Thursday, October 1, 2015

ዜና (የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ)

ዜና
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ)
‪#‎በህወሓት‬ መራሹ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የስንብት ጥያቄ የሚያቀርቡ አባላት ከቀን ወደቀን ቁጥራቸው እጅግ በጣም እያሻቀበ እየመጣ መሆኑ ታወቀ፡፡
‪#‎በክርስትና‬ እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓል ዕለት የጎንደር ከተማ "የፈራ ይመለስ" የሚል ፅሁፍ የታተመባቸው ቀያይ ቲሸርቶች በለበሱ ወጣቶች ተጥለቅልቃ ከፍተኛ የሆነ አመፅን አስተናገደች፡፡
‪#‎በተኸለ‬ አምባ እና በሌሎች የወልቃይት በርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎች አዝመራቸውን እንዳይሰበስቡ በፌደራል ፖሊስ በመታገዳቸው ጥይት ያታኮሰ ከፍተኛ ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ ውጥረቱ አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡
===================================================
በህወሓት መራሹ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የስንብት ጥያቄ የሚያቀርቡ አባላት ከቀን ወደቀን 
ቁጥራቸው እጅግ በጣም እያሻቀበ እየመጣ መሆኑ ታወቀ፡፡
መቶ በመቶ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ከአንድ አካባቢ በወጡ የህወሓት አባላት ድኩማን ወታደራዊ አዛዦች ብቻ ቁጥጥር ስር ሆኖ በከፋ አስተዳደራዊ በደል እየማቀቀ በዘር ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው ብዙኃኑ የመከላከያ ሰራዊት የሰባት ዓመታት አገልግሎት የኮንትራት ጊዜውን የጨረሰው የስንብት ጥያቄ ያዘሉ ደብዳቤዎችን ያለማቋረጥ እያስገባ በየእርከኑ የሚገኙ የመከላከያ የአስተዳደር ቢሮዎች በማመልከቻ ማዕበል ክፉኛ እየተመቱ የሚገኙ ሲሆን የአገልግሎት ጊዜው አልሞላ ብሎት የስንብት ደብዳቤ ማስገባት ያልቻለው የሰራዊቱ አባል ደግሞ የሰቀቀን ኑሮውን ለማሳጠር በራሱ እርምጃ እየወሰደ ያለምንም ፋታ እየከዳ ነው፡፡
ድኩማኖቹ ህወሓታዊያን የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዦች የአገልግሎት ጊዜ ኮንትራታቸውን ጨርሰው የስንብት ደብዳቤ ለሚያስገቡት በስርዓቱ የተንገሸገሹ እና በእጅጉ ተማረው ተስፋ የቆረጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሰራዊቱ አባላት "ከመከላከያ ሰራዊቱ ፈፅሞ መልቀቅ አይቻልም..." የሚል አሉታዊና ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም ድኩማኖቹ ወታደራዊ አዛዦች የአገልግሎት ዘመኑን የጨረሰ ማንኛውም የመከላከያ ሰራዊት አባል በአሁኑ ሰዓት የስንብት ጥያቄ የማቅረብ መብት እንደሌለውና አሰናብቱኝ ብሎ በሚያመለክት ላይ እርምጃ የሚወስዱ መሆናቸውን ጠንከር ያለ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
ከየማሰልጠኛው ተመርቀው በየጊዜው ሰራዊቱን የሚቀላቀሉ አዳዲስ አባላት ብዙም ሳይቆዩ ስለሚከዱ "ነባሩ ሰራዊት" ከተሰናበተ በእነሱ ላይ ቅንጣት ታክል እምነት ስለሌላቸው በአገዛዙ ላይ የከፋ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል በማብራራት በማሳመን ለማባበል እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡
የህወሓት አገዛዝ በየጊዜው ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚከዱትን አባላት ከየተሸሸጉበት አድኖ የመያዝ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
በየጊዜው ያለምንም ፋታ የሚከዱ የሰራዊቱ አባላት ወደየ ትውልድ ቀያቸው አይደለም የሚመለሱት፤ ገሚሶቹ ከነትጥቃቸው በረሃ ወርደው ይሸፍታሉ፤ አብዛኞቹ የነፃነት ትግሉን ይቀላቀላሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ድምበር ተሻግረው እግራቸው ወደመራቸው ይሰደዳሉ፡፡
በአጠቃላይ አሁን እጅግ በጣም በርካታ አባላት ላነሱት የስንብት ጥያቄ የተሰጠውን "አይቻልም" የሚል ድኩማን ህወሓታዊ ወታደራዊ አዛዦች ምላሽ ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ሰፍኖ የቆየውን ውጥረትና አለመተማመን ከጫፍ አድርሶት አገዛዙ ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ የሆነ ከባድ አደጋ እያንዣበበ ይገኛል፡፡

በክርስትና እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓል ዕለት የጎንደር ከተማ "የፈራ ይመለስ" የሚል ፅሁፍ የታተመባቸው ቀያይ ቲሸርቶች በለበሱ ወጣቶች ተጥለቅልቃ ከፍተኛ የሆነ አመፅን አስተናገደች፡፡
የጎንደር ከተማ ለውጥ የሻቱ ወጣቶች ከ500 በላይ የፈራ ይመለስ የሚል ፅሁፍ የታተመባቸው ቀያይ ቲሸርቶች አሳትመው በማሰራጨት በጎንደር በከፍተኛ ድምቀት በየአመቱ መስከረም 17 ቀን የሚከበረውን የመስቀል በዓል ለመታደም ደመራው ወደ ሚለኮስበት መስቀል አደባባይ ይተማሉ፡፡
ቀጥሎም ደመራው የሚለኮስበት መስቀል አደባባይ ከምዕመኑ ቁጥር ባልተናነሰ ሁኔታ በፌደራልና በልዩ ኃይል የህወሓት ፖሊሶች ተወሮ በማግኘታቸው የደመራውን በተለመደው ሰዓት አለመለኮስ በምክንያትነት በመጠቀም በአምባገነኑ የህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ላይ ተቃውሟቸውንና በጉልበት አንገዛም ባይነታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልፀዋል፡፡ 
የህወሓት ፌደራልና ልዩ ኃይል ፖሊሶች ለአገዛዙ ያላቸውን ጥላቻና ተቃውሞ የገለፁትን "የፈራ ይመለስ" ያሉ ባለቀያይ ቲሸርት የጎንደር ወጣቶችን በቆመጥና በአፈሙዝ በብርቱ በመደብደብ ተቃውሞውን ለማርገብ ሞክረዋል፡፡ በመሆኑም በወጣቶቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ ምዕመናን ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የከተማዋ ወጣቶች እና ነዋሪዎች ጭምር በህወሓት ፖሊሶች እየታፈሱ ወደ ዘብጥያ ተወስደዋል፡፡ በተለይም ደግሞ "የፈራ ይመለስ" የሚል ቀያይ ቲሸርቶች የለበሱ ወጣቶች በልዩ ሁኔታ እየታደኑ ታፍነው እየተወሰዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከ100 በላይ የሚሆኑ የጎንደር ወጣቶች በልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ ብቻ ታጉረው ከፍተኛ ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ ተረጋግጧል፡፡

በተኸለ አምባ እና በሌሎች የወልቃይት በርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎች አዝመራቸውን እንዳይሰበስቡ በፌደራል ፖሊስ በመታገዳቸው ጥይት ያታኮሰ ከፍተኛ ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ ውጥረቱ አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡
በወልቃይት የሚገኙ ገበሬዎች ማንኛውም ሰው ተነስቶ የሚያርሰውን በተለምዶ "ሞፈር ዘመት" እየተባለ የሚጠራውን መንገድ ተጠቅመው በግንቦትና በሰኔ ወራት ጫካ መንጥረው ምድረ በዳውን በማረስ የተለያዩ አዝዕርቶችን በተለይም ሰሊጥ ዘርተው ያበቀሉ ሲሆን አሁን በመኸር ክወና ላይ ተሰማርተው ባሉበት የህወሓት አገዛዝ ደን ጨፍጭፋችሁ አርሳችኋል በሚል ተልኮሻ ምክንያት ፌደራል ፖሊስ በየማሳቸው በማሰማራት ለማገድ በመሞከሩ ነው "ግንቦት እና ሰኔ ገና መሬቱን ማልማት ስንጀምር ከተቆረቆራችሁ ለምን አልከለከላችሁንም?" በሚል ህዝቡ በአንድነት ተነስቶ ግጭት የተቀሰቀሰው የህወሓት ፌደራል ፖሊሶች ተክላይ የተባለውን ገበሬ ከማሳው አስረው ወስደው አደባይ ላይ በመረሸናቸው የዘርባቢትና እድሪስ ቀበሌዎች ነዋሪዎች በአንድነት "ሆ" ብለው ተነስተው ፖሊሶችን ትንቅንቅ ገጥመዋቸዋል፡፡
በተለይም የአካባቢው ሚሊሻዎች ከህዝቡ ጎን በመቆም በፌደራል ፖሊሶች ላይ ተኩስ ከፍተው ውጊያ በመግጠም ሁለት ፖሊሶችን አቁስለዋል፡፡

በአካባቢው የታጠቁ ሚሊሻዎችና ገበሬዎች የደረሰ አዝመራቸውን እንዳይሰበስቡ ለማገድ በየማሳው በተሰማሩ ፌደራል ፖሊሶች መካከል የተከፈተው ጦርነት ለማስቆም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ኃይል በአካባቢው ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ግጭቱ የባሰውን ተቀጣጥሎ የሰፈነውን ውጥረት እንዲያይል አደረገው እንጂ ሊያረግበው እንዳልቻለ የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች ገልፀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment