(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)
**************************
ባለፈው አመት ነሃሴ1 ቀን 2008 ዓም በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ በተሳተፉ የባህርዳር ወጣቶች ላይ የተወሰደውን እርምጃ በማውገዝና ሰማአታቱን ለመዘከር የተጠራው የስራ ማቆም አድማ መላው የከተማውን ህዝብ ባሳተፈ ሁኔታ ተግባራዊ ሆኗል። እርምጃው ከተማውም ሆነ ክልሉ ከብአዴን እጅ ወጥቶ የለውጥ ጥያቄ ባነገቡ ሃይሎች እየተመራ መሆኑን የሚያሳይ ነው በማለት ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሰማዓታቱን ቀን ከመዘከሪያው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ከተማዋን ወረዋት ነበር። የደህንነት ሃይሎች፣ በከተማው ፍንዳታ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍንጭ አግኝተው የነበረ ቢሆንም፣ የት እና እንዴት ሊካሄድ ይችላል የሚለውን ባለማወቃቸው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች የማሰማራትና የቁጥጥር ስራ የመስራት አማራጮችን በመውሰድ በተለያዩ አካባቢዎች ጥበቃ ሲካሂዱ ውለዋል። የቦንብ ፍንዳታው ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ የተካሄደ ሲሆን፣ ፍንዳታውን ተከትሎ የደህንነት ሃይሎች ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተው፣ ተጠርጣሪ ወጣቶችን እንዲይዙ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ከሁሉም በላይ ነሃሴ 1 ቀን የሚካሄደውን የሰማዓታቱን ዝክር እንዲያስቀሩ ማንኛውንም ጥረት እንዲያደርጉ ታዘዋል። አንዳንድ የደህንነት አባላት ስብሰባው የተጠራበትን ሰአት በማስታወስ ፣ አድማውን ከእንግዲህ ማስቆም አይቻልም በማለት ለአዛዦች ግልጽ አድርገው ተናግረዋል። አድማው የሚካሄድ ከሆነ፣ “ለብአዴን/ኢህአዴግ ትልቅ ውድቀት ነው፣ ይህ አድማ በማንኛውም መንገድ መካሄድ እንደሌለበት መጠቀም ያለባችሁን ሁሉ ማስፈራሪያ እና መውሰድ ያለባችሁን ሁሉ እርምጃ ውሰዱ” የተባሉት የከተማዋ የደህንነት አባላት፣ ጠዋት ላይ ዋና ዋና ወደ ሚሏቸው የከተማ ሰዎች ስልክ እየደወሉ በአድማው እንዳይሳተፉ ሲያስጠነቅቁ አርፍደዋል። የራሳቸውን ደጋፊዎች የታክሲ አሽከርካሪዎች በማሰማራት አድማ የሌለ ለማስመሰል ሞክረዋል።
ይሁን እንጅ ከውስጥ ሆነው አድማውን የሚደግፉና ከአስተባባሪዎች ጀርባ ሆነው ድጋፍ የሚሰጡ የደህንነት ሰራተኞች ለወጣቶቹ ጥቆማ በመስጠት አንዳንድ አስተባባሪዎች እንዳይያዙ ከለላ የሰጡ ሲሆን፣ አድማውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆኑ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ባጃጆች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ድጋፍ ሰጥተዋል።
የደህንነት ሃይሎች ማስፈራሪያ ወደ ጎን በማለት የባህርዳር ከተማ ህዝብ ጥሪውን በመቀበል አድማውን የንግድ ድርጅቶች በመዝጋት ተግባራዊ ሲያደርግ ውሎአል።
አድማው እየተካሄደ ባለበት ወቅት የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በባህር ዳሩ የርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ውስጥ ዝግ ስብሰባ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ምንጮች በተገኘው መረጃ መሰረት ስብሰባው በድንገት የተጠራ ነው፡፡ስብሰባው አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በከተማዋ የሚገኙ የቢሮ ሃላፊዎች በሙሉ የስብሰባው ታዳሚዎች ሆነዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው “ አድማው የነጻነት ትግሉ የሚቀጥል መሆኑን ማሳያ ነው” ይላሉ። “የባህርዳር ህዝብ የተሰውበትን ልጆቹን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን፣ እነሱ ያነሱዋቸውን የነጻነት፣ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄዎች ዳር ሳያደርስ ትግሉን እንደማያቆም በአደባባይ ሳይማማል፣ በሃሳብ ተማምሏል” በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት አንድ መምህር፣ ህዝቡ ያለማንም ግፊት በራሱ ጊዜ ተናቦ ያደረገው አድማ መሆኑን ይገልጻሉ። መመህሩ፣ ህዘቡ ስርዓቱን አልተቀበለውም፣ በከተማው መንግስት በተደጋጋሚ ስብሰባ ይጠራል፤ በስብሰባ ላይ የሚገኘው ህዝብ ግን ቁጥሩ ትንሽ ነው፤ ለውጥ የሚጠይቁ ሃይሎች አድማ ሲጠሩ ህዝቡ ፣ ጉዳት እንደሚያመጣ እያወቀ እንኳን አድማውን ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል። እዛኛው ስብሰባ የታሸገ ውሃ እየጠጣህና ጥሩ ምግብ እንደምትበላ እያወክህ እንዲሁም ጥሩ ቦታና ስራ እንደምታገኝ እያወክ በስብሰባው ላይ መገኘት አትፈልግም፣ የዚህኛውን ወገን ጥሪ የምትቀበል ከሆነ መታሰር፣ ስራን ማጣት፣ የንግድ ድርጅትን ማዘጋት ግፋ ሲልም ሞት እንዳለ እያወክ በደስታ ጥሪውን ተቀብለህ ተግባራዊ ታደርጋለህ። ታዲያ ህዝቡ በማን እየተገዛ ነው? የማንን ጥሪ እየሰማ ነው። መንግስትና ህዝብ አንድ ሆነው አያውቁም፣ ያውቃሉ እንኳን ቢባል ለመለያየታቸው ከዚህ የበለጠ ማስረጃ የለም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሰማዓታቱን ለመዘከር ጥሪውን ያስተላለፉት ወገኖች በበኩላቸው፣ የከተማው ህዝብ ጥሪውን ሰምቶ ተግባራዊ በማድረጉ አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለቁበትን ትግል ከዳር ሳናደር አርፈን እንደማንቀመጥ የባህርዳር ህዝብ ይወቅልን ብለዋል። ትግሉ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መስፋፋት እንደሚገባውም ምክራቸውን ለግሰዋል።
No comments:
Post a Comment