Monday, August 28, 2017

ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ዝነኛው የ“ሕልም አለኝ” ንግግራቸው (የኔነህ ከበደ)

በቀደመው ዘመን አፍሪካ አሜሪካውያን ከባርነት ቢላቀቁም በዘር ላይ ከተመሰረተው ዓይነተ ብዙ መድልዎና ጭቆና ነፃ ለመውጣት እልህ አስጨራሽ ትግልን ጠይቋቸዋል፡፡
ከነዚህ አይነታቸው የበዛ የመብት ማስከበሪያ ጥረቶቻቸው ውስጥ የዋሽንግተኑ ሠልፍ ተብሎ የሚታወቀው ክንውን አንዱ ነው፡፡
የዋሽንግተኑ ሰልፍ የተካሄደው የዛሬ 54 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡
ታዋቂው አፍሪካ አሜሪካዊ የመብት ተሟጋች ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ “ሕልም አለኝ” የሚለውን ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ያስገኘላቸውን አነቃቂ ንግግር ያደረጉት በዚሁ አጋጣሚ ነበር፡፡Image may contain: 5 people, indoor
በዚያን ጊዜ በአሜሪካ አፍሪካ አሜሪካውያኑ ተመርጠውና ተሾመው ለከፍተኛ ኃላፊነት ለመብቃት ይቅርና መሠረታዊ የመምረጥ መብታቸው በሰፊው ይጣስና ይጨፈለቅ ነበር፡፡

በ21 ግዛቶች ከነጭ ጋር መጋባት የሚከለክሉ ሕጐች ስራ ላይ ውለው የነበረ መሆኑ የመድልዎው አንድ ገፅታ ሆኖ ይነሳል፡፡
በ2ኛ ደረጃ ዜግነት ከመታየታቸውም በላይ ይፈፀሙባቸው የነበሩ መድልዎች ሰብዕናቸውን የሚፈታተኑ ነበሩ፡፡
አፍሪካ አሜሪካውያኑ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በስነ-ልቦና ይፈፀምባቸው የነበረው ማግለልና ይደርስባቸው የነበረውን ፖለቲካዊ ጭቆና ለማስወገድ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የዘለቀ ትግልና ሙግት አድርገዋል፡፡
የአፍሪካ አሜሪካውያኑን ሁለገብ የመብትና የእኩልነት ትግል ፈር በማስያዝ የመሪነት ሚና ከተጫወቱት መካከል ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር አንዱ ናቸው፡፡
በታሪክ ታላቁ የዋሽንግተን ሰልፍ ተብሎ በሚታወቀው የአፍሪካ አሜሪካዊያኑ ሰልፍ ላይ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ያደረጉት መሳጭ ንግግር ዘመን የማይሽረው ሆኖ ይጠቀስላቸዋል፡፡
ኪንግ እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በተካፈሉበት በዋሸንግተኑ ሠልፍ ያደረጉት ንግግር የትንቢት ያህል ተቆጥሮላቸዋል፡፡
በዚያ ንግግራቸው አፍሪካ አሜሪካውያን ከባርነት ነፃ ካወጣቸው አዋጅ 100 ዓመት በኋላም ነፃ እንዳልሆኑ አነሱ፡፡
ያኔ ላይ ቆመው የወደፊቷ አሜሪካ የዘር መድልዎ ጭቆናና መብት አልባነት የሌለባት እኩልነት የሰፈነባት ሀገር እንደምትሆን ተመኙ፡፡ - “ሕልም አለኝ” አሉ፡፡
ይሄ ንግግራቸው በታሪክም “ሕልም አለኝ” የሚል መጠሪያን አገኘ፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ የዛሬ 54 ዓመት በዛሬዋ እለት ያደረጉት “ሕልም አለኝ” ንግግራቸው በ20ኛው ክፍለ ዘመን በአሜሪካ ለሕዝብ ከተደረጉ ንግግሮች ሁሉ በመሳጭና አነቃቂነቱ የላቀ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ “የሕልም አለኝ” አላማቸውን በሕንዱ የነፃነት አባት ማህተማ ጋንዲ መንገድ በሰላማዊ መንገድ ዓላማቸውን ለማሳካት ያደረጉት ጥረታቸው ዕውቅናው ገዝፎላቸው ከዋሽንግተኑ ሰልፍ ጥቂት ወራት በኋላ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸነፉ፡፡
የመብት ሙግቱ ማርቲን ሉተር ኪንግን ከሕልም አለኝ ንግግራቸው ሦስት ዓመታት በኋላ በተፈፀማባቸው ፖለቲካዊ ግድያ ሕይወታቸውን አጡ፡፡ ሕልማቸው ግን በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለዋይት ሐውስ መብቃት ፍቺ አግኝቷል፡፡
ይሄም ሆኖ በምድረ አሜሪካ ይሄ የዘር ጉዳይ አነጋጋሪቱ አሁንም ድረስ ያልተቋጨ ሆኖ ይገኛል፡፡
@ምንጭ ሸገር 

No comments:

Post a Comment