ባለፉት ሃምሳ አመታት በተወሰኑ ኃይሎች ኢትዮጵያዊነትን ማንቋሸሽ ወይም ኢትዮጵያዊነትን መካድ እንደ ተራማጅነትና እንደነፃነት ወይም እንደ ፀረ ጭቆና ትግል የተቆጠረ ይመስላል፡፡ ይህ ግልብና ጥራዝ ነጠቅ አመለካከት በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን ጉልበትና ኃይል አግኝቶ ኢትዮጵያን ማፍረስ ህገ መንግስታዊ እውቅና ተሰጥቶት የማፍረስ መብት ከጭቆና የመላቀቅ አማራጭ ተደርጓል፡፡ በመሰረቱ ግን ይህ የጥራዝነጠቅነትና የቅኝ ገዥዎች ከፋፍለህ ግዛው አስተሳሰብን በጥሞና ለተመለከተው ፀረ ጭቆና ትግል ከሀገርና ከዜግነት ጋር ምንም ዓይነት የሀሳብ ዝምድና የለውም፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ዘዴውና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ከጭቆና እና ከአገዛዝ የተላቀቀንበት ታሪክ የለንም፡፡ በንጉሳዊ ስርዓት፣ በደርግ ወይም በወታደራዊ አገዛዝ፣ በህወሓት/ኢህአዴግ "የብሔር ብሔረሰብ" አገዛዝ ያለፍናቸውን የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ብንመለከት የጭቆናው ዘዴና ስልት ይለያይ እንጂ በሶስቱም ስርዓቶች ኢትዮጵያውያን ከጭቆና ተላቀን የሀገራችንና የስልጣን ባለቤት ሁነን ወደ እድገትና ብልፅግና አልተራመድንም፡፡ የሀገራችንና የስልጣን ባለቤትም አልሆንም፡፡ ጨቋኞች ይቀያየሩ እንጂ ሁሉም አገዛዞች ለኢትዮጵያውያን የመከራና የግፍ ዘመን ናቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት የምናደርገው ትግል ለአገዛዝ ለውጥ ወይም ከጅብ ዋሻ ወደ ጅብ ዋሻ ለመሄድ ሳይሆን በምንም መልኩ የሚፈፀምን ጭቆና እና ኢፍትሐዊነት በማስወገድ በኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሩና የስልጣን ባለቤት ሆኖ የሚፈልገውን የሚሾምበት እና የማይፈልገውን የሚሽርበት ህጋዊ ስርዓት በሀገራችን መትከል ነው፡፡
የእኛ የኢትዮጵያውያን ችግራችን ኢትዮጵያዊ መሆናችን ወይም ኢትዮጵያ ሀገራችን አይደለችም፡፡ ትልቁና ዋናው ችግራችን በኢትዮጵያ ምድር በማንኛውም መልኩ የሚፈፀምን ጭቆና አስወግደን የህዝብ አስተዳደር ማስፈን አለመቻላችን ነው፡፡ ከላይ እንደገለፅነው በሶስቱም አገዛዞች የጭቆና ዓይነቶች ይለያዩ እንጂ በጨቋኞች ስር መሆናችን የተረጋገጠ ሀቅ ነው፡፡ የጭቆናው ዓይነት የባህል፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የአስተዳደር መጓደል፣ የፍትህ እጦት በአጠቃላይ የዜጎች በግለሰብና በቡድን የሚጋሯቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መብቶች መነጠቅ እንደ አገዛዙ የመጨቆኛ ዘዴ ይለያይ እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ የተሸከምነው እስካሁንም የተጫነብን መከራ ነው፡፡ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን የጭቆና ዓይነቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታግለን በኢትዮጵያ ህዝባዊ አስተዳደር ከተከልን የማይፈታ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄ አይኖርም፡፡
እነዚህ የጭቆና ዓይነቶችና ዘዴዎች ከሀገረ ኢትዮጵያ ጋር ወይም ከኢትዮጵያዊ ዜግነት ጋር የሚያገናኘው ምንም ዓይነት ክር የለም፡፡ ሀገር ወይም ዜግነት ጭቆናን ከሚፈፅሙ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ጋር የአስተሳሰብ ቁርኝት የላቸውም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን ማጥፋት ጭቆናን ማጥፋት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን መካድም ከጭቆና መላቀቅ አይደለም፡፡ ጨቋኘነትና ዜግነት የተግባር ዝምድና የላቸውም፡፡
ይህንን ከላይ የጠቀስነውን መሰረታዊ ሀቅ በምሳሌ ለመረዳት የሩቅ ታሪክ መጥቀስም ሆነ ርቆ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ኤርትራውያን ኢትዮጵያዊነትን ሲክዱ ከጨቋኝና ከጭቆና አላመለጡም፡፡ ሱዳኖች ለሁለት ሲከፈሉ ከጭቆና፣ ከጦርነት እና ከእርዛት አላመለጡም፡፡ ሶማሌዎች ሲበታተኑ ከጭቆናና ከግፍ አገዛዝ አላመለጡም፡፡
ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን የግለሰብም ሆነ በወል የምንጋራቸው መብቶች ተከብረው ወደ እድገትና ብልፅግና እንድንገሰግስ ዋናው የትግል አትኩሮታችን መሆን ያለበት ጭቆናን ከኢትዮጵያ ማስወገድ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የሰውነትና የዜግነት መብት ከተከበረ የማይከበር የመብት ዓይነት የለም፡፡ በሰውነታችን እና በዜግነታችን ውስጥ ኃይማኖታችን፣ ፆታችን፣ባህላችን፣ ቋንቋችን፣ ሙያችን አብረውን አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ህዝባዊ አስተዳደር ከተከልን የማንሻገረውና የማንፈታው የፖለቲካ እና የፍትህ ጥያቄ አይኖርም፡፡
ለማጠቃለል የእኛ የኢትዮጵያውያን የችግራችን መሰረት ኢትዮጵያ ሀገራችን ወይም ዜግነታችን ሳይሆን ጭቆናን ከሀገራችን አለማስወገዳችን ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን ማፍረስ ወይም ኢትዮጵያዊነትን መካድ ከጭቆና እንደማያላቅቅ ተረድተን ጭቆናን የማስወገድና በምትኩ በሀገራችን ህዝባዊ አስተዳደር መትከል የሁላችንም የዜግነት ግዴታ መሆኑን ተገንዝበን የሁሉም ችግሮቻችን ምንጭ የሆነውን አገዛዝ በማስወገድ ዴሚክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚደረገው ትግል ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment