የህወሓት አገዛዝ የሚቆጣጠረው መከላከያ ሰራዊት አባላት የሆኑ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቁስለኛ ወታደሮች ዳሽ-6 በተባለ አውሮፕላንና ኤም.አይ-17 ሄሊኮፕተር ከሶማሊያ አየተጫኑ ድሬ ደዋ ላይ በመራገፍ ላይ ናቸው (የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ) ራሱን በመንግስትነት ስም የሚጠራው የማፍያው ቡድን ህወሓት የምዕራባዊያንን ቁሳዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ በማግኘት ስልጣኑን ለማደላደል ሲል ብቻ ከ10 ዓመታት በፊት ማለትም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ የሆኑ ዕልፍ አዕላፍ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ያለማቋረጥ ወደ ሶማሊያ በረሃማ ምድር እያስገባ እጅግ በጣም አሰቃቂ ለሆነ እልቂት እየዳረጋቸው ይገኛል፡
፡ የህወሓት አመራሮች የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረትን ከሁለት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ አፈራርሰውት ለቀው እንደሚወጡ ለህዝቡ ገልፀው ወደ ምድራዊ ሲኦል ወደሆነችው ሶማሊያ ጦር ጭነው ያስገቡ ሲሆን ነገር ግን አልሸባብ የተባለ ሌላ ፅንፈኛ ቡድን ፈጥረው ምስኪን ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን ከማይወጡበት የጦርነት አዙሪት ውስጥ ከተዋቸው ለድፍን 10 ዓመታት ሰቅጣጭ የሞት ገፈትን ሲግቷቸው ቆይተዋል፡፡ ቀጠናውንም የባሰ አለመረጋጋት እንዲሰፍንበት አድርገውታል፡፡ በዶላር ፍቅር ዓይኑ የታወረው የህወሓት አገዛዝ ከ10 ዓመታት በፊት ጦሩን ወደ ሶማሊያ ሲያስገባ እሱ እንደሚነግረን መጀመሪያ ላይ ጦርነት የገጠመው ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት ከሶማሊያ ጎሳዎች መካከል በጠንካራነቱና በታላቅነቱ ከሚታወቀው የሃውዬ ጎሳ ጋር ነበር፡፡ በመሆኑም በገብረ ዲላ እና በሌሎች ህወሓታዊ ድኩማን የጦር አዛዦች የሚመሩት 43ኛ እና 44ኛ ክፍለ ጦር ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል፤ መሪዎቹ ጭነዋቸው የሄዱትን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ለሶማሊያ በረሃ ገብረው አምስትና ስድስት ወታደሮችን ብቻ አስከትለው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ ሞቃዲሹ ውስጥ አንድ የሃውዬ ጎሳ አባል በአንድ ህንፃ ውስጥ መትረየስ ጠምዶ ቢያንስ አንድ ሻምበል ጦር ብቻውን ጨርሷል፡፡ የድሃ ልጆች ለኢትዮጵያ ምንም አይነት ጠቀሜታ በሌለው ጦርነት በክንቱ ደማቸው ፈሶ ረግፈው ያለቀባሪ ቀርተዋል፡፡ አሁንም በዘግናኝ ሁኔታ መገደላቸው ቀጥሏል፡፡ ሬሳቸውም እንዳያርፍ ተፈርዶበት በየጎዳናው በገመድ ታስሮ ሲጎተት ታይቷል፡፡ ምንም እንኳን አሮጌዎቹ የአየር ኃይል አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች የወታደር ሬሳና ቁስለኛ ወደ ድሬ ደዋ ያለማቋረጥ ማመላለስ የጀመሩት ካለፈው 2007 ዓ.ም ጀምሮ ቢሆንም አሁን አሁን ደግሞ የባሰውኑ ስራ በዝቶባቸዋል፡፡ ዳሽ-6 አውሮፕላንና ኤም.አይ-17 ሄሊኮፕተር በቁስለኛ ወታደሮች ጥቅጥቅ ብለው ተሞልተው ከወደ ሶማሊያ እየመጡ ድሬ ደዋ ላይ በማራገፍ ላይ ናቸው፡፡ ከሶማሊያ በአውሮፕላንና በሄሊኮፕተር ተጭነው ድሬ ደዋ ላይ የተራገፉት ቁስለኛ የሰራዊቱ አባላት ወደ ሐረር ወታደራዊ ሆስፒታል እየተወሰዱ በመግባት ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም የሐረሩ የመከላከያ ሆስፒታል ከአቅሙ በላይ በቆስለኞች መሞላቱን የሆስፒታሉ ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ለቁስለኞች የሚደረገው ህክምና እና እንክብካቤ በራሱ ከአድሏዊነት የፀዳ እንዳልሆነ ተጎጅዎች ቅሬታቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ የህወሓት ታጋዮች የነበሩ የሰራዊቱ አባላት ሆዳቸውን በቆረጣቸው ቁጥር ደቡብ አፍሪካና ሳዑዲ አረቢያ ድረስ እየሄዱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየታከሙ ተገደው የሶማሊያው ጦርነት ውስጥ ተማግደው ስጋቸው በእሳት ተጠብሶ የተመለሱት ወታደሮች ግን ጦር ኃይሎች ሆስፒታልን እንኳን በዓይኖቻቸው የማየት እድላቸው የጠበበ እንደሆነ እና አካላቸውን ላጡትም ምንም አይነት የሞራልም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው ብሶታቸውን ዘርዝረዋል፡፡ በተጨማሪም ሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ የአየር ኃይል አባላት በአውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች ብልሽትና እንዲሁም የመለዋወጫ እጥረት ምክንያት ስራ ፈትተው ለረጂም ጊዜ በመቀመጣቸው በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያዘለ ጥያቄ በአንድነት አንስተዋል፡፡ የአየር ኃይሉ ምክትል አዛዥ ጀነራል ማዕሾ ሐጎስ ወደ ቦታው አምርቶ ጥያቄ ያነሱ አባላትን የማረጋጋት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ለተነሳው ጥያቄ ተገቢ መፍትሄ ባለመሰጠቱ አሁንም ቅሬታው ባለበት ቀጠለ እንጂ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ የእነዚህን ሶማሊያ ዘማቾች የአየር ኃይል አባላት ሚስቶች የምስራቅ አየር ምድብ አዛዥ የሆነው ኮሎኔል አበበ ተካ በየተራ እያማገጠ እንደሚገኝም ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን ገልፀውልናል፡፡ በአጠቃላይ ሰሞኑን በኢትዮጵያና በሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር ላይ በህወሓት መራሹ መከላከያ ሰራዊትና በአልሸባብ ተዋጊዎች መካከል ከባድ ጦርነት እንደተካሄደ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48061#sthash.9qDzLxmr.dpuf
No comments:
Post a Comment