Monday, August 21, 2017

ትግላችን በተፈጥሮ ሞት ህይወቱ ካለፈው መለስ ዜናዊ ጋር ሳይሆን በህወሐት እና በመለስ የተተከሉብንን ዘረኝነት፣የሃሳብ ደሃነት እና የመንፈስ ድርቀት ከስራቸው ነቅሎ በመጣል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው!!! (ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)



ሰሞኑን በሀገራችን ህወሐት/ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሃን ስለ መለስ ዜናዊ 5ኛ ሙት ዓመት በተመለከተ እየተሰራጨ ያለው ፕሮፓጋንዳና መሪ ቃል ከዛሬ 50 ዓመት በፊት በሶቪየት ህብረት ምድር የጆሴፍ ስታሊን ሞት ተከትሎ ሲደረግ የነበረውን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ ስታሊን በሀገሩ ጨካኝና አረመኔ ቢሆንም እሱ የሚቆጣጠረው መዋቅር በስልጣን ላይ ስለነበረ በ15ቱም የሶቪየት ግዛቶች አስከሬኑ እየተዘዋወረ በብዙ ሽዎች የሚቆጠር ህዝብ እየወጣ እንዲያለቅስና ለስታሊን አድናቆት እንዲሰጥ ይደረግ ነበር፡፡ ዛሬ የሶቪየት ህብረት ግዛቶች ተገነጣጥለው 15 ቁርጥራጭ ሀገሮች ሆነዋል፤ስታሊንም ሆነ አገዛዙ ክፉ ታሪክ ሆነው አልፈዋል፡፡
ዛሬም በኢትዮጵያ መለስና ህወሐት በፈጠሩትና በሚቆጣጠሩት የመገናኛ ብዙሃን ከዚህ አገዛዝ የተለየ ሀሳብ ስላላቸው ብቻ በሽዎች መገደላቸውን ሰምተን ሳናበቃና የተለየ ሃሳብ ያንፀባረቁ በሽዎች በየእስር ቤቱ ታግተው በሚገኙባት፣ ዜጎች በዘር ጥላቻና በጎሰኝነት ከመኖሪያ ቀያቸው በሚፈናቀሉባት ሀገር ሟቹ መለስ ዜናዊ "የሃሳብ ድህነትን ያሸነፈ መሪ" በሚል መሪ ቃል ሙት ዓመቱ በአገዛዙ በመዘከር ላይ ይገኛል፡፡ ሀሳብን እንደ ጦር የሚፈራው ህወሐት/ኢህአዴግ ይህንን መሪ ቃል ሲያስተላልፍ አንድም የኢትዮጵያን ህዝብ በመናቅ ነው ያለዛም የሀሳብ ድህነት ምን እንደሆነ አለማዎቅ ነው:: ከዚያም ካለፈ ሕወሃት ከወደቀና ስልጣናችን ካበቃ በኋላ ስለእኛ የሚወራ ምንም ነገር የለም ከሚል መጭውን የመፍራት የስነ ልቦና ቀውስ ነው፡፡ በእኛ እምነት፡-Image may contain: one or more people
-1. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ የዜግነት ስልጣን የለውም፡፡ እነሱ በፃፉት ህገ መንግስት የስልጣን ባለቤት ዜጎች ሳይሆኑ "ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች" የሚባሉት ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ እነዚሁ "ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች" ከፈለጉ እንዲገነጠሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
2. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚባሉ በጠላትነት የሚተያዩ ሁለት ድሃ ሀገሮች ተፈጥረዋል፡፡ 
3. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን ወደብ አያስፈልገንም ብለው በፊርማቸው አረጋግጠው የኢትዮጵያን ታሪካዊ ወደብ ባለቤትነት አስረክበው ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላትና የታነቀች ሀገር ሆናለች፡፡
4. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን መነሻው ምን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት ከትንሽዋ ኤርትራ ጋር በተደረገ ጦርነት ከሰባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ካለቁ በኋል የተገኘውን ድል ይግባኝ በሌለበት ድርድር በአልጀርስ ስምምነት የኢትዮጵያን ግዛት አስረክበው ለዳግም ጦርነት እያዘጋጁን ይገኛሉ፡፡
5. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያ በታሪኳ አድርጋው የማታውቀውን የውጭ ሀይሎችን ለማስደሰት ሶማሊያ ውስጥ ጦር አዝምታ ብዙ ኢትዮጵያውያን ካለቁ በኋላ ስለተሰውት ኢትዮጵያውያን እና ለጦርነቱ ስለወጣው ወጪ ለፓርላማ እንዲያስረዱ ሲጠየቁ "ይህ ፓርላማ እኔን ለመጠየቅ ስልጣን የለውም" የሚል የእብሪት መልስ ሰጥተው አልፈዋል፡፡
6. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን መለስ ዜናዊ አፄ ኃይለስላሴ የአፍሪካ ህብረት መስራች አባት እንደሆኑ እያወቁ በአፍሪካ ህብረት ግቢ ሀውልታቸው እንዳይቆም ተከራክረዋል፣ ይህንን አቋማቸውን ለሚያሽከረክሩት ፓርላማ ቀርበው አስረድተዋል፡፡
7. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን ጥረት፣ድካም እና ወድድር ለውጤታማነት መመዘኛ መሆኑ ቀርቶ ሙስና እና ባቋራጭ መክበር እንደ ማህበረሰብ መገለጫችን ሆነዋል፡፡
8. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን የትምህርትና የእውቀት መሰረት የሆነው መጠየቅና መመራመር፣ እራስንና አካባቢን መረዳት መሆኑ ቀርቶ ትምህርት በኩረጃና በግልበጣ ብቻ የሚገኝ ለማህበራዊ ሽግሽግ የሚያገለግል ተራ ሸቀጥ ሆኗል፡፡
9. በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረትን የመሰረቱና ታላላቅ ዲፕሎማቶች የፈለቁባት ሃገር መሆኗ ተረስቶ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት መፅሃፍት ላይ የተፃፉ የአየር ንብረት ለውጥ ሀሳቦችን ይዞ ከፈረንጆች ጋር ማውራት የተደራዳሪነትና የዲፕሎማሲ ልዩ እወቀትና ጥበብ ሆኖ ታይቷል፡፡
በአጠቃላይ በመለስና በህወሐት/ኢህአዴግ ዘመን የተለየ ሀሳብ ያለው የሚገደልበት፣የሞራልና የመንፈስ እሴቶች የሚዳከሙበት፣ ዜግነት በጎሰኝነት ተተክቶ የእርስ በእርስ መፈራራትና መጠራጠር የሰፈነበት፣ መሪ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የማህበረሰብ የሞራል መሪ መሆን ሲገባው "ባንዲራ ጨርቅ ነው"፣ "የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው"፣ "ከዚህ ወርቅ ከሆነ ብሔረሰብ በመወለዴ እኮራለሁ" እየተባለ በዘፈቀደ የሚነገርባት ሀገር ሆናለች፡፡ 
ከላይ በጠቀስናቸው የመለስና የድርጅቱ ውርሶች በድምርና በተናጥል በሀገር ላይ ያደረሱት ጥፋት ፅዋው ሞልቶ ኢትዮጵያን የማፈራረሱ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር ለመሸጋገር ምልክቶችን በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ማየት ጀምረናል፡፡ ስለሆነም ይህንን መለስና ህወሐት የተከሉብንን ዘረኝነት፣ የሃሳብ ደሃነት እና የመንፈስ ድርቀት ከስራቸው ነቅለን በመጣል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚደረገው መራራ ትግል ቆርጠን እንድንነሳ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ነሐሴ 14 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment