በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስኳር እጥረት ተፈጥሮ ባለበት ሁኔታ፣ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ መጋዘን ስኳር የጫኑ 125 መኪኖች በኢትዮጵያና ኬንያ ጠረፍ ላይ በምትገኘው ሞያሌ ከተማ ላይ መቆማቸው ታውቛል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የአገሪቱን የስኳር አቅርቦት መሸፈን ተስኖት፣ ስኳር ከው እያመጣ እንደሚያከፋፍል ቢታወቅም፣ 125 መኪኖች እያንዳንዳቸው 400 ኩንታል በድምሩ 50 ሺ ኩንታል ስኳር በመጫን ወደ ኬንያ እያመሩ ሲሆን፣ በገጠማቸው የቴክኒክ ችግር ምክንያት ላለፉት 25 ቀናት ለመቆም ተገደዋል።
ስኳሩ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ መጫኑና ወደ ኬንያ እንደሚጓዝ ይታወቅ እንጅ የማን ንብረት እንደሆነ ወይም ለአገር ውስጥ ገበያ ሳይቀርብ ለምን እንደሚወጣ የታወቀ ነገር የለም።
እነዚህ በብራይት ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት አክሲዮን ማህበር ስር የታቀፉ ከ125 በላይ መኪኖች ወንጅ ፋብሪካ ላይ ለ12 ቀናት ሞያሌ ላይ ደግሞ ለ13 ቀናት ስኳሩን እንደያዙ የቆሙ ሲሆን፣ ወደ ኬንያ ለመግባት በመከልከላቸው ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል።
እያንዳንዱ መኪና በእቁብና በባንክ ብድር የተገዛ እንደመሆኑ እዳችንን መክፈል አልቻልንም የሚሉት ሹፌሮች፣ መኪኖቹ ላለፉት 25 ቀናት በመቆማቸው ስኳሩ በዝናብ ሊበላሽ እንደሚችል፣ እስካሁን ድረስ ለቆሙባቸው የካሳ ክፍያ ማን እንደሚከፍላቸው እንደማያውቁና ኬንያ ውስጥ ከገቡ በሁዋላ ስኳሩን ቶሎ አራግፈው የመመለስ እድላቸው አንስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። ሹፌሮቹ ስኳሩን ከወንጂ ፋብሪካ መጫናቸውን እንጅ የማን እንደሆነ እንደማያውቁ ይናገራሉ።
ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንለት የ ብራይት ድንበር ተሸጋሪ የደረቅ ጭነት አገልግሎት አንድ ሃላፊ መኪኖቹ ስኳር እንደጫኑ ለረጅም ጊዜ ወንጂና ሞያሌ ላይ መቆማቸውን አምነተው፣ ይህም የሆነው የኬንያ ህግ አንድ የጭነት መኪና ከ280 ኩንታል በላይ ጭኖ እንዳይጓዝ ስለሚከለክልና የእኛ መኪኖች ደግሞ እያንዳንዳቸው 400 ኩንታል የጫኑ በመሆኑ ወደ ኬንያ መግባት አትችሉም በመባላችን ነው ብለዋል። መኪኖች የያዙትን ጭነት እንደያዙ ወደ ኬንያ እንዲገቡ እንዲፈቀድላቸው የኬንያ ባለስልጣናትን ለማነጋገር ሙከራ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ግን ስኳሩ እየተቀናነሰ እንዲጫን ስለሚደረግ በቅርቡ መፍትሄ ያገኛል ብለዋል። ስኳሩ የማን ንብረት እንዲሆነና ለምን ከአገር እንደሚወጣ ግን የገለጹት ነገር የለም።
የኢትዮጵያ ወርኃዊ የስኳር ፍላጎት ወደ 600 ሺ ኩንታል የሚጠጋ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ያሉ ፋብሪካዎች በቀን የማምረት አቅማቸው ከ20 ሺ አይበልጥም።
No comments:
Post a Comment