Sunday, August 13, 2017

የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃት/ኢህአዴግን እንደማይፈልግ በህይወት መስዋዕትነት አረጋግጧል ስለሆነም የትግል አጀንዳችን፡ "ሕወሃት/ኢህአዴግ ይውረድ፤ የባለአደራ መንግስት ይቋቋም!!!! የሚል መሆን አለበት!!


(ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተላለፈ የትግል ጥሪ)
የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሩና የስልጣን ባለቤት ሆኖ የሚፈልገውን ለመሾምና ያልፈለገውን ለመሻር የሚያስችል ህጋዊ ስርዓት እንዲመሰረት ባለፉት አመታት እጅግ መራራ ትግል አድርጓል፡፡ የትግሉ ደረጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሂዶ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት ከተለመደው ውጭ የማንንም የተደራጀ ሀይል አመራር ሳይጠብቁ እንደ አካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በማንገብ ከታጠቀው አገዛዝ ጋር ባዶ እጃቸውን በራሳቸው ፈቃድ ተጋፍጠዋል፡፡ በቆራጥነት በተከፈለው የህይወት መስዋዕትነት በብዙ ኢትዮጵያውያን ላይ በተፈጠረው ቁጭትና እልህ የትግሉ አድማስ እየሰፋ ሀገራዊ ቅርፅ እየያዘ መጥቷል፡፡ ትግሉ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ከፍተኛውን የህይወት መስዋዕትነት ዋጋ ከፍለዋል፡፡Image may contain: 2 people, people standing
ሁላችንም እንደምንገነዘበው አሁን በላያችን ላይ የተጫነው አገዛዝ ለስልጣኑ ህልውና መሰረት አድርጎ የያዘው ስልት የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶችን ማጥፋትና በልዩነት ላይ የተመሰረተ ጥላቻን እና አለመተማመንን መሰረት ያደረገ የከፋፍለህ ግዛው የአገዛዝ ዘይቤ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በጋራ የምንጋራቸውን ማለትም ሀይማኖትን እና ሀይማኖተኝነትን አዋርዷል፤እውቀትና አዋቂዎች ክብር እንዲያጡ አድርጓል፤ሽምግልና እና ሽማግሌዎችን በኢትዮጵያ ማህበራዊ አደረጃጀት ላይ ያላቸውን ሚና እንዲያጡ አድርጓል፤የኢትዮጵያ ልጆች ቋንቋ፣ባህል፣እምነት የመጡበት አካባቢ ሳይለያያቸው በአንድ ጉድጓድ እየተቀበሩ የገነቡትን ብሔራዊ ክብርና የሃገር ሉዓላዊነት መንፈስ አዳክሟል፤በኢትዮጵያ ውስጥ እሱ የማይቆጣጠረው የሙያና የሲቪክ ማህበር እንዲኖር ባለመፈለጉ ሀገሪቱን በሁሉም ዘርፍ ምድረ በዳ እና የተቋም ደሃ አድርጓታል፡፡ 
ይህም አሁን ያለው አገዛዝ የሚከተለው የአገዛዝ ዘይቤ ጣሊያን ሀገራችንን ቅኝ ለመግዛት በሞከረበት አምስት የመከራ አመታት ውስጥ ሲተገብረው የነበረ ጨቁኖ የመግዛት ስልት ነው፡፡ ጣሊያን በዛን ዘመን በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ጥላቻና መናናቅ እንዲፈጠር በትጋት ሰርቷል፡፡ ይከተለው የነበረው የአስተዳደር ክልልም አሁን ባለው አይነት የከፋፍለህ ግዛው ዘይቤ የተዋቀረ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የነበሩ መልካም እሴቶችን በማጥፋት እና በማንቋሸሽ ረገድ አሁን ካለው አገዛዝ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ህዝብ ያዳምጣቸዋል እና ይከተላቸዋል የሚላቸውን ብርቅዬ ኢትዮጵያውያንን በማሳደድና በመግደል አሁን ካለው አገዛዝ ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ፋሽስት ጣሊያን በአንድ ቀን ሌሊት በደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚኖሩ ከ350 በላይ ኢትዮጵያውያንን መረሸኑ የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ አሁን ያለው አገዛዝም የህዝብ ጥያቄ አንግበው ባዶ እጃቸውን የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ገድሏል፡፡ 
በእንደዚህ ያለው የጋራ እሴቶችን አውድሞ፣የህዝብ ምሳሌዎችን ገሎ በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ የከፋፍለህ ግዛው አገዛዝ ዘመን ጠንካራ መሪ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ማፍራት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ቢፈጠሩም ተከታትሎ ያጠፋቸዋል፣ይገድላቸዋል፡፡ በዚህ አገዛዝ የተገደሉ ታጋዮችን፣በየእስር ቤቱ የታጎሩ የፖለቲካ መሪዎችን እና ተመስርተው የፈረሱ ድርጅቶችን ብዛት ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ካለው አገዛዝ ተላቅቆ በሀገራችን ህዝባዊ አስተዳደር እውን እንዲሆን መከተል ያለበት የትግል ስልት ከማንም የተደራጀ የፖለቲካ ሀይል አመራር በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ቀደምት አባቶቻችን ከጣሊያን የቅኝ ግዛት ሙከራ ያለንጉስና ያለማዕከላዊ አመራር ነፃነታቸውን እንደተቀዳጁ ሁሉ እኛም በዚህ ዘመን የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ትግሉን እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በማስተባበር በሚደረግ ሰላማዊ የትግል ስልት ነው፡፡ በዚህ እረገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተደረገው ትግል እጅግ የሚያበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡አሁንም ከገቢ ግብር ጋር ተያይዞ በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ህዝቡ የማንንም የተደራጀ ሀይል መሪነት ሳይጠብቅ እያደረገ ያለው ተቃውሞ ወደ ነፃነት መቃረባችንን እና ዜጎች ትግሉን የራሳቸው አድርገው መያዛቸውን የሚያሳይ ግልፅ ምሳሌ ነው፡፡Image may contain: 15 people, people sitting and indoor
በመጨረሻም አሁን በኢትዮጵያችን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ለሚደረገው መራራ ትግል መከተል ያለብን የትግል ስልት ትግላችን በግለሰብ ወይም በድርጅት ብቻ የተንጠለጠለ ሳይሆን ዓላማ ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ንቅናቄ መሆን አለበት፡፡ ዓላማችንም እስካሁን በየአካባቢው ለምናነሳቸው ጥያቄዎች መንስኤ የሆነው የሕዝብን ጥያቄ ሊመልስ ያልቻለው ሕወሃት/ኢሕአዴግ ወርዶ 'በኢትዮጵያ ባለአደራ መንግስት ይቋቋም' የሚል መሆን አለበት፡፡ ይህንን ካላደረግን ግን አሁን ያለው አገዛዝ በሚከተለው አጥፍተህ ጥፋ እና የአውዳሚነት ፖለቲካ ሀገራችን ከምትገኝበት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እድገት ደረጃ ጋር ተያይዞ የብተና አደጋ አስፈሪው እጣ ፈንታችን ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከተጋረጠብን የብተና አደጋ ለመዳንና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ህዝቡ እያደረገ ያለውን አጠቃላይ ንቅናቄ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች ትልቁ ሀገራዊ አጀንዳ ላይ በማተኮር ለሚደረገው ህዝባዊ ንቅናቄ የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ 
ነሐሴ 07 ቀን 2009 ዓ.ም. 
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment