መንግሥት እንደ ጠላት፣ ጡረታዬን መከልከሉ ያሳዝነኛል
· የሶማሊያን ወራሪ ሃይል ድባቅ የመቱ ጀግኖች ታሪክ ተቀብሯል
· ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሚሰጠው ትርጉም ተዛብቷል
· ለሶማሊያ የምናደርገው ድጋፍና እርዳታ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል
@አዲስ አድማስ
የዛሬ 40 ዓመት የዚያድ ባሬ አገር ሶማሊያ፤ እንደዛሬው የፀና መንግስት የሌላት፣ ደካማ ጎረቤታችን አልነበረችም። ከጦቢያ እገዛና ድጋፍ የምትሻ ምስኪን አገርም ፈፅሞ አልነበረችም፡፡ ይልቁንስ ኮሙኒስቷ ሶቭየት ህብረት እስከ አፍንጫዋ ድረስ በዘመኑ የጦር መሳሪያ ያስታጠቀቻት የፈረጠመች አገር ነበረች። የመሪዎቿም ዓላማ በዙሪያዋ ያሉትን ጨፍልቃ “ታላቂቱን ሶማሊያ” መፍጠር ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት ዚያድ ባሬ መሪነትና አዋጊነት ኢትዮጵያን በኃይል ለመውረር የተነሳችው፡፡
በአዲስ የመንግስት ምስረታ ሽግግር ላይ ለነበረችው ኢትዮጵያ ወቅቱ ፈታኝና አስቸጋሪ ነበር፡፡
ቢሆንም የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፤ ህዝቡ የአገሩን ዳርድንበርና ሉአላዊነት ከወራሪዋ ሶማሊያ እንዲከላከል ላደረጉት የእናት አገር ጥሪ ያገኙት ምላሽ፤ ፈጣንና በአገር ፍቅር ወኔ የተሞላ ነበር ይላሉ - በወቅቱ በጦርነቱ ላይ ከተሳተፉት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ የሆኑት መቶ አለቃ በቀለ በላይ፡፡ የያኔው ጎረምሳ፣ ለእናት አገር ጥሪው ምላሽ ሲሰጡ፣ ገና የ19 ዓመት ወጣት ነበሩ። ከ3 መቶ ሺ ሚሊሻዎች አንዱ የነበሩት መቶ አለቃ በቀለ፣ የሳቸው ክፍለ ጦር ተመርጦ በአየር ወለድ መሰልጠኑን ያወሳሉ፡፡ በዕብሪት አብጦ ኢትዮጵያን በኃይል የወረራትን የዚያድ ባሬ ሰራዊት፤ መክቶና ድባቅ መትቶ ለመመለስ፣ አያሌ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አልቀዋል፡፡
የዕድል ጉዳይ ሆኖ፤ በህይወት ተረፉ እንጂ መቶ አለቃ በቀለም ከሞት በመለስ ያልቀመሱት አበሳና ፍዳ የለም - ነፃነቷ የተጠበቀች አንዲት ኢትዮጵያን ለማቆየት፡፡ መቶ አለቃ በቀለ፣ ከሶማሊያ ጋር በነበረው አሰቃቂ ፍልሚያ፣ በሰሩት የጦርነት ጀብዱ፣ የአገሪቱን ብሔራዊ የጦር ሜዳሊያ ኒሻን፣ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እጅ ተሸልመዋል፡፡ በአገር ተከብረዋል ተወድሰዋልም፡፡
“የጀግናው ወሮታ” በሚል ርዕስ የህይወት ታሪካቸውን የሚዘክር ባዮግራፊ የተፃፈላቸው መቶ አለቃ በቀለ በጀግንነታቸው አገርና ትውልድ እንዳከበሯቸው ተገቢውን ወሮታ ከአገርም ሆነ ከመንግሥስት አግኝተው ለመኖር አለመታደላቸውን ይናገራሉ፡፡ የደርግ መንግስት ወድቆ፣ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ፣ ሰራዊቱ በጅምላ “የደርግ ሰራዊት” በሚል ተፈርጆ፣ ለእስር መዳረጉን በቁጭት ያስታውሳሉ፡፡ አገርንና ህዝብን ይቅርታ
ጠይቁ ተብለውም፣ “ምን በድዬ፤ ህዝብና አገር ሙትልኝ ሲሉኝ በመሞቴ?!” ብለው አሻፈረኝ በማለታቸው፣ ሌሎች ይቅርታ ጠይቀው ከእስር ሲለቀቁ፣ እሳቸው ከ2 ዓመት በላይ ታስረው መፈታታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በደሉ ግን በእስር ብቻ አላበቃም የሚሉት የጦር ሜዳው ጀግና፤ ለፈፀምኩት ጀብዱ ወሮታዬ እንደ ጠላት፣ ጡረታ መከልከልና ታሪካችንን ትውልድ እንዳያውቀው መደበቅና መቅበር ሆኗል ይላሉ፡፡ እኚህ የጦቢያ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ በአዛውንት ዕድሜያቸው፣ ጡረታም መጠለያም ታሪክም… ጭንር ተነፍገው፣ ህይወታቸውን በሰጧት አገር፣ እንደ አልባሌ ተጥለውና ተረስተው እየኖሩ መሆናቸውን በቁጭት ይናገራሉ፡፡ ሌላው ሁሉ ሳያንስ፣ ለሳቸውና መሰሎቻቸው ማስታወሻ ተብሎ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በር ላይ የተሰራው “ድላችን ሀውልት”፤ ስያሜው ተቀይሮ “የኢትዮ ኩባ” ወዳጅነት ሃውልት” ሲባል መስማቴ ከምንም በላይ ያሳዝነኛል ብለዋል፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ከፈፀመች እነሆ 40 ዓመት ሞላት፡፡ እኚህ ጀግናስ አሁን የት ነው ያሉት? የጀግንነት ውሎአቸውን…፣ ከአገሪቱ የተከፈላቸውን ወሮታ፣… የዛሬውን ህይወታቸውን … በሀዘንና በቁጭት ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አውግተውታል፡-
ወደ ውትድርና መቼና እንዴት ገቡ?
በ1967 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ማጋጠሙን ተከትሎ፣ በተደረገ ወታደራዊ ምልመላ አማካኝነት ነው፡፡ በወቅቱ ሶማሊያን በመሳሪያ ያስታጠቀው የሶሻሊስት ሶቪየት ህብረት ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ገና በለውጥ አብዮት ውስጥ ነበረች፡፡ ሶማሊያ ለረጅም ዘመን ወታደራዊ ኃይሏን ስታፈረጥም ነበር የቆየችው፤ በዚህም የተነሳ በመካከላችን ከፍተኛ የኃይል አለመመጣጠን ነበረ፡፡ በሶማሊያ ወረራ ሳቢያ ነው በ1969 ለውትድርና ከተለመለመሉ ወጣቶች አንዱ የሆንኩት፡፡ በወቅቱ እድሜዬ 19 አመት ነበር፡፡
ያኔ የሀገራቱ ወታደራዊ አወቃቀር ምን መልክና ቅርፅ ነበረው?
ሰራዊቱ አራት ክፍለ ጦሮች ብቻ ነበሩት። የታጠቀው መሳሪያም ሶማሊያ ከነበራት አንፃር በእጅጉ የሚራራቅ ነው፡፡ 1ኛ ክፍለ ጦር በወቅቱ የአዲስ አበባ ዙሪያን ሲጠብቅ፣ 2ኛ ክፍለ ጦር ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያን፣ 3ኛ ክፍለ ጦር ሀረርጌን እንዲሁም 4ኛ ክፍለ ጦር የሶማሌ ጠረፍን ነበር የሚጠብቀው፡፡ ነገር ግን የዚህ ክፍለ ጦር ኃይል በእጅጉ አነስተኛ በመሆኑ ነበር የዚያድ ባሬ ጦር በቀላሉ አውድሞት ኢትዮጵያን የወረረው። በወቅቱም ጠንካራ መከላከል ያላጋጠመውና የሶማሊያ ጦር በአጭር ጊዜ የኦጋዴን ክልልን አቋርጦ እስከ ደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል የዘለቀው በዚያ የተነሳ ነው፡፡
በወቅቱ እንደገልፅኩት፤ ኢትዮጵያ በመንግስት ለውጥ ላይ በመሆኗ፣ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ “ተነስ ታጠቅ ሀገርህ በጠላት ተደፍራለች” የሚል ጥሪ ባደረጉበት ሰዓት፣ 3 መቶ ሺህ ሚሊሻ ነው በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ፣ የመከላከል እርምጃ የተወሰደው። ይህ ምልምል ኃይል ነው የሶማሊያ ወራሪን ከሃረርና ድሬደዋ እንዳያልፍ የተከላከለው፡፡
እርስዎ በየትኛው የጦር ክፍል ነው የተመደቡት?
እኛን ሲያሰለጥን የነበረው የኢትዮጵያ አየር ወለድ ነው፡፡ የተፈለግነውም ከአየር ወለዱ በተሻለ ከጠላት በስተጀርባ ተገኝተን የማጥቃት እርምጃ እንድንወስድ ነበር፡፡ ግን ለዚህ ግዳጅ የተፈለገውን ያህል ስልጠና ባለማግኘታችን ወደ መደበኛ ጦር ነው የገባነው፡፡ ስልጠናችንን አቋርጠን፣ ጥቅምት 1970 ነው፣ ወደ ጦር ግንባር የዘመትነው፡፡
የመጀመሪያ የጦር ሜዳ ተጋድሏችሁ ምን ይመስል ነበር?
የሶማሊያ ወራሪዎች የሃረር ሬድዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር፣ ከሀረር ከተማ 2 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የፈዲስ ተረተርና የሀረር ቢራ የሚያመርተው፣ ሶፊ የተሰየመበት የሶፊ ተራራ ላይ ሰፍሮ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ነው፣ እኛ የመጀመሪያ የጦር ሜዳ ግዳጅ የተወጣነው፡፡
በወቅቱ ሀረር ከተማን ወራሪው ኃይል ያለማቋረጥ ይደበድብ ነበር፡፡ የሀረር ህዝብ እኛ ስንደርስ ቤቱ አያድርም ነበር፡፡ ምሽግ ቆፍሮ በየምሽጉ ነበር የሚያድረው፡፡ ያገኘውን መሳሪያ ማለትም ቆንጨራ፣ ገጀራ በመያዝ ነበር ጠላትን ለመፋለም ይጠባበቅ የነበረው፡፡ ሁኔታው በእጅጉ ያሳዝን ነበር፡፡ ጠላት ከተማውን ያለ ርህራሄ በእሳት እያቃጠለ፣ ህዝቡን ያስጨንቅ ነበር፡፡
ሀረርን ከዚህ ጥቃት እንዴት ነው የታደጋችሁት?
እኛ ማረፊያ አጥተን ያረፍነው የሃረር ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው ቦታ ሁሉ በጠላት አረሮች ይደበደብ ነበር፡፡ እዚያ ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ሆነን፣ ወደ ሶፊ ተራራ ስንመለከት፣ የጠላት አስተኳሽ፣ ተራራው አናት ላይ ቆሞ የተኩስ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ያለማቋረጥ ይጮሃል፤ “ልክ ነህ ዝቅ አድርግ … ከፍ አድርግ” እያለ ለተኳሾች ኢላማ ሲያመቻች በመገናኛ ሬዲዮ ይሰማል፡፡ ያለማቋረጥ በሶማሊያኛ ቋንቋ “ኦርያ ማ! መቀሌ ሰን! … ኦርያ ማ! መቀሌ ሰን!” እያለ አስተኳሹ ይጮሃል፡፡
በወቅቱ ሻለቃ፣ በኋላ ሌ/ኮሎኔል የሆኑት አዛዣችን ወኔ ቀስቃሽ ትዕዛዝ ነበር የሰጡን፡፡ “ይሄን አስተኳሽ … ሃረርን እያቃጠለ ያለን ጠላት … ከእነነፍሱ ይዛችሁልኝ ስትመጡ ብቻ ነው በእውነት የፓራ ኮማንዶ ሰልጣኝ መሆናችሁ የሚታወቀው … ለሀገራችሁ ያላችሁ ፍቅርም የሚለካው በዚህ ነው” አሉን፡፡ የጦራችን አባላት 140 ብቻ ነበርን። ትዝ ይለኛል፤ ሰዓቱ የጀንበር መጥለቂያ አካባቢ ነው፡፡ ወደ ተራራው ስንጠጋ፣ በሚደንቅ ሁኔታ ያ አስተኳሽ፣ በጠላት አንድ ሻለቃ ጦር ተከብቦ ነው የሚያስተኩሰው፡፡ እኛ እንግዲህ እዚህ የጠላት ጦር መሃል ነው የገባነው፡፡ ፍፁም ተመጣጣኝ አልነበረም ጦራችን፡፡ እነሱ ከ600 በላይ ናቸው፤ እኛ ደግሞ 140 ነን፡፡ በዚያ ላይ እኛ የነፍስ ወከፍ መሳያ ነው የያዝነው፤ እነሱ ዘመናዊ መሳሪያ ነው የታጠቁት። ይሄ ታሪክ ሲነገር ለብዙዎች የማይታመን ተረት ተረት ነው የሚመስለው፡፡ እዚህ ከ600 በላይ ጦር መሃል ገብተን ስንታኮስ፣ ጥይት አልቆብን በሳንጃ ነበር የተሞሻለቅነው፡፡ ውጊያችንን ሙሉ ለሙሉ በሳንጃ ነበር ያደረግነው፡፡ የኛ ኢላማ አስተኳሹ ነው፤ በፅናት ነበር የተዋጋነው፡፡ ያንን አስተኳሽ ከእነ መገናኛ ሬድዮው ይዘን፣ በቃላችን መሰረት ለአለቃችን አስረከብን፡፡ የሶማሌ ጦርም መፍረክረክ ጀመረ፡፡ ተራራውንም አስለቅቀን፣ ሃረርን ከመቃጠል ታደግናት፡፡ በጦነቱ ከተሳተፍነው 140 ጓዶች፣ 60ዎቹ ሲሞቱ፣ 80ዎቹ ነን በህይወት የተረፍነውና ግማሹም ቁስለኛ የሆነው፡፡
የሶማሊያ ወራሪ ኃይልን ድል ለማድረግ የተደረገው ፍልሚያ በበቂ ሁኔታ ተነግሮለታል፤ ተዘግቧል ይላሉ?
በፍፁም፡፡ ታሪኩ አለመነገሩ በጣም ይቆጫል። በተለይ ያንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች፣ ታሪክ መቀበሩ ያሳዝናል ያስቆጫል፡፡ ወታደራዊ ጥበብ ራሱ ሳይንስ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ስለ እኛ መውደቅና መሸነፍ ነው በስፋት የሚነገረው፡፡ ለሀገር ዳር ድንበር ያበረከትነው አስተዋፅኦ መና ቀርቶ፣ በትውልዱ እንዳይታወቅ መደረጉ በእጅጉ ያስቆጫል፡፡
ከደርግ ጋር ተጨፍልቀን፣ እኛ በእናት ሀገር ፍቅር ልክፍት፣ ለዳር ድንበሯ ምትክ የሌለው መስዋዕትነት የከፈልን ሰዎች፣ ምንም እንዳልሰራን ተደርጎ በየቦታው መሳለቂያ ሆነናል፡፡ ይሄ አሳዛኝ የታሪካችን ምዕራፍ ነው፡፡ አለመታደል ነው፡፡ የዚያን ሰራዊት አወዳደቅና አፈራረስ ምክንያቶች፣ ነገ ከነገ ወዲያ ታሪክ የሚፋረደው ጉዳይ ነው፡፡ እንደ‘ኔ ግን በወቅቱ የደርግ ሰራዊት ተሸንፎ አይደለም የወደቀው፡፡ የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንደሚባለው፣ ሰራዊቱ ሳይሆን ስርአቱ ነው ተሸንፎ ሰራዊቱም አብሮ የተጨፈለቀው እንጂ ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ልክፍት የነበረው ሰራዊት ነበር፡፡
በመሰረቱ በኛ ሀገር የሰራዊት ሚና አረዳድ ችግር እስካሁንም አለ፡፡ ኢህአዴግ እኛን የኢትዮጵያ ሰራዊት ብሎ ሊቀበለን አልፈለገም፤ “የደርግ ሰራዊት” ነበር የሚለን፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በብዙዎች “የኢህአዴግ ሰራዊት” እየተባለ ይጠራል፡፡ ይሄ አንደኛው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚሰጠው ትርጉም ከጅምሩ መዛባቱንና አሁንም ድረስ መቀጠሉን አመላካች ነው። አንዱ መንግስት ሲፈርስ ሰራዊቱ መፍረሱ አሳዛኝ ነው። ንጉሱ በቁጭት ያቋቋሙት ባህር ኃይል እንዲፈርስ መደረጉ አሳዛኙ የታሪካችን አካል ነው፡፡
ለዚህ ተጋድሏችሁ የታሪክ ማስታወሻዎ የላችሁም?
ነበረን፤ ግን እንደ አለመታደል ሆኖ ዛሬ ስሙ ተቀይሮ፣ ታሪካችን እንዳይነሳ ሆኗል፡፡
ብዙዎች ላያውቁት ይችላሉ፡፡ የትኛው ነው ማስታወሻችሁ?
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ሃውልት “የድላችን ሃውልት” ነበር መጠሪያው፡፡ ሃውልቱ ላይ የተቀመጠው ምልክት፣ እኔና መሰሎቼ በጦር ሜዳ ለፈፀምነው ጀብዱ የተሰጠን ኒሻን አርማ ነው፡፡ ይሄን ብዙዎች አያውቁትም፡፡ አሁን “ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ሃውልት” ሲባል ስሰማ አዝናለሁ፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ታሪካችን፣ በትውልድ እንዳይዘከር ለማድረግ የታለመ ነው፡፡
ሃውልቱ ለምን ተግባር እንደቆመ የምታውቁ ሰዎች “ስያሜው ሊቀየር አይገባም” የሚል ተቃውሞ ለምን አላቀረባችሁም?
ለማን ነው የምናቀርበው? … የሚሰማ ሲኖር እኮ ነው። አሁንም ቢሆን ይሄ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እኛ እንዳንጠራበት መደረጉ ያሳዝናል ያሳፍራል፡፡ የነበረን ታሪክ እንዳልነበረ ለማድረግ ጥረት መደረጉ አሳዛኝ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኩባዎች ከኛ ጋር ተዋግተዋል፡፡ ግን መታሰቢያቸው በሌላ ሊሆን ይችላል እንጂ ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ የሀገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር የወደቁትን ጀግኖች መታሰቢያ ማሳጣት፣ በእውነት የታሪክም ተወቃሽ ያደርጋል፡፡ እኛ እናውቀዋለን፤ አዲሱ ትውልድ ግን የዚህን ሃውልት ምንነት እንዲያውቀው መንገድ አልተከፈተለትም። እኔ ደርግ ጥሩ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ግን ሰራዊቱ ለሀገር ዳር ድንበር የከፈለው መስዋዕትነት መና መቅረት የለበትም፡፡
መስዋዕትነታችን መና ቀርቷል ብለው ይቆጫሉ?
ለሀገር ዳር ድንበር የከፈልነው መስዋዕትነታችን አስታዋሽ ማጣቱ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ‘ኮ በ1983 ደርግ ሲወድቅ ታስሬያለሁ፡፡ ወሮታችን የተከፈለን በእስር ነው፡፡ በጦላይ ወታደር ማሰልጠኛ ውስጥ ለ2 ዓመት ተኩል ታስሬያለሁ፡፡ በወቅቱ ይቅርታ ጠይቁና ውጡም ተብለን ነበር፡፡ “ጥፋተኞች ነን፤ ሀገርንና የኢትዮጵያን ህዝብ በድለናል” ብላችሁ ይቅርታ ጠይቁ ተብለን ነበር፡፡ የጠየቁ አሉ፡፡ እኔ ግን፤ “ሀገሪቱንና ህዝቡን በድለሃል ነው እንዴ የምትሉኝ፤ … በፍፁም አልበደልኩም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያን ክብር! ሉአላዊነት! ነፃነትና ዳር-ድንበሯን ለመጠበቅ ስል፣ ከሞት በመለስ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍያለሁ” ነበር ያልኳቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ “ሂድና ሙትልኝ” ሲል ሞትኩለት እንጂ ምን የበደልኩት አለ? ይሄን ይቅርታ ካልጠየቅ ተብዬ በአቋሜ በመፅናቴ፣ 2 ዓመት ተኩል ታስሬ ሲሰለቻቸው ለቀውኛል፡፡
አሁን ሶማሊያ ከረጅም የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ መንግስት እየመሰረተች ነው፡፡ ይሄን ሲያዩ ምን ይሰማዎታል?
ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን የወረረችው፡፡ በ1956 ዓ.ም ጀነራል አማን አምዶም የቀለበሱት ወረራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በ1953 ዓ.ም የወረራ ሙከራ አድርገው ነበር፤ እሱም ከሽፏል። ሶማሊያ ነፃነቷን ከቅኝ ገዥዎቿ ከተቀዳጀች ጀምሮ ለኢትዮጵያ የተኛችበት ጊዜ የለም፡፡ ዛሬም ድረስ በሰንደቅ አላማዋ ላይ ባለ 5 ኮከብ አርማ ነው የምትጠቀመው፡፡ ዛሬም ድረስ ይሄ ህልሟ የተዳፈነ እንጂ ፈፅሞ የተቀበረ አይመስለኝም። የ5ቱ ኮከብ አላማ፡- ከሀገሪቱ ዜጎች ጭንቅላት እስካልወጣ ድረስ ለዳር ድንበራችን ትተኛለች ብዬ አላምንም፡፡ ይሄ ድጋፍና እርዳታችንም ውሎ አድሮ፣ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል የሚል ስጋትም አለኝ፡፡
የሀገሪቱ የጦር ሜዳይ ተሸላሚ ነዎት….
አዎ! የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀግና፣ የ2ኛ ደረጃ ሜዳይ ተሸላሚ ነኝ፡፡ በ1977 ነው ከደርጉ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም እጅ የተሸለምኩት፡፡ ይሄን እድል የሚያገኙት ደግሞ ጥቂቶች፣ የተለየ የጦር ሜዳ ጀብዱ የፈፀሙ ብቻ ናቸው፡፡
እርስዎን ለዚያ ያበቃዎት የተለየ የጦር ሜዳ ጀብዱ ምንድን ነው?
በእርግጥ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ በአንድ የጦር ሜዳ ውሎ ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ብዙ ውሎዎች ተደማምረው የሚገኝ ነው፡፡ ግን በዋናነት አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከወራሪው ሃይል ነፃ በወጡበት ጊዜ ደርግ “በምስራቅ የተገኘው ድል በሠሜን ይደገማል” በሚል ጦሩን ነቅሎ ወደ ሰሜን ሲወስድ፣ ጥቂት ብርጌዶችን ኦጋዴንን እንዲጠብቁ ያደርጋል፡፡ በወቅቱ የዚያድ ባሬ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ቢወጣም ጠረፉ ላይ ሰፍሮ ነበር፡፡ ደርግ ሰራዊቱን ወደ ሰሜን መውሰዱን ያወቀው ዚያድ ባሬ፤ ወረራ ለማድረግ ተንቀሳቀሠ፡፡ ያ ዳግም ወረራ ከተደረገባቸው አውራጃዎች መካከል ቀብሪ ዳሃር፣ ዋርዴር፣ ገላዲ፣ ቦህ፣ ሉድሞ፣ ሊምበል የመሣሠሉት ናቸው፡፡
እኔ የነበርኩበት ክፍል ጦር ዋና መቀመጫው ቀብሪ ዳሃር ነበር፡፡ በአንድ ሻምበል ጦር የተደራጀ ነበር፡፡ ወራሪው ሃይል ከሌላም አንድ ሻምበል ጦር ጋር እኛን በከበባ ውስጥ አስገባን፡፡ 6 ወር ሙሉ ከወገን ጦር ተቆርጠን ነው ውጊያ ያደረግነው። ስንቅና ትጥቅ የሚደርሠን ከአውሮፕላን ነበር፡፡ እኛ አንድ ሻለቃ ብርጌድ ብቻ ሆነን፣ የተከበብነወ በአምስት ክፍለ ጦሮች ነበር፡፡ የጠላት ጦር የሚመራው ደግሞ በራሱ በዚያድ ባሬ የመከላከያ ሚኒስትር ነበር፡፡ እኛ ምሽጋችንን ቆፈርን፣ 6 ወር ሙሉ እንቅልፍ የለ፣ እረፍት የለ፣ በመከላከል ላይ ቆየን፡፡ በዚህ መሃል ብዙ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡ በጠላት ጦርና በኛ መካከል የነበረው ርቀት 3 መቶ ሜትር እንኳን አያክልም ነበር፡፡ አፍንጫ ለአፍንጫ ተጋጥመን ነው 6 ወር የቆየነው፡፡
መጨረሻ ላይ ጠላት አንድ ብርጌድ የአየር መቃወሚያ፣ አንድ ሻለቃ መድፈኛ፣ አንድ ብርጌድ ታንከኛ፣ አንድ ብርጌድ ሜካናይዝድ ጦር አደራጅቶ፣ 4 መቶ የማንሞላውን ለመደምሰስ ግስጋሴ ጀመረ። እኛ የመከላከያ ምሽጋችን ውስጥ በተጠንቀቅ ነበር የተዘጋጀነው፡፡ በቅፅበት ሶስት ታንኮች ምሽጋችንን ሠብረው ገቡ፡፡ ከላይ የአየር ውጊያ፣ ከስር የታንክ ውጊያ ውርጅብኝ ይወርድብን ጀመር፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ እነዚያን ታንኮች ከምሽጉ ውስጥ እንዳሉ እየፈጯቸው፣ እያደቀቋቸው፣ የሰው ልጅ አካልና አፈር አብሮ እየተቦካ ብዙ ወገን ረገፈ። እነዚያ ታንኮችን የሚቋቋም መሣሪያ ማግኘት አልቻልንም። ወንድሞቻችን አይናችን እያየ፣ በታንክ ሠንሠለት ጎማ ተፈጩ፡፡ ይሄ ዛሬም ድረስ ከህሊናዬ የማይጠፋ ነው፡፡
በወቅቱ ሁኔታውን ለተመለከተ፣ የዘላለም የአዕምሮ እረፍት ነው የሚያጣው፡፡ እኔም ያ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም… ኢትዮጵያዊ ወኔዬ በእጅጉ ተቀሠቀሠ። ቦንቦቼን ታጥቄ፣ ብቻዬን ከምሽጌ ወጥቼ፣ ቀጥታ ወደ አንደኛው ታንክ ነው ያመራሁት፡፡ ታንክ ላይ መድፍ፣ መትረየስ፣ ፒኬቲ የሚባል መሣሪያ አለ፡፡ ታንክ እነዚህን ሁሉ የያዘ አውዳሚ መሳሪያ ነው፡፡ በደረቴ እየተሣብኩ ወደ ታንኩ ሄድኩና፣ በእጄ ያየዝኩትን ቦንብ በጭስ ማውጫው አጎረስኩት፡፡ ታንኩ እንዳልነበር ሆኖ ከእነ 8 ምድብተኛ ተኳሾቹ ዶግ አመድ ነው የሆነው። የወገኔን ደም ተበቅያለሁ፣ የሃገሬን ዳር ድንበር ህይወቴን አጋፍጬ ማስከበሬ ያኮራኛል፡፡
ዛሬ ህይወትን እንዴት እየመሩት ነው?
አምስት ልጆች አሉኝ፡፡ ስራ የለኝም፡፡ የሚያውቁኝ እየረዱኝ በሠው እጅ እየኖርኩ ነው። መንግስት ጡረታዬን እንኳ አይከፍለኝም፡፡ ዛሬ ሰውነቴን ብታዩት እንደ ድሪቶ የተሰፋፋ ነው፡፡ የቤት ኪራይ የሚከፍሉልኝ፣ ልጆቼን የሚቀልቡልኝ ታሪኬን የሚያውቁ ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ለሃገሬ ዳር ድንበር ያበረከትኩት አስተዋፅኦ ተዘንግቶ፣ እንደ ጠላት፣ ጡረታ እንኳ መከልከሌ ያሣዝነኛል፡፡ ለሃገሬ በከፈልኩት ዋጋ የምኩራራ ብሆንም፣ ለጀግንነቴ በተከፈለኝ ወሮታ ግን እያዘንኩ እኖራለሁ፡፡ መቼም የሰው እጅ እያዩ ከመኖርና ቤት አልባ ከመሆን የበለጠ ጉስቁልና የለም፡፡
ባለቤትዎስ …. አብራችሁ ነው የምትኖሩት?
የመጀመሪያዋ የትዳር አጋሬና የሁለት ልጆች እናት ባለቤቴ በ1996 ዓ.ም ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየችኝ፡፡ በዚያን ጊዜ እሷ ስትሞት ሁለቱም ወንዶች ልጆቼ አንዱ የ4 ዓመት፣ ሁለተኛው የ2 ዓመት ጨቅላ ህፃናት ነበሩ፤ እነዚህን ህፃናት ያለ እናት ብቻዬን ለማሳደግ፣ በጦር ሜዳ ከተፈተንኩት አውደ ውጊያዎች ሁሉ ህይወቴን የፈተነኝ ዘመን ነው፡፡ የልጆቼ እናት ከሞተችብኝ በኋላ ለ7 ዓመት በሀዘን አሳለፍኩ፡፡ ከዚያ የፈጣሪ ፍቃዱ ሆነና አሁን አብሬያት የምኖረው ባለቤቴ ጋር አዲስ ሕይወት መሰረትን፡፡ አበው ሲተርቱ፤ መከራው ያላለቀ በሬ ሲሞት፣ ቆዳው ለከበሮ ይወጠራል ይላሉ፡፡ አዲሱ የትዳር ጉልቻዬም እንደገና በፈተና ተሞላ፤ ይኸውም እኔን አዲሷ ባለቤቴ ወደንና ፈቅደን የድህነትን ተራራ አብረን ተጋፍጠን መኖር ስንጀምር፣ እሷም በአቅሟ ስራ ነበራት፡፡ እኔም ወጥቼ ወርጄ በማመጣው የዕለት ገቢ ተደጋግፈን ጎጆያችንን እየመራንና ልጆቻችን ማሳደግ ስንጀምር መጋቢት 14 ቀን 2006 ዓ.ም ሌላ የመከራ ድግስ ይዞልኝ መጣ፡- ይኸውም ውዷ ባለቤቴ የዕለት ስራዋን ለማከናወን ከምንኖርበት አየር ጤና ሰፈር ወደ ስራ ቦታዋ አብነት አካባቢ ለመሄድ ከካራ ቆሬ የተነሳ 66 ቁጥር አውቶቡስ ትሳፈራለች፡፡
ይህ ቀን ለውዷ ባለቤቴም አውቶብሷን ለተሳፈሩ ሁሉ አዝማም ቀን ነበር፡፡ 66 ቁጥር አውቶብስ አየር ጤናን አልፎ፣ ወደ አለርት ሆስፒታል ወይም ዘነበወርቅ ገደል እስከሚገባ ተሳፋሪው እየጮኸ እየተንገጫገጨ፣ ያን ሁሉ የጫነውን ሰው ይዞ ዘነበወርቅ ገደል ገባ፡- በአደጋው የሞተ ሞተ፤ የተረፈው የሰው ልጅ እንደ ኮንቴነር መጫኛ በክሬን ነበር የወጣው፡፡ ባለቤቴም በአካሏ ላይ ከፍተኛ አደጋ ከአደረሰባት በኋላ በዚሁ መልክ በህይወት ተረፈች። የደቆነ ሳይቀድስ አይቀርም ይባል የለም ዛሬ ባለቤቴ አካሏ ጎደሎ ከሥራ ውጭ ሆነ እነሆ እስከ፣ አሁኗ ሰዐት ድረስ እሷኑ በማሳከም ላይ እገኛለሁ። በአሁኑ ሰዓት ያኔ ህይወት ለሀገሬ ለኢትዮጵያ በከፈልኩት መስዋዕትነት ልክ ሳይሆን ሀገርንና ወገንን እንደበደለ፣ ወንጀለኛ ለኢትዮጵያ በደሜ ፍሳሽ በአጥንቴ ክስካሽ፣ ስጋዬ እንደ ዲርቶ ልብስ በመርፌ ተሰፍቶ፣ የሀገሬን ዳር ድንበር ሉአላዊነት እና የታላቁን ህዝብ ክብር በአስከበርኩበት ምድር ላይ ለእግሬ መቆሚያ፣ ለአንገቴ ማስገቢያ አጥቼ፣ በዚህ ዘመን እንደ ሀገር ባለውለታ መጦርና ተከብሬ በክብር መኖር ሲገባኝ፣ ከአብራኬ የወጡ ልጆቼና ቤተሰቤ ሁሉ እንደ አንድ የጦር ሜዳ ጀግና ቤተሰብ ሳይሆን እንደ ወንጀለኛ ቤተሰብ ከእኔ ጋር ከቦታ ቦታ መጠለያ በማጣት የሰውን ኩሽና ስንጠርግ እንከራተታለን፡፡
No comments:
Post a Comment