Thursday, August 31, 2017

ኦብነግ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ጠላት የሆነውን የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ አገዛዝን ለማስወገድ በጋራ እንዲነሳ ጥሪ አቀረበ (ኢሳት ዜና –ነሐሴ 25/2009)


የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ጠላት የሆነውን የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ አገዛዝን ለማስወገድ በጋራ እንዲነሳ ጥሪ አቀረበ።
የህወሀት መንግስት ከዚህ በላይ በስልጣን ላይ ከቆየ ኢትዮጵያን እንደሶሪያና የመን የብጥብጥ ሀገር ሊያደርጋት ይችላል ሲል ኦብነግ አስጠንቅቋል።
አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ነን ልዩነታችንን ወደ ጎን በማድረግ የህወሃትን መንግስት ለማስወገድ በጋራ እንነሳ ብሏል ግንባሩ።
አንድ ከፍተኛ አመራሩ ለህወሀት መንግስት ተላልፈው የተሰጡበት ኦብነግ ዓለም ዓቀፍ ህግን በመተላለፍ የተፈጸመው ተግባር ዋጋ ያስከፍላል በማለት ለሶማሊያ መንግስት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።Bilderesultat for ኦብነግ
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር የተመሰረተው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1976 ነው። ግንባሩ የሶማሌ ክልልን ነጻ ለማድረግ ፕሮግራም ነድፎ ለበርካታ አመታት በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጋራ አብሮ መኖር ይቻላል የሚለውን አቅጣጫ በመከተል ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በጥምረትና በህብረት በመስራት ላይ ይገኛል።
ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ከሚመራው መንግስት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ያደረጋቸው ድርድሮች ለህወሀት ትንፋሽ መውሰጂያ ዕድሜ ከመስጠት ያለፈ ትርጉም እንዳልነበረው ታዛቢዎች ይገልጻሉ።
በትግል መቆየት ያልፈለጉ አንዳንድ የግንባሩን አመራሮች በማስኮብለል በተደጋጋሚ ግንባሩ ፈርሷል የሚለው የህወሃት ፕሮፖጋንዳን ያፈረሱ ጥቃቶች በሶማሌ ክልል ከተፈጸሙ በኋላ የሁለቱ ሃይሎች ድርድር መቋረጡ የሚታወቅ ነው።
በተለይም የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ሁለት ተደራዳሪዎችን የህወሀት መንግስት ከኬኒያ አፍኖ ከወሰደ በኋላ በኦብነግ በኩል የድርድር ፍላጎቱ ሳያበቃ እንዳልቀረ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ።
ኦብነግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር መሰራት መጀመሩን አስታውቋል።
ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር ባለፈው በጀርመን ያደረገው ስምምነት ግንባሩ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ለመታገል በመወሰን አዲስ መሰመር ይዞ ብቅ ለማለቱ በአስረጂነት በመጠቀስ ላይ ነው።
የኦብነግ ውሳኔ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነም ይነገራል።
ሰሞኑን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር አንድ ከፍተኛ የአመራር አባሉ ለህወሀት መንግስት ተላልፈው መሰጠታቸውን ተከትሎ መግለጫ አውጥቷል።
ላለፉት ሶስት አመታት ነዋሪነታቸውን በሞቃዲሾ አድርገው የቆዩት አብዱከሪም ሼህ ሙሴ ባለፈው ሳምንት ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ችግር ወደ ሶማሊያ ማእከላዊ ግዛት ጋልሙዲግ መሔዳቸውንና በጋልካዩ ከተማ በአካባቢው የጸጥታ ሃይል መያዛቸውን የኦጋዴን ነጻነት ግንባር አስታውቋል። አቶ ሀሰን አብዱላሂ የግንባሩ ቃል አቀባይ ናቸው።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር እንዳስታወቀው የሶማሊያ መንግስት ዓለም ዓቀፍ ህግ ጥሷል። የሶማሊያንም ህገመንግስት የሚንድ ተግባር ፈጽሟል።
በመሆኑም ግንባሩ አስፈላጊ ነው ያለውን የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ ነው የግንባሩ ቃለቀባይ አቶ ሀሰን አብዱላሂ የሚናገሩት።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ የህወሀት መንግስትን ለመጣል የሚደረገው ትግል በጋራ መካሄድ እንዳለበት ጥሪ ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም።
የግንባሩ ቃለቀባይ አቶ ሀሰን አብዱላሂ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት የተናጠል ትግል የሚያዋጣ አይደለም። አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ነን። አንድ ሆነን ይህን ስርዓት እናስወግድ በማለት የቀደመውን ጥሪ ዛሬ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስ ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment