(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 18/2009
በጅማ ዛሬ የደረሰውና ምናልባትም የመንግስት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የተባለው የቦምብ ጥቃትም በሀገሪቱ ያለውን ያለመረጋጋት ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን መረጃዎቹ አመልክተዋል። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉት የተኩስ ልውውጦችም ሆኑ ያልተረጋጉ ሁኔታዎች በሀገሪቱ ስላለው የጸጥታ ጉዳይ እንዳጤን አድርጎኛል ብሏል የካናዳ መንግስት ባወጣው ሪፖርቱ። በሪፖርቱ እንደተመለከተው በሀረርና በድሬደዋ እንዲሁም በሆለታና አምቦ መንገዶች አዋሳኝ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጦችና ያለመረጋጋት ሁኔታዎች ይታያሉ። የሆለታና አምቦ ከተሞች ደግሞ በኢትዮጵያው ኦሮሚያ ክልል ማእከል ላይ የሚገኙ ከተሞች ሲሆኑ ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ደግሞ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ከተሞች ናቸው።
በነዚህ አካባቢዎች ያለው ያለመረጋጋት ሁኔታ ወደ ዋና ከተማዋ ብሎም ወደሌሎቹ አካባቢዎች ስላለመዛመቱ ርግጠኛ ሆነን መናገር እንችልም ።እናም ሀገራችን ካናዳ ይህን ጉዳይ በትኩረት እያጤነችው ትገኛለች ብሏል ሪፖርቱ። ከዚህም ጋር ታያይዞ ካናዳ ዜጎቿ በኢትዮጵያ ባሉ አጠቃላይ ከተሞችም ጉዞ እንዳያደርጉ እገዳ ጥላላች።ይህን ያደረገቸውም ይላል ሪፖርቱ በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ጉዳይ አስተማማኝ ባለመሆኑ ነው።
ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ መንግስትም በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና በተለይ በምስራቃዊው የኢትዮጵያ ክፍል የተኩስ ለውውጦች እንደሚሰሙ በሪፖርቱ አመልክቶ ነበር። ሪፖርቱ የተኩስ ልውውጡ የሚሰማባቸውን የሀረርና የባቢሌ አካባቢዎች መሆናቸውን ይገልጻል። እነዚህ መንገዶች በቀጥታ ከአዲስ አበባ ጋር የሚገናኙ ዋና መንገዶች የሚያልፍባቸው መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው በሪፖርቱ መገለጹ ይታወሳል። ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የሕወሃት/ኢሃአዴግ መንግስት ግን ሪፖርቱን በማጣጣል በአካባቢው ተሰማ የተባለው ተኩስ ያን ያህል የሚጋነንና ሀገር ተረበሸ የሚያስብል አለመሆኑን በመናገር ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ የሚታወስ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም ዛሬ በጅማ ቦምብ መፈንዳቱ ተሰምቷል።በአደጋውም 13 ሰዎች ቆስለዋል። የቦምብ ጥቃቱ የተፈጸመው ባለታወቀ ግለሰብ ነው ቢባልም ከአካባቢው የወጡትና ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች ግን በፍንዳታው የመንግስት እጅ እንዳለበት የሚያመለክቱ ናቸው። በጅማ ለገሀር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቦምብ ጥቃቱን ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ አለመያዙም ጉዳዩን አጠያያቂ አድርጎታል።
No comments:
Post a Comment