Wednesday, August 30, 2017

እንዴት ሰነበታችኹ ወገኖች? MaMa - ማማ - በማስረሻ ማሞ

እንዴት ሰነበታችኹ ወገኖች? 
እርግጥ ነው በቀቢጸ ተስፋና ድንግዝግዝ ባለ ኑሮ ውስጥ የሚላወስን ኅብረተሰብ ‘እንዴት ሰነበትህ ብሎ መጠየቅ ብቻውን አመርቂ አይደለም። ጫዎታና ወግ የሚያምረው ለመሰንበት ቅድሚያ በመስጠት ነውና፦እንዴት ውላችሁ አደራችሁ? እላችኋለኹ በድጋሚ።
በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነገር የነበረው የነሐሴ አክራሞት ሁላችኹም እንዳያችኹት በ“ቀቢጸ ተስፋ”ና “በድንግዝግዝ” የተዋጠ ኾኗል። መጪውን ዘመን የጨገገ አስመስሎም እያሳየን ነው።
የአትሌቲክስ ፖለቲካ - የመንፈስ ፖለቲካና የወሰን ግጭት በብሔርተኝትና በማንነት ፈረሶች ላይ እየጋለቡ ነው።
ጥያቄው በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ “ጭጋጉን” የምናሳልፈው እንዴት ነው? የሚለው ነው።
ዛሬ ወደ እናንተ የመጣኹት እንደ አንድ ግለሰብ የሚሰማኝን ነገር ለማካፈል በሚል ነው።
ያገር ቤት ናፍቆት ውስጥ ውስጡን እንደሚቦረቡረው እንደ ብዙው ተሰዳጅ ኢትዮጵያዊ ወደ አገር ቤት አልፎ አልፎ ስልክ እደውላለኹ። ከምጠይቃቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ታዲያ፦ “እንዲያው የሰፈሬ ሰው ሠላምና ፍቅር እንዴት ነው”? የሚለው ነው። በተደጋጋሚ የሚሰጠኝ መልስ ግን አስተካዥ ነው። 
“አይ አንተ የምታውቀው ሠላምና ፍቅር አሁን የለም፤ ጎረቤት ከጎረቤት ጋራ መነጋገር ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል። የተኮራረፈው ይበዛል።” ይሉኛል።
እኔን እንደ አባትም እንደ እናትም ኾነው ያሳደጉኝ ጎረቤቶቼ አይነጋገሩም። በሌላ አነጋገር ከአምስት ቤተሰቦች የተውጣጣ 20 ቤተሰብ በጋራ ተቀምጦ ችቦ አያበራም፤ “ሕዳር ሕዳር - ትወዳለች ማር” ብሎ በየዓመቱ ንፍሮ እየቃመ አይዘፍንም። “አድባር አንቻዬ አንድ ገንቦ ጠላ ለብቻዬ” እያለ የእንቁጢጥ አይጨፍርም።
እንግዲህ በሕይወት እያለሁ የልጅነት ታሪኬ ወደ ተረትነት ኮታ ሲጣል እንዴት አልተክዝ!?
“ለመኾኑ ሽማግሌ የለም በሰፈሩ?” . . . ስላቸው
“ሁሉም ከተጣላ እንዴት ብሎ ሽማግሌ ይኖራል?” ይሉኛል።
ለዚህ ጥያቄ የሚኾን መልስ ለማግኘት ከሰፈሬ ዘበት ወጣ ብዬ ወደ ድሮ ታሪክ ልውሰዳችኹ፡- ታሪኩ ከሽምግልና ጋራ የተያያዘ ነው። በዳግማዊ ሚኒልክ ዘመን የተፈጸመ ታሪክ ነው። ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) በዚህ በኛ ዘመን ቋንቋ - በኾነ ነገር “ይደብራቸውና” ሥራቸውን አስታጉለው ከቤተ መንግሥት ይቀራሉ። 
ዳግማዊ ምኒልክ፦ “ይኼ ሰው ምን ኾኗል ሂዱና ጥሩት እስኪ” ብለው ሰው ይልካሉ። አባ መላ “እምቢ” ይላሉ። ምኒልክ ደግመው ሌላ መልክተኛ ይሰዳሉ። አሁንም አባ መላ “አኩርፊያለሁ፤ አኩርፊያለሁ፤ አልመጣም” ይላሉ። መል’ክተኞቹ መል’ክቱን ይዘው ወደ ምኒልክ ይመለሳሉ። 
“ምን አላችሁ?” አሉ ምኒልክ። 
“አልመጣም አሉን” አሉ መልክተኞቹ። 
“ተውት በቃ እኔ እሄዳለሁ።” ብለው ሚኒልክ ወደ ሀብተጊዮርጊስ ቤት ያቀናሉ። 
ምኒልክ “አንተ ሰው አኩርፈኸኛል መሰል” ብለው በሩን ከመሻገራቸው - ሀብተጊዮርጊስ ከመቀመጫቸው ተነስተው ኩርፊያቸውን አሽቀንጥረው ይጥላሉ።Bilderesultat for ESAT Mama Aug 30 , 2017
ከዚህ ታሪክ የምናተርፈው ነገር፦ “ሁለት የተጣሉ ሰዎች የሚያስታርቃቸው ሽማግሌ ያጡ እንደኾነ፤ አቤቱታ የቀረበበት ሰው ሽማግሌ ኾኖ ወደተበደለው ቤት ሄዶ ነገር ያብርድ የሚል ነው።”

ኩርፊያ - መበደላችንን፣ መጠቃታችንን፣ ደስ አለመሰኘታችንን የምንገለጥበት መንገድ ነው። የምናኮርፈው ለራሳችን ቀይ መስመር ብለን ያሠመርናቸው መስመሮች ሲጣሱብን ነው። ኩርፊያ ውስጥ የመበደል ጥያቄ አለ። ነገር ግን በማኩረፍ ሰንሰለት ተጠፍንጎ ታስሯል። እያንዳንዳችን ራሳችንን ከኩርፊያ ነጻ ካላወጣነው ሰንሰለቱን መበጠስ አይቻለንም። መጠገን ያለበት ኅብረተሰባዊ መሰንጠቀ ላይ ቆመን ነው የምናወራው።
ይኼ የመሰነጣጠቅ አደጋ - ያለመደማመጥና ሁሉም በፊናው በከፍተኛ ፍጥነት የመግለብልብ ችግር የጎረቤቶቼ ዕጣ ፈንታ ብቻ አይደለም፤ የአጠቃላዩ ማኅበረሰብ ዕድልፈንታ ኾኖም እያየነው ነው። በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ሰፈር።
በእኛ ዘንድ ለማኅበራዊ ሚዲያው ያለን አመለካክት ራሱ ይገርማል። “መንግሥት” ወኪሉን ኀይለማርያም ደሳለኝን ኒውዮርክ ድረስ ልኮ “ማኅበራዊ ሚዲያው ያስፈራኛል፤ መላ በሉኝ እባካችሁ” ማለቱን እናስታውሳለን። አቶ መለስ ደግሞ ባንድ ወቅት የቅንጅትን መፍረስ ካረጋገጡ በኋላ ለሕዝቡ ‘ጠላታችን ድህነት ነው” ብለው፤ በውስጥ ለጓዶቻቸው “የሚቀጥለው ጦርነት የሚዲያ ነው” ብለዋቸው ነበር። እውነታቸውን ነው፤ ጦርነቱ በሚዲያው በኩል ነው የሚጧጧፈው።
አቶ መለስ ይኼን ፍልሚያ ለማሸነፍ የተከተሉት ስትራቴጂ መበታተን ላይ ያተኮረ ነበር፤ እስካሁንም ነው። የሚዲያ ጦርነቱን ለማሸነፍ መጀመርያ መበታተን፤ ቀጥሎ ማሠር፣ ከዚያ ማሰደድ፣ ገልብጦ መግረፍ፤ “ሽብርተኛ” በሚል መጤ ወንጀል መፈረጅ ነው። ይኼን ሁሉ አድርጎም - የኢትዮጵያ መንግሥት የማኅበራዊ ሚዲያውን ይፈራዋል፤ በተቃራኒው የማኅበራዊ ሚዲያው እንደ ጎረቤቶቼ በኩርፊያ በር ዘግቶ ይጮኻል። ግማሹ የኢትዮጵያ መንፈስ የሚባል ፈረስ ይጋልባል፤ ግማሹ የኦሮሙማ መንፈስ የሚባል ፈረስ ይጋልባል፤ ሌላው የአጋዝያን መንፈስ ጋላቢ ነኝ ይላል። ብሔርተኝትና ማንነት ኩርፊያ ውስጥ ኾነው ሊጨበጥና ሊዳሰስ ወደማይችል “መንፈስነት” እየተቀየሩ መጪውን ዘመን ጭግግ ያደርጉታል።
ያው ሁላችኹም እንደምታውቁት አብዛኞቻችን ዓላማችንን የምንናገረው ኩርፊያ ውስጥ ተወሽቀን ነው። መጀመርያ እስኪ ዓላማዎቻችንን ትክ ብለን እንመልከታቸው? ብሔርተኝነትና ማንነት አይደሉምን? እንግዲያስ ብሔርተኝንትና ማንነት እምነት አይደሉምን? እንዲያስ ከኾኑ የግልና የራስ ብቻስ አይደሉምን? ዓላማችንን ለማሳካት የምንወጣበትና የተንጠለጠልንበት መሰላል ቆመንለታል የምንለው ኅብረተሰብስ አይደለምን? ዓላማችንን ለማስፈጸም ስንል የወጣንበትን መሰላል ስንመለስ ብናጣው ምን ይውጠናል?
የአንድ አክቲቪስት፣ የአንድ ጋዜጠኛ፣ የአንድ ጸሐፊ፣ ወይም የአንድ የፖለቲካ መሪ ወይም ደግሞ እንደኔ ያለው ጎርፍ አመጣሽ ተናጋሪ የምንከተለው ግላዊ የፖለቲካዊ ዓላማ ለአንድ አገራዊ ኅብረተሰብ የማጣፈጫ ቅመም እንጂ ብቻውን የሠላምና ደኅንነቱ ማረጋገጫ አይኾንም።
በእኔ እምነት አሁን ያለችውና ወደፊት የምትመጣው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ከኩርፊያ ራሱን ነጻ ያወጣና የሽምግልናን እሴት ተግባራዊ የሚያደርግ ትውልድ ነው። ብዙዎቻችን ከላፕቶፓችን ውጪ በአካል የተላበስነውን ጨዋነት ወደ ውጪ እንዲወጣ ለማድረግ አቅም አጥተናል። ከገዛ ራሳችን ጋራ ሱባዔ መግባት አቅቶናል። ከግል ዓላማ በላይ ለሰው ልጆች ሰብእና፣ ለተፈጥሮ ልዕልናና ለአገር ሕልውና የሚበጅ አገራዊ ግብ የሚተልም ትውልድ ነው ያሻናል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ ናት። ኢትዮጵያ መቶ ሚልዮኖች ዜጎች የሚኖሩባት ዜግነት ያልተከበረባት አገር ናት። ኢትዮጵያ ከ80 የሚበልጡ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት አገር ናት። በዚች ኢትዮጵያ በምትባል ተሠርታ ባላለቅች አገር ላይ አንዳንዶቻችን በቋንቋ አኩርፈናል፤ አንዳንዶቻችን በማንነት አኩርፈናል፤ ሌሎቻችን በደልና ጥቃት ከሚያደርሰው ወገን ኾነንም አኩርፈናል።
እኛ እንዲህ በተኮራረፍንበት በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያውያን በሮማ ፖሊሶቸ እንደ ቆሻሻ በውኃ ከመንገድ ላይ ይጠረጋሉ፤ ይታጠባሉ። ኢትዮጵያውያን በዓረብ አገራት ከፎቅ ላይ ይወረወራሉ፣ ይደፈራሉ፣ ይገደላሉ፤ ወደ አገራቸው ከመመለስ ይልቅ በዚህ ስቃይ ውስጥ ማለፍን ይመርጣሉ። የመረጡት ስቃይ የሚወዱ ስለኾኑ አይደለም። ወደ ባዶ ቤት መመለስ ስለሚያስፈራቸው ነው።
ኢትዮጵያውያን በየመን የዓሳ ነባሪ ቁርስ ናቸው። ኢትዮጵያውያን በሊቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሲዖልን ሽታ የሚምጉ ናቸው። ከእስር ቤት የማምለጥ ዕድል ያገኙትን ኢትዮጵያውያን ደግሞ የሜዲትራኒያን ባህር ይውጣቸዋል። ኢትዮጵያውያን በቀይ ባህር ዳርቻ የአይሲስ ራት ኾነዋል። ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ በእሳት ተቃጥለዋል። ኢትዮጵያውያን ሴቶች የጂቡቲን እልፍኝ እንዲያሞቁ ተደርገዋል። ኢትዮጵያውያን ሴቶች በምሥራቅ አፍሪካ ለወሲብ ሽያጭ እየቀረቡ ነው።
አገር ውስጥ ደግሞ አጥር በማካለል ሰብብ በአንዲት አገር ላይ ክልል ከክልል ጋራ መሣርያ ይማዘዛል። ነገሩን አሰገራሚም አሰደናቂም የሚያደርገው ይኼ የአጥር ጠብና ግጭት የተፈጠረው ከ25 ዓመት በላይ አብረው በሠሩ የአንድ ፓርቲ ሰዎች መካከል መኾኑ ነው።
በኢሬቻ በዐል ላይ የሞቱት ሰዎች የሞቱበትን ምክንያትና ለሞታቸው ምክንያት የኾኑት ሰዎች እነማን እንደኾኑ ሳይነገር - ተሽቀዳድሞ ሐውልት መገንባት ከአፍሪካ ሥልጣኔ ጋራ መላጋት ነው። የየጢያ ትክል ድንጋይ ያንን አይነገረንም፣ የአክሱም ሐውልት ያንን አያሳየንም፣ የሜሩ እና የግብጽ ፒራሚዶች እንደዚህ አልተቀረጹም። ለመኾኑ በግጭቱ ምን ያህል ሰው ሞተ? ምን ያህሉስ ከቀየው ተፈናቀለ? ይኼ ግጭት በዚሁ ከቀጠለ የሚጓዘው ወደየት ነው? አሜሪካ የባርያ ፈንጋዩን የጄነራል ሮበርት ኤድዋርድ ሊን ሐውልት በማፍረስ ቨርጂኒያ ላይ በምትወዛገብበት ሰዓት ኦሕዴዶች ፍርድ ዐልባ ሐውልት ያቆማሉ።
ዘረኝነትና የበላይነት በዓለም ላይ የተጋረጡ የሰው ልጆች የሕልውና አደጋዎች ናቸው። የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከተሰጠው ሚና አልፎ አምላክ የመኾን ፍላጎቱን ለማሟላት ሲል ዘረኝነትንና የበላይነትን ፈጠረ። ዘረኝነት የተፈጠረው በሰው ልጅ አዕምሮ ነው። ስለዚህ መፍትሄውም ያለው በሰው እጅ ውስጥ ነው። መፍትሄው ሥልጡን መኾን ነው። የሠለጠነ ሰውና ሥልጡን ማኅበረሰብ መፍጠር ነው።
የሥልጣኔ ነገር ከተነሳ ስለ ፓሪስ ጉዞዬ ትንሽ ላውጋችሁ። ብዙ ጸሐፍትና ብዙ ሰዎች “የምዕራባውያን ሥልጣኔ” ሲሉ እሰማለሁ፤ አነባለሁ። ይኼ ስያሜ ባስመዘገቡት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲለካ አብሯቸው የሚሄድ አይመስለኝም። እኔ ብዙ ጊዜ ብጠቀም የምመርጠው “የምዕራባውያን ዝማኔ” የሚለውን ነው። የዘንድሮውን ዓመታዊ እረፍት ለማሳለፍ ከነ ቤተሰቦቼ ወደ ፓሪስ ሄጄ ነበር። ዕቅዳችን ኤፍል ታወርንና በዓለም እጅግ ትልቁ የሚባለውን ሎውቨ ሙዚየምን መጎብኘት ነበር። ሰፊውን ሙዚየም “በወፍ በረር” ወደ ስምንት ሰዓት ያህል ፈጀብን።
ፓሪስ መሀል ላይ ያለው ይኼው ግዙፍ ሙዚየም ከመግቢያ በሩ ላይ የአፍሪካ ሥልጣኔ የኾነውን ፒራሚድ (የግብጽ ነገሥታት የመቃብር ሐውልት) በመስታወትና በብረት ተሠርቶ ጉብ ብሏል። ብዙ ሰው ከፒራሚዱ ጋራ ፎቶ ይነሳል። ፓሪስም የራሷ ያልኾነን ሥልጣኔ በመሸጥ ትተዳደራለች። ከሎውቨ’ ሙዚየም የውስጠኛ ክፍል ኾናችሁ ወደ ውጪ ስትመለከቱ ሌላኛው የመስታወት ፒራሚድ - መሬት ላይ በተነጠፉ ፒራሚዶች ተውቧል። የአትክልት ስፍራው በሙሉ በሦስት ማዕዘን ተግጥግጧል። የአፍሪካ ሥልጣኔ ከላይና ከታች በመስታወት ተቀምጧል።
ብዙ ጊዜ ምዕራባውያን “ሥልጣኔያችሁ ከየት ነው የሚቀዳው” ሲባሉ ግሪክን ይጠቅሳሉ። የግሪክ ታላላቅ ፈላስፎችና ጸሐፍት ግን ሥልጣኔን የቀዱት ከግብጽ እንደኾነ ይናገራሉ። ፓይታጎረስ የሚባል ግሪካዊ ነጋዴና የሂሳብ ሰው “ፓይታጎረስ ቲረም”ን ለግሪክ ያስተዋወቀው ግብጽን ከጎበኘ በኋላ ነበር። ለግብጾች ሥልጣኔ የዐባይ ወንዝ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተላቸውም ፓይታጎረስ ጽፏል። የአባይ ወንዝ ሥልጣኔ የአፍሪካ ሥልጣኔ ነው። ፓይታጎረስ እውነቱን ተናግሯል፤ ያገኘውን እውቀት ተጠቅሞበት ባለቤትነቱ ግን የእርሱ እንዳልኾነ አስቀምጧል።
ይኹንና ከሦስት ሺሕ ዓመታት በፊት በዐባይ ወንዝ አካባቢ የሚኖሩት የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች ብዙ አማልክት ነበሩዋቸው። እያንዳንዱ አማልክት የሕዋውን ሚዛን ለመጠበቅ የራሱን ተግባርና ኀላፊነት ይወጣል። በዘመኑ የነበሩት ጠቢባንም አማልክቶችን በሥዕልና በቅርጻቅርጽ ሥነ ጥብበ የአዞ መልክ ያለው፣ የጎማሬ መልክ ያለውና የተለያየ የእንስሳት መልክ ያላቸው አድርገው ስለዋቸዋል። አብዛኞቹ የግማሽ ሰው ግማሽ እንስሳ መልክ የተላበሱ ናቸው።
እንደ ምሣሌ ለመጥቀስ ከብዙዎቹ አማልክት አንዷ አይሲስ ትባላለች። በዚያ ዘምን ትመለክ የነበረችው አይሲስ ከዚህ ዘመኑ አይሲስ ጋራ ፈጽሞ ተቃራኒ ነች። አይሲስ የአምላክ እናት በመባልም ትታወቃለች። አይሲስ ለግብጾች የልባም ሚስት፣ የእናትነት፣ የፍቅር፣ የመሰጠትና የክብካቤ ምልክትም ነበረች። በጥንታውያን ግብጾች በአማልክቶቹ የሚገለጸው የሰው ልጅ ምኞትና ፍላጎት በአንድ አምላክ ጠቅላይ ገዢነት አይገለጥም። አምላክነት ከተፈጠሮ ጋራ የተያያዘና የተቆራኘ ተደርጎ ይወሰድም ነበር።
የፓሪስ ጉብኝቴ አሁን ዓለም ያለችበትን የዘር፣ የቋንቋና የቀለም ምስቅልቅል ወደኋላ ተመልሼ በመሃይም አንደበቴ እንዲህ እንድጠይቅ አድርጎኛል። ሁለት ሺሕና ሦስት ሺሕ ዓመታት ወደ ኋላ መጓዝ ሳይስፈልገን የሰው ልጅ ወደ አመክንዮ ተሻግሬያለሁ ባለበት በዚህ በ20ኛውና በ21ኛ ከፍለዘመን 160 ሚልዮን ሕዝብ ለጦርነት ገብሯል። አብዛኞቹ ጦርነቶች የተካሄዱት በሃይማኖት፣ በብሔርተኝትንና በማንነትን ጥላ ስር ተሸጉጠው ነው።
በዓለማችን ላይ ያሉት ጥፋቶችና ውድመቶች በአብዛኛ ሰው ሰራሽ ናቸው። ሐኪማቸውም ሰው ብቻ ነው። የሰው ልጅ በዚህ ሕልቆ መሳፍርት በኾነ ግዙፍ ተፈጥሮ ውስጥ ሚናው ኢምንት ነው። የአምላክነትን ሚና ለብቻው ሊያስወስደው የሚያስችል የተለይ ብቃት የለውም። ተፈጥሯዊ የሚባሉት አደጋዎች ራሳቸው የሰው ልጅ ለማይጠረቃ ስሜቱና ፍላጎቱ ሲል የሚፈጥራቸው ችግሮች ናቸው።
ውድ የማማ ታዳሚዎች፦ በኢትዮጵያ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መታፈን - ብዙዎቻችንን ያለ ተቆጣጣሪ በረኛ ወደ አደባባይ እንድንወጣ አድርጎናል። የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፍጥነትና ግስጋሴ ብዙዎቻችንን ትንፋሽ የሚያሳጣ ሩጫ እያስሮጠን ነው። ሁሉን መዘገብና ስለ ሁሉ ነገር አስተያየት መስጠት ያለብን እየመሰለንም - ያለ አግባብ ባክነናል። በምናየው የየዕለት ሐዘንና ሰቆቃ - ተስፋቢስነት ተጠናውቶናል። ከዚህ መሰሉ ጭጋግ ለማምለጥ ኩርፊያችንን ማሸነፍ ይጠበቅብናል። ወደ አደባባይ እየወጣ ለሚያስቸግረን የበላይነትና የልዩነት ስሜት ጠባቂ በረኛ ልናቆም ይገባናል።

የምናደርገውን ሁሉ ስለ ሰላምና ፍቅር ስንል እናድርገው። 
ቸር ሰንብቱ።፡

@MaMa - ማማ - በማስረሻ ማሞ

No comments:

Post a Comment