በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዘፈቀደ የሚጣለውን ግብር በመቃወም የሚደረጉ አድማዎች እንደቀጠሉ ነው። በወልድያ አድማው ለ4ኛ ቀን ሲቀጥል በኮምቦልቻም ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎአል። በአዋሳ ደግሞ የተሽከርካሪዎች አድማ መጀመሩ ታውቋል። በመቀሌም ባጃጅ ተሽከርካሪዎች አድማ መተው ውለዋል።
በወልድያ የሚካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ተቃውሞውን በማስፈራራትና በሽምግልና ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት አልሳካ ሲል ዋና ዋና የሚባሉ ነጋዴዎች እየተያዙ በመታሰር ላይ ናቸው። እስካሁን ባለን መረጃ 7 ነጋዴዎች በኮማንደር ስለሺ ትዕዛዝ መታሰራቸው ታውቋል።
በኮምቦልቻም አድማው ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን፣ አድማውን የቀን ሠራተኞች ጭምር በመቀላቀላቸው ሁኔታው ያስፈራው መንግስት የክልሉን አድማ በታኝ በከተማዋ ማሰማራቱ ታውቋል።
በትናንትናው ዕለት የረቡዕ ገበያ ሳይውል በመቅረቱና ነጋዴዎች በማደማቸው ካድሬዎችና ፖሊሶች በየነጋዴዎች ቤት እየዞሩ ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ሲያስፈራሩ ሕዝቡ በአንድ ላይ በመሰባሰብ “ምንድነው እያላችሁ ያላችሁት? ለመሆኑ ይች ሀገር የማናት?” በሚል ጥያቄ እንዳፋጠጧቸውና ያንን ተከትሎ አድማው እየተባባሰ መምጣቱ ታውቋል።
አድማው ከቤት ውስጥ ያለመውጣት በሆነበት ሁኔታ አድማ በታኝ ኃይል በከተማዋ ምን ሊበትን እንደተሰማራ አልገባንም ሲሉ ነዋሪዎች ገልፀዋል።
No comments:
Post a Comment