መረጃዎችን በስልክ እንደሚለዋወጡ ገልፀዋል። በ2008 በኦሮሚያ ስለተነሳው ተቃውሞ፣ የፓርቲያቸው ምላሽ እና የአቶ በቀለ አቋምን በተመለከተ እንዲህ
"መንግስት ወደ ውይይት እንዲመጣ ግፊት ለማድረግ ጥረናል። ደብዳቤ ፅፈናል። መግለጫ አውጥተናል። መንገድ በመዝጋት እና ንብረት በማውደም ጥቃት አልፈፀምንም። አቶ በቀለም እንዲህ አድርጉ ብሎ ትእዛዝ አላስተላለፈም። የድርጅታችን አቋምም እንዲህ አልነበረም። መንግስትም ያውቃል። የአቶ በቀለን ፌስቡክ ላይ የሚፃፈውን እከታተል ነበር። አንድም ቀን በሃይል የሚወሰድ እርምጃን ደግፎም ቀስቅሶም አያውቅም። እንዲያውም፤ የሰው ንብረት ላይ አንዳች ነገር እንዳታደርጉ ሰውም እንዳትጎዱ እያለ ነበር ሚፅፈው። ስብሰባ ላይም እንዲህ ነበር የሚለን። መንግስት ወደ ሃይል ቢቀየርም እኛ ወደ ሃይል መግባት የለብንም። ምክንያቱም እኛ እውነት አለን ወደ ሃይል ከገባን የሚደግፈን ህዝብ ይጎዳብናል ይለን ነበር። የትግል ስልቱም ሰላማዊ ነው። ለወደፊቱ ለሃገራችን ሰላም የሚያመጣው መንገድ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ መታገል እንደሆነ ፅኑ እምነት አለው። ከመሬት ወረራው ጋር በተያያዘ አርሷደሮች ያለምንም ካሳ መፈናቀላቸውን ይቃወማል። አንድ ከተማ የሌላ ከተማ ማስተር ፕላን ማዘጋጀትም ከህገመንግስቱ ውጪ ነው ይላል። በሌላ ብሄር ላይ የተለየ አስተሳሰብ የለውም። ሁሉም እኩል መሆን አለበት ነው የሚለው። የፓርቲያችን አቋምም ይህ ነው። ፓርቲያችን የኦሮሞ ይሁን እንጂ ከሌሎችም ጋር አብረን ነው የምንሰራው። ከትግሬ፣ ከደቡብ፣ ከአማራ።"
አቃቤ ህግ ለአቶ ጉርሜሳ በመስቀለኛ ጥያቄ አቶ በቀለ አመፅ የማነሳሳት ተግባር ይፈፅሙ አይፈፅሙ በምን እርግጠኛ እንደሆኑ ጠይቀዋቸው ሲመልሱ " በኛ ፓርቲ ለአባላት እንዲህ አይነት ተግባር የተከለከለ ነው። አቶ በቀለ ደግሞ ከአባልነት በተጨማሪ አመራር ነው። ህጉን አክብሮ የማስከበር ሃላፊነት ያለበት ሰው ነው። በባህሪውም በሃይል የሚያምን ሰው አይደለም።" በማለት መልሰዋል።
አቃቤ ህግ በመቀጠል አቶ በቀለ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጓቸው የስልክ ግንኙነቶች አመፅ ቀስቅሰው ይሁን አይሁን ያውቁ እንደሆን በማለት ያቀረበው ጥያቄ ከአቶ በቀለ ዘንድ ተቃውሞን አስነስቷል። "አቶ ጉርሜሳ የኔ መከላከያ ምስክር ናቸው እንጂ የሱ [የአቃቤ ህግ] አይደሉም። አመፅ ቀስቅሷል የሚል ከሆነ እንደዛ ብሎ የሚመሰክርለት ማምጣት ነበረበት። " በማለት አቶ በቀለ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል። በዚህ መሃል አቃቤ ህግ ከማይክ ውጪ [ሪከርድ ውስጥ እንዳይገባ] ለመናገር ጠየቆ ተፈቅዶለት፤ ዛሬ አርብ በመሆኑ የምንወጣ የነበረው 5:30 ነው አሁን ደግሞ አልፏል። በተጨማሪም እርቦኛል ጨጓራዬን አሞኛል። እያመመኝ ስራዬን በአግባቡ መቀጠል አልችልም። " በማለት ችሎቱ እንዲቋረጥ ጠይቋል። ዳኞችም ሰአቱ እንዳለፈ እንደሚያውቁ፣ ከመዝገቦቹ ብዛት የተነሳ እንዲህ አይነት አሰራር የተለመደ መሆኑን፣ እነሱም ረሃባቸውን ችለው እየሰሩ እንደሆነ በመጥቀስ ትንሽ ታግሶ መስቀለኛ ጥያቄውን ከጨረሰ በኋላ ቢወጣ ወይም አብሮት ያለው አቃቤህግ እንዲተካው ሃሳብ አቅርበዋል። አቃቤ ህጉም ጥያቄ ማቅረብም ሆነ መስራት የሚችለው ጤናው ሲጠበቅ መሆኑን እና በዚህ ሁኔታ ሆኖ መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ እንደማይችል እንዲሁም የተሰየመው አቃቤህግ እሱ ስለሆነ እሱ ራሱ መቀጠል እንዳለበት ገልፇል። አቶ በቀለም " እንዲህ አይነት ነገር ከዚህ ትልቅ ተቋም የሚጠበቅ አይደለም። ለፍ/ቤቱ ስርአትም የሚመጥን አይደለም። እኛ ፆማችንን እየዋልን ነው ምንከታተለው። ያው እኛ ለህዝቡ የፍትህ ስርዓቱ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ነው። ምናልባት አቃቤ ህጉ ከሌላ አካል መመሪያ ለመቀበል የፈለጉ ነው የሚመስለን።" በማለት ሃሳባቸውን ተናግረዋል።
"እንዲያውም ይህ ጉዳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። ተከሳሾች ምሳ ሳይበሉ የከሰአቱን ችሎት እንዲከታተሉ በመደረጋቸው የሚያቀርቡት አቤቱታ ተገቢ መሆኑን የሚያሳይ ነው።" ያሉት የመሃል ዳኛው አቶ በላይሁን አወል፤ ከዚህ ቀደም አቃቤ ህጎች ተጋግዘው ሲሰሩ የነበረበት አግባብ እንደነበረ አስታውሰው በዚህ ሁኔታ እንዲቀጠል ቢታዘዝም ለችሎቱ እንደማይጠቅም በመግለፅ "አሁን 6:35 ነው ልክ 7:30 ላይ እንገናኝ" ብለው የተከሳሾቹን ምሳ በተመለከተ ከዚህ በፊት በተወሰነው መሰረት የተመጣጠነ ምግብ እንዲበሉ በማለት የጠዋቱን ችሎት ዘግተዋል። [ክርክሩ 15 ደቂቃ ያክል ቢፈጅም በመዝገቡ የተሰየመው አቃቤህግ አቶ አንተነህ በአቋሙ በመፅናቱ ምንም መቀየር አልተቻለም።]
የከሰአቱ ችሎት እንደ ጀመረ አቶ በቀለ ተነስተው አሰተያየታቸውን ሰጥተው ነበር። "ከሰአት እንደወጣን ወደሽንት ቤት ሄደን ነበር። እጃችን እንኳን ለመታጠብ ሳይፈቀድልን አንድ ዳቦ ተሰጥቶናል። እሷን በልተን ነው እዚህ ያለነው። አቃቤ ህጋችን ምሳ በልተው ጤናቸው ተሽሏቸው ስለመጡ ደስ ብሎናል።" የሚል፤ አቶ በቀለ ገርባ ከሰጡ በኃላ ዳኞቹ ምንም ምላሽም ሃሳብም ሳይሰጡ በጠዋቱ ችሎት ተቋርጦ ወደ ነበረው የአቶ ጉርሜሳን መስቀለኛ ጥያቄ ምላሽ ወደ ማድመጡ ሂደት ተገብቷል።
አቃቤህግ ጥያቄውን በድጋሚ አቅርቧል። አቶ በቀለ ከሌሎች ጋር በሚያደርጉት የስልክ ልውውጥ ቅስቀሳ ያድርጉ አያድርጉ የሚያቁት ነገር አለ የለም ለሚለው የአቃቤ ህግ ጥያቄ አቶ ጉርሜሳ ሲመልሱ "የግል ጉዳያቸውን በተመለከተ ከቴሌ ሴንተር ብትጠይቅ ጥሩ ነው። የፓለቲካ ጉዳይ ከሆነ ግን አውቃለሁ። ምን አይነት አመለካከት እንዳለው አውቃለሁ። በፓርቲያችን አንድ ሰው ወደ አመራርነት የሚመጣው ደንቡን እና ተልእኮውን ሲተገብር እና ሲያስተገብር ነው። አቶ በቀለ ደግሞ የስራ አስፈፃሚም አባል እና ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር ነው።" ብለዋል። አቃቤ ህግም መስቀለኛ ጥያቄውን መጨረሱን በመግለፁ ጠበቆች ለአቶ ጉርሜሳ ባቀረቡላቸው የድጋሜ ጥያቄ የሚከተለውን መስክረዋል። አንድ የፓርቲያቸው አባልም ሆነ አመራር ከፓርቲያቸው ተልእኮ ውጪ የተንቀሳቀሰ ከሆነ የሚገመገምበት አግባብ መኖሩን እንዲሁም አቶ በቀለም በዚህ ጉዳይ ተገምግመውም ሆነ ሪፖርት ቀርቦባቸው እንደማያውቅ መስክረዋል። በተጨማሪም ከፓርቲ ውጪ ባላቸው ግንኙነት አመፅ ስለመቀስቀሳቸው ሰምተው የማያውቁ እና በፍፁም ሊሆን የሚችል ነገር አለመሆኑን በመግለፅ አቶ በቀለ የሰላማዊ ትግል አራማጅ በመሆናቸው የማርቲን ሉተር ኪንግ መፅሃፍ ተርጉመው ያቀረቡ መሆኑን በመግለፅ ምስክርነታቸውን ጨርሰዋል።
በመቀጠል ለአቶ በቀለ ምስክር ሆነው የቀረቡት አቶ ጉቱ ሙሊሳ ናቸው። አቶ ጉቱ ሙሊሳ አቃቤ ህግ ከደህንነት ቢሮ ስልክ በመጥለፍ አገኘሁት ባለው ሪፓርት ላይ ጊንጪ ነዋሪ መሆናቸው ተጠቅሶ አቶ በቀለ ‘መሬታችንን ጉራጌ እና ስልጤ ሲወስደው ዝም አንልም’ ብለዋቸዋል የተባሉ ናቸው። አቶ ጉቱ ሲመሰክሩ፤ የኦፌኮ አባል መሆናቸውን፣ መኖሪያቸው አዲስ አበባ እንደሆነ፣ አቶ በቀለ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከውጪ ሲመለሱ ጥቅምት ወር 2008 ላይ ለሰላምታ መጨረሻው 07 በሆነ ስልክ እንደደወለላቸው እንዲሁም ከመሬት ጋር በተያያዘ ያወሩት ነገርም ሆነ ያስተላለፉላቸው መመሪያ አለመኖሩን መስክረዋል።
አቃቤ ህግ እንዴት የደወሉበትን ጊዜ እንዳስታወሱ እና ለሌሎች የደወሉበትን ጊዜም ማስታወስ አለማስታወሳቸውን ጠይቋቸው፤ የሌሎች ሁለት ወዳጆቻቸውን የመጨረሻ ቁጥር በመጥቀስ ጊዜውንም ለማስታወስ ሞክረዋል እንዲሁም የአቶ በቀለን በተለየ የሚያስታውሱበት ምክንያት ከእስር የወጡት በቅርብ በመሆኑ እና ከተፈቱ በኋላ ስላልተደዋወሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻ ለመመስከር የቀረቡት አቶ ሉምባ ደምሴ ይባላሉ። ለ1ኛ ተከሳሽ አቶ ጉርሜሳ አያና ምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ነው የቀረቡት። በአቃቤ ህግ የማስረጃ ዝርዝር አቶ ጉርሜሳ አቶ ሉምባን ደውሎ በኦሮሚያ የተነሳው አመፅ ወደ ደቡብ እንዲስፋፋ ነግሯቸዋል ተብሎ ከደህንነት ቢሮ የተገኘው የስልክ ጠለፋ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። ምስክሩ ከ1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያና ጋር ተደዋውለው በኦሮምያ የተነሳው አመፅ በደቡብ መስፋፋት እንዳለበት እንዳልነገሯቸው የሚያስረዱ መሆኑን ጠበቆች በጭብጥነት አሲዘዋል። በጠበቆች በቀረበላቸው ዋና ጥያቄ መሰረት የሚከተለውን መስክረዋል። አቶ ጉርሜሳን የኦፌኮ አመራር ሆነው እንደሚያቋቸው፣ እሳቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ አመራር በመሆናቸው በመድረክ የሚገናኙ መሆኑን፣ ከጉርሜሳ ጋር በማህበራዊም ሆነ ፓለቲካዊ ጉዳዮች እንደሚጠያየቁ፣ ሁለቱም እንደ ፓርቲያቸው ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እነ የምርጫ ፓለቲካ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ እንዲሁም በስልክ ተደዋውለው የነገሯቸው ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል። አቃቤ ህግ " ‘በኦሮሚያ የተነሳው አመፅ ወደ ደቡብ እንዲስፋፋ’ የሚለው ሃሳብ ወንጀል ነው አይደል?" በሚል ያቀረበው መስቀለኛ ጥያቄ፤ በዋና ጥያቄ ያልተነሳ ነው በተጨማሪም እራስን መወንጀል ይሆናል ብለው የተከሳሽ ጠበቆች ተቃውመውታል። አቃቤ ህጉ ተቃውሞው ውድቅ እንዲደረግ ቢከራከርም ዳኞችም ወንጀል ነው አይደለም የሚለው ነገር ምስክሩ የሚመሰክሩበት ፍሬ ነገር አይደለም በማለት ጥያቄው እንዲታለፍ በመወሰን የቀረበውን መቃወሚያ ተቀብለዋል። ዳኞች አክለውም ከጉርሜሳ ጋር አልተነጋገርኩም ባሉበት ጉዳይ ላይ [በሌለ ጉዳይ ላይ] እየተከራከርን ነው ብለዋል። አቃቤ ህግ መስቀለኛ ጥያቄውን በመቀጠል በስልክ ልውውጥ ከሚያደርጓቸው ሰዎች ጋር ሁሉ ያወሩትን የሚያስታውሱ መሆኑን እና አለመሆኑን ጠይቋቸው ምስክሩ እንደማያስታውሱ ተናግረዋል። ጠበቆች በድጋሚ ጥያቄ ከአቶ ጉርሜሳ ጋር ከሰላምታ ውጪ የተለየ ነገር ቢያወሩ ሊያስታውሱ ይችሉ ነበረ ወይ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎ አስታውስ ነበር የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄ፤ ግራ ዳኛ ሆነው የተሰየሙት አቶ ግርማ ደባሱ በ2008 በኦሮሚያ እና ሌሎች የሃገራችን ክፍሎች ተከስቶ የነበረውን ነገር ያስታውሱ እንደሆን ጠይቀዋቸው ሁኔታውን እንደሚያስታውሱ የተናገሩት ምስክሩ በወቅቱ ከነበረው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከአቶ ጉርሜሳ ጋር በስልክ ያወሩት ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።
ለእለቱ የቀረቡት ምስክሮች በመጠናቀቃቸው ለቀጣይ ቀጠሮ የሚከተለው ትእዛዝ ተሰጥቷል።
★እስካሁን የተሰሙ የመከላከያ ምስክሮች ቃል በፅሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ እንዲያያዝ
★ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾች የቆጠሯቸው ምስክሮች 1ኛ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ 2ኛ ክቡር አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ 3ኛ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ 4ኛ ዶ/ር አብይ አህመድ እና 5ኛ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የፍርድ ቤቱ ፓስተኛ መጥሪያ እንዲያደርስ፤ 6ኛ አቶ አንዷለም አራጌ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት መጥሪያው እንዲደርሰስ እና በቀጠሮ ቀን እንዲያቀርባቸው
★ሌሎች መጥሪያ ላልወጣላቸው ምስክሮች መጥሪያ እንዲደርስ እና ባሉበት እንዲደርሳቸው
ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ከጥቅምት 27 እስከ 29/2010 ቀጠሮ ተይዟል።
No comments:
Post a Comment