በኦሮሚያ ወጣቶች የተጠራውን ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ በመላው ኦሮሚያ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሳተፉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/አለምአቀፍ ድጋፍ ቡድን ጥሪ አቀረበ።
ከነገ በስቲያ እሮብ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየውና በመላው ኦሮሚያ የተጠራው አድማ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የግብር ጫናን በመቃወምና በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በልዩ ፖሊስ የተጨፈጨፉ ሰዎችን ለማስታወስ ነው።
የኦፌኮ አለምአቀፍ ቡድን አስተባባሪ አቶ ኔጌሳ ኦዶ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት በኦሮሚያ ባልተቀናጀ ሁኔታ ሲደረግ የነበረው ተቃውሞ በአንድ ወጥ ሁኔታ እንዲካሄድ ከመጪው ረቡእ ጀምሮ ለ5 ቀናት ተጠርቷል።
በኦሮሚያ የወጣቶች ሕብረት ቄሮ የሚል ስያሜ አለው።ቄሮ ማለት በኦሮምኛ ወጣቶች የሚል ትርጉም እንዳለው ይነገራል።
እናም በቄሮ የተጠራው ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ ከዚህ በፊትም በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በአገዛዙ የሚፈጸሙ ግፍና በደሎችን በመቃወም ባልተቀናጀ ሁኔታ ሲካሄድ መቆየቱን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ አለም አቀፍ ድጋፍ ቡድን አስተባባሪ አቶ ኔጌሳ ኦዳ ይገልጻሉ።
አቶ ኔጌሳ ኦዳ እንደሚሉት ከነገ በስቲያ ረቡእ ጀምሮ ለ5 ቀናት የሚካሄደው የኦሮሚያ ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ ግን ሁሉንም አካባቢዎች የሚያዳርስና ለሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች የተደረገ ጥሪ ነው።
በኦሮሚያ ያለአግባብ የተጫነውን የግብር እዳ እንዲሁም በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በልዩ ፖሊስ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ለማስታወስ እንደሆነም አቶ ኔጌሳ ኦዳ ገልጸዋል።
እናም መላው የኦሮሚያ ነዋሪዎች ነጻነትን ለማግኘት ዋጋ መክፈል እንዳለባቸው የኦፌኮ አለምአቀፍ ድጋፍ ቡድን አስተባባሪ ጥሪ አድርገዋል።
በኦሮሚያ የተጠራው አጠቃላይ አድማ በሕዝቡ ድጋፍ አግኝቶ ተግባራዊ ከሆነ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ክስረት ሊያስከትልበት እንደሚችል ተንታኞች ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment