Thursday, August 10, 2017

ባህር ዳር ተጨናንቃለች (የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)


ከአንድ ቀኑ አድማ በኋላ በከተማዋ ውስጥ በህቡዑ በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመፍራት ነሃሴ 1 ቀን በተከፈቱ የመንግስት ተቋማት ላይ ጥቃት ይሰነዘራል በሚል ከፍተኛ ጥበቃ ሲደረግ ውሏል፡፡በተለይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው ቢሮ እና በዕለቱ ከፍተው በዋሉ ተቋማት ላይ የቦንብ ጥቃት ይደርሳል የሚል መረጃ ደርሶናል ያለው የአገዛዙ የጸጥታ ሃይል በከፍተኛ ሁኔታ አካባቢውን በመቶዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ከቦ ውሏል፡፡ባህር ዳር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያልተነሳላት በወታደራዊ አገዛዝ ስር ያለች ከተማ እንደሆነች እየታየ ነው፡፡በሁሉም አካባቢ ወታደሮች ከሁለት አልፈው አራትና አምስት በመሆን ሲዘዋወሩ ይታያሉ፡፡
በትላንትናው እለት የተጀመረው ባለሃብቶችን የማሰር ዘመቻ ቀጥሎ በባህርዳር ታዋቂውን ባለሃብት የድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው አባት፣ አቶ ሽባባው የኔዓባትን ጨምሮ ዋና ዋና የሚባሉ ከ20 በላይ ነጋዴዎች የነጻነት ሰማአታቱን ለመዘከር ስራ አቁማችሁዋል በሚል ከታሰሩ በሁዋላ አሁንም በአድማው የተካፈሉ የንግድ ድርጅቶች እየታሸጉ ነው።በእስሩ ዝርዝር በፍስለታ ፆም የዘጉ የስጋ ቤት ባለቤቶችም ሰለባ ሆነዋል፡፡አንደኛ ፖሊስ ጣቢያም በበርካታ እስረኞች ቤተሰቦች ተከቧል፡፡
የገዥው መንግስት አመራሮች የባህርዳር እና አካባቢዋ፣የጎንደርና ደብረታቦር ወጣቶች የተሰውበትን የሰማዕታት ቀን ለምን አከበራችሁ በሚል የእስር እርምጃ መጀመሩ ህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ እያስቆጣው ነው፡፡የክልሉ መንግስት የክልሉ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብና ቀኑ በሃዘን ታስቦ እንዲውል በማድረግ በዕለቱ የጠፋውን ክቡር የሰው ልጆች ህይወት አስቦ መዋል ሲገባው፣ ለምን ዕለቱን አሰባችሁ በማለት እስር መጀመሩ ስርዓቱ ሆነ ብሎ ያጠፋውን ህይወት እንዳናስታውስ ለማድረግ እየጣረ ነው የሚል አስተያየት በከተማዋ የሚገኙ ምሁራንና ነዋሪዎች እየሰጡ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment