Thursday, August 31, 2017

የስራ ማቆም አድማዎች በትብብር እንዲካሄዱ ጥሪ ቀረበ (ኢሳት ዜና ነሃሴ 25 ቀን 2009 ዓም)


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የስራ ማቆም አድማዎች ብሄራዊ ቅርጽ ይዘው እንዲከናወኑ ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበዋል። በመጪው መስከረም 2 ቀን 2010 ዓም የታቀደው የስራ ማቆም አድማ እውን እንዲሆን ከተፈለገ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሊሳተፉበት እንደሚገባ ኢትዮጵያውያን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በቅርቡ በኦሮምያ ተጥርቶ በነበረው አድማ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊሳተፉ ይገባ እንደነበር የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች ፣ ይህ ባለመሆኑ የህወሃት አገዛዝ ከፋፍሎ ለማጥቃት ተመችቶታል ብለዋል።
ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል፣ “አሁን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዳክሞ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ ትግሉን ለፍጻሜ ለማድረስ ከአካባቢ ፖለቲካ ወጥቶ ብሄራዊ አጀንዳ በመያዝ ሁሉንም ህዝቦች አስተባብሮ ማካሄድ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚኖር ሌላ ወጣት ደግሞ፣ የስራ ማቆም አድማዎች በህዝብ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ በጥንቃቄ ሊካሄዱ እንደሚገባ መክሮ፣ በደንብ በተጠኑ እና ስርዓቱ የገቢ ምንጭ አድረጎ የሚጠቀምባቸውን ተቋማት ለይቶ በእነሱ ላይ አድማ ማድረግ ይገባል ብሎአል። የገዢው ፓርቲ የንግድ ተቋማት የሚያመርቷቸውን ምርቶች ባለመጠቀም፣ እንዲሁም አድማዎች ግልጽ የሆነ ግብ ተደርጎላቸው መካሄድ አለባቸው ብሎአል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ የጠላቶቻችን ሃይል ለይቶ ማወቅ ተገቢ ነው ይላሉ። ትላልቅ መንገዶችን የመዝጋት ጥሪ ሲተላለፍ በጋራ ተግባራዊ ማድረግ አለብን የሚሉት አስተያየት ሰጪው ይህ ካልሆነ የምንከፍለው መስዋትነት ይጨምራል ይላሉ ። አስተያየት ሰጪው አክለው ሲናገሩ “አንዱ ሲመታ ሌላው የሚሰራበት ሁኔታ መቆም አለበት፣ እኛ መናበብ ብንችል ሰዎቹ በትንፋሽ ብቻ ለቀው ይሄዳሉ” ብለዋል። የአጋዚ ወታደሮች አምቡላንሶችን እየተጠቀሙ በህዝብ ላይ እንደሚተኩሱም አስተያየት ሰጪው የአይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል
ከመስከረም በሁዋላ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተባብሰው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ የሚናገረው ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ በአድማው በመንግስትና የግል ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎችም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል። በተለይ መመህራንና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዋነኛ ተባባሪዎችና አስተባባሪዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment