Monday, August 21, 2017

የማስተር ፕላኑ ‹‹ማስተር›› አቶ ማቴዎስ በቃኝ እያሉ ነው

ለዋዜማ ዋና አዘጋጅ የደረሱና እየተከታተልናቸው ያሉ ግርድፍ መረጃዎችን እነሆ እናጋራችሁ
-አቃቤ ህግ የፀሐይ ሪልስቴት ባለቤቶች ማንነት እንዲጣራ አዘዘ
-የትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ባለቤት አሜሪካ ተሸሽገዋል

የማስተር ፕላኑ ‹‹ማስተር›› አቶ ማቴዎስ በቃኝ እያሉ ነው፡፡
በ130 ዓመታት የአዲስ አበባ ታሪክ ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረው 10ኛው የከተማዋ መሪ ፕላን ‹‹አለቃ›› የነበሩት አቶ ማቴዎስ አስፋው ከአዲስ አበባ ካቢኔ መልቀቅ ፈልገዋል እየተባለ ነው፡፡ ማስተር ፕላኑን ካበጁት መሐል በጉልህ ስማቸው የሚነሳው የማስተር ፕላኑ ፊታውራሪ አቶ ማቴዎስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ግል ሥራቸው ማዘንበል ፈልገዋል ይላሉ ምንጮች፡፡ ኾኖም ለከንቲባው በይፋ የሥራ መልቀቂያ ማስገባት አለማስገባታቸው አልታወቀም፡፡ Image may contain: 1 person, sitting and indoor
ከጸደቀ ገና ሁለተኛ ወሩን እንኳ ያላገባደደው የከተማዋ መስተር ፕላን አያሌ ውጣ ውረዶችን አልፎ ነው ለዚህ የበቃው፡፡ 
አዲስ አበባ ባልጸደቀ ማስተር ፕላን ቢያንስ ሦስት ዓመታት ተመርታለች፡፡ ብዙ ፖለቲካዊ ቀውስ ካስከተለ በኋላ ሐምሌ 6፣ 2009 በዕለተ ሐሙስ የጸደቀው ማስተር ፕላን ከተማዋን ከ10 ወደ 13 ክፍለ ከተሞች ይሸነሽናታል፡፡ የወደጎን መስፋፋት ቀርቶ የጥግግት እድገት ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ በዚህም ዘለግ ያሉ ሕንጻዎች እንዲገነቡና ብዙዎቹ ሕንጻዎች ከ30 እስከ 60 በመቶ ወለላቸውን ለመኖርያ ቤት እንዲያዉሉ ያስገድዳል፡፡
አቶ ማቴዎስ የማስተር ፕላኑን ዝግጅት ብቻም ሳይሆን እንዲተገበር ጥበቃ የሚያደርገው ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ አስተዳደር የጸደቀ ማስተር ፕላንን መቆጣጠር ብቻ ዓላማውን ያደረገ የኮሚሽን ማሥሪያ ቤት ኖሮ አያውቅም፡፡
ከፍተኛ የኪነ ሕንጻና ከተማ አስተዳደር ባለሞያና የአማካሪ ድርጅት ባለቤት የሆኑት አቶ ማቴዎስ ምን ሆንኩኝ ብለው የአዲስ አበባ ካቢኔን ለመሰናበት እንደፈለጉ ምንጫችን የሚገምተው ነገር የለም፡፡ 
=================

አቶ ጌታቸው አምባዬ የፀሐይ ሪልስቴት ባለቤቶች ማንነት እንዲጣራ አዘዋል
ከፀረ ሙስና ትግሉ ጋር በተያያዘ የከፍተኛ አመራሩ የማይዳሰስ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የተባለውና በቻይናዎች ባለቤትነት እንደተያዘ የሚነገርለት ግዙፉ የፀሐይ ሪልስቴት የማንነት ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ ከሕዝብ በደረሰ ጥቆማ ከቻይኖቹ ጀርባ የኢህአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት ሳይኖሩበት አልቀረም የተባለው ይህ ኩባንያ በሁለት የቻይና ግዙፍ ኩባንያዎችና በአንድ ቻይናዊ ሚሊየነር ጥምረት እንደተመሠረተ ነው የሚታወቀው፡፡
ኾኖም እውነታው ሌላ ሊሆን ይችላል በሚል የልዩ አቃቢ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ ማንኛውም ፀሐይ ሪልስቴትን የተመለከተ መረጃ አንድም ሳይቀር እንዲላክልኝ ሲሉ አዘዋል ይላሉ ውስጥ አዋቂዎች፡፡
በ30ሺ ስኩዌር ካሬ ላይ ያረፈውና 13 ግዙፍ የአፓርትመንት ሕንጻዎችን የያዘው ፀሐይ ሪልስቴት የሚገኘው በምሥራቅ አዲስ አበባ ሲኤምሲ አደባባይ አካባቢ ነው፡፡ ኩባንያው እነዚህን 13 የመኖርያ፣ የገበያ፣ የቢሮና የመዝናኛ ሕንጻዎችን ለማቆም የመደበው ገንዘብ 3 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር መሆኑ የኩባንያውን አቅምና ጉልበት ያመላከተ ነበር፡፡ 13ቱ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች በድምሩ 650 ቤቶችን በውስጣቸው ይይዛሉ፡፡
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2012 እንደተመሠረተ የሚነገረው ፀሐይ ሲጂሲኦሲ (CGCOC) የተባለ የቻይና ኩባንያና ሬድ ፎክስ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ካምፓኒ የሚባል ሌላ የቻይና ኩባንያዎች በጥምረት የመሠረቱት ነው፡፡ከሁለቱ ኩባንያዎች ሌላ Qian Xiao ተብለው የሚጠሩ ቻይናዊ ሚሊየነር በዚህ ድርጅት ውስጥ የአንበሳው ድርሻ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ሲጂሲኦሲ (CGCOC) ለኢትዮጵያ እንግዳ ኩባንያ አይደለም፡፡ በጀሞ አካባቢ ሀንሰም የመስታወት ፋብሪካን ያንቀሳቅሳል፡፡ የአዳማ የንፋስ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታን ያከናወነውም ይኸው የቻይና ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 
ፀሐይ ሪልስቴት ለአንድ ካሬ ብቻ 30ሺ ብርና ከዚያ በላይ የሚያስከፍል፣ አንድን 200 ካሬ ስፋት ያለው ባለ ሦስት መኝታ ቤት በ6 ሚሊዮን ብር የሚሸጥ የከፍተኛው ማኅበረሰብን ብቻ ትኩረት ያደረገ የሪልስቴት ኩባንያ ነው፡፡ ኾኖም ኩባንያው ከሞላ ጎደል የመኖሪያ ሕንጻዎቹን ቢያጠናቀቅም አሁንም ድረስ 40 በመቶ የሚሆነው መኖርያ ቤት በተፈለገው ፍጥነት እንዳልተሸጠለት ይነገራል፡፡
የዚህ ኩባንያ ባለቤቶች ቻይናውያን ስለመሆናቸው፣ ኩባንያው ውስጥ የተሰገሰጉ ከፍተኛ የኢህአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት ስለመኖር አለመኖራቸው ይጣራል ተብሏል፡፡ በ2014 መስከረም ወር የኩባንያውን የግንባታ ሥራ መርቀው ያስጀመሩት የኢፌድሪ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ነበሩ፡፡
============

የትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ባለቤት አቶ ወንድወሰን መስፍን አሜሪካ ተሸሽገዋል
ለ55 ሰዎች እስራት፣ ለ15 ግዙፍ ኩባንያዎች እግድ፣ ምክንያት የሆነው አዲሱ የጸረ ሙስና ዘመቻ ባለሐብቶችን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሳይከት አልቀረም፡፡ ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዕውቅ የባለሐብቶች ሽሽት ተጠናክሮ መቀጠሉ፡፡ 
በለስ ቀንቷቸው ቀደም ብለው ለሥራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ያቀኑት የትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ (ቲሲቲ) ባለቤትና መሥራች ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሚሊየነር አቶ የወንድወሰን መስፍን ባሉበት አሜሪካ ተሸሽገዋል ሲሉ የዋዜማ ታማኝ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ እርሳቸው የፈጠሩት ኩባንያቸው በቅርቡ በፍርድ ቤት ማንኛውንም ገንዘብና ንብረት እንዳይንቀሳቀስ እግድ ከተጣለባቸው 15 ግዙፍ ኩባንያዎች አንዱ ሆኗል፡፡
የዕውቁ የራስ መስፍን ልጅ እንደሆኑ የሚነገረው አቶ ወንድወሰን መስፍን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1978 በምድረ አሜሪካ ካሊፎርኒያ የተመሠረተ እድሜ ጠገብ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ በአይቲ ላይ የሚሳተፈው ኩባንያቸው ወደ አፍሪካ እግሩን ያስገባው በናይጄሪያ ዕውቁን የአሜሪካ የአይቲ ኩናንያ ኦራክል ኮርፖቴሽንን በመወከል እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚያም የተቀናጀ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አስተዳደርን ለሌጎስ መስተዳደር በማቀበል ስኬታማ ሥራ ሠርቷል ተብሏል፡፡
ኢትዮጰያ ውስጥ ቢሮ ከከፈተ በኋላም በአቶ ግርማ ዋቄ ዘመን የኢትዮጵያ አየር መንገድን የአይቲ ሥራ ለማከናወን የሦስት መቶ ሚሊዮን ብር ጨረታ ላይ መሳተፉ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የጀርመኑ ግዙፍ ሳፕ (SAP)፣ በፋየር ፌክስ (FairFax) ተወክሎ የነበረ ሲሆን፣ የአሜሪካው ግዙፉ ኦራክል በአቶ ወንድወሰን ኩባንያ ቲሲቲ ተወክሎ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ኦራክል ለጨረታ የቀረበው የገንዘብ ጣሪያ መጠን እኔን አይመጥነኝም በሚል ከጨረታው ራሱን ማግለሉ ይታወሳል፡፡
ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ 500,000 ብር ጉቦ በማቀባበል የተጠረጠሩትና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት አቶ ኢዮብ በልሁ የዚሁ ኩባንያ ሠራተኛና የአቶ ወንድወሰን መስፍን የቅርብ ረዳት እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
የአቶ ወንድወሰን መስፍን ኩባንያ ቲሲቲ ለቡና ባንክ፣ ለንግድ ባንክ፣ ለቀድሞው የኮንስራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የአይቲ ሥራዎችን የሠራ ሲሆን አቶ ወንድወሰን ከአገር ከመሸሻቸው በፊት ኩባንያው ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ተከፍሎት የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር ቴክኖሎጂን ተግባራዊ የሚያደርግ የአይቲ ሥራ እያከናወነ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱን የተቀናጀ ፋይናንስ አስተዳደር ሥራ የፓይለት ፕሮጀክት ሠርቶ ያስረከበውም ይኸው ድርጅት ነበር፡፡
በራስ መስፍን ልጅ በአቶ ወንድወሰን መስፍን ጦስ ዘብጥያ የተወረወሩት የገንዘብና ትብብር ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አለማየሁ ጎጆን ብቻ አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም አቶ በትረወርቅ ታፈሰ የተባሉና የቀድመው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩም ሰው ይገኙበታል፡፡
እኚህ ምክትል ፕሬዚዳንት የባንኩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ሳሉ ለአቶ ወንደወሰን መስፍኑ ትራንስ ናሽናል ኮምፒውተርስ ሐሰተኛ የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ኤልሲ) ከፍተዋል በሚል ነበር የተከሰሱት፡፡ በዚህ በሐሰት እንደተከፈተ በተነገረ ሰነድ 12 ሚሊዮን ብር ወደ ባንኩ ሳይመለስ አቶ ወንድወሰን እጅ ቀልጦ ቀርቷል ተብሏል፡፡
አቶ ወንድወሰን መስፍን ከቡና ባንክ ጋርም ተመሳሳይ የማጭበርበር ተግባር እንደፈጸሙ ይጠረጠራሉ፡፡ ከርሳቸው ጦስ ጋር ተያይዞም በቅርቡ ወደ ዘብጥያ የሚወረወሩ የተለያዩ የግል ባንክ ኃላፊዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም የዋዜማ ምንጮች ይጠረጥራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment