ታሪኩ አባዳማ – ጥቅምት 2008
ሰሞኑን በ ዩቱብ የተቀነባበረ የ ‘(ህዳሴ)’ ዘገባ በወያኔ ፓርቲ ተሰራጭቶ ሳታዩ አልቀራችሁም። ሙስና ላይ ያነጣጠረ ፣ በሹማምንቱ ሌብነት ዙርያ ያጠነጠነ ፤ ኪራይ ሰብሳቢነትን በጥልቀት የመረመረ የወያኔ ቱባ ሹማምንት ውይይት መሆኑ አንዳንዶችን እንዳስገረመ ጭምር የተነገረለት ዘገባ። አገሪቱ የተዘፈቀችበትን ምግባረ ብልሹ አስተዳደር በጨረፍታ ያመለከተ ፣ ‘ጥናታዊ’ ሪፖርት ላይ ለመምከር በከፍተኛ ፖለቲካ መሪዎች መካከል የተደረገ ግልፅ አውጫጪኝ ፣ አፈርሳታ በ ዩቱብ ቀርቧል… የሹማምንት አፈርሳታ።
ዘገባውን ያገኘሁት TPLF cannot be reformed; like apartheid, it should be dismantled” “ህወሓት በጥገናዊ ለውጥ ሊቃና አይችልም። እንደ አፓርታይድ ከሥሩ ነቅሎ መጣል እንጂ” እያለ ትናንት ግንባር ቀደም መፈክር ሲያሰማ ከነበረው ድረ-ገፅ ኢትዮሚዲያ ላይ ሲሆን ምንጩ ደግሞ የዚያው የወያኔው ዜና አውታር ዋልታ መሆኑ ተጠቅሷል። ኢትዮሚዲያ ከዋልታ ተቀብሎ ዘገባውን ሲገልፅ ‘እነሆ ጠ/ሚኒስትሩ ተሀድሶ reform ለማድረግ ተነሱ’ የሚል ምርቃት አክሎበታል። ሪፖርቱን አይተው ‘ወያኔ ሙስና ላይ ሊዘምት ነው… በጎ አዝማሚያ ነው’ የሚል አስተያየት ሰጪዎችም ብቅ ብለዋል። የአመለካከት አድማስ ስፋቱ የፈቀደለትን ያህል ነገሮችን ግራ ቀኝ አይቶ የመሰለውን ሀሳብ መሰንዘሩ መልካም ቢሆንም ለወያኔ ተራ ፕሮፓጋንዳ ትኩረት ሰጥቶ ለውጥ ሊመጣ ነው ብሎ ተስፋ ማድረግ ግን ተጃጅሎ ማጃጃል ነው።
ሹማምንቱ ተሰብስበው አስተዳደራቸው ምን ያህል በብልሹነት የዘቀጠ መሆኑን በተውኔት መልክ ሲያሳዩን የታዛቢ ተውኔት የማቀነባበር ተልእኮ ያላቸው ደግሞ ‘ለውጥ ሊመጣ ነው ፣ ሌቦች ሊመነጠሩ ነው’ ይሉናል።
የመረጃው ምንጭ ዋልታ ከደረቅ ወይራ የተጠረበ መሆኑን ለማረጋገጥ ከመካከላችን ምስክሮች እያፈላለገ ይመስላል… እኛ ደግሞ ከእርጥብ ጮርቃ ብሳና የተተከለ ዋልታ ከዝናብ አያስጥልም ብንል ጨለምተኛ አያሰኘንም። ለዚህም ብዙ ነገር መጥቀስ ይቻላል።
ወያኔ ይህን አፈርሳታ ለመጥራት የተገደደባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ ብዬ አምናለሁ። ዋናው ግን እጅጉን እየተባባሰ የመጣው አስተዳደራዊ ኢፍትሀዊነት ፣ በየሹማምነቱ ቢሮ ደጃፍ ፣ በወህኒዎች እና በይስሙላ ፍርድ ቤቶች እየተፈፀመ ያለው ግፍ ፤ የባለስልጣናት እና ደላሎች ኑሮ ከተራው ህዝብ ዕለታዊ ህይወት እጅጉን የራቀ እየሆነ መቀጠሉ ፣ ጣሪያ የነካው የኑሮ ውድነት የብዙሀኑን ኑሮ ጨለማ ማድረጉ ለአብነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።
የሁሉም ክልል ነዋሪ የሆኑ ብዙሀን ዜጎች ከወሬ ያለፈ አንዳችም ጥቅም ማየት አለመቻላቸው እና ይብስ ብሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለረሀብ መጋለጣቸው አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን ሲነገር ከቆየው የደብል ዲጂት እመርታ ወሬ ጋር የማይጣጣም ስለመሆኑ ውነቱ እያገጠጠ በማጋለጡ። ፈረንጆቹ ዳሜጅ ኮንትሮል የሚሉት አይነት እርምጃ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። እነኝህን ሁኔታዎች አስመልክቶ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያ በያዘችው መንገድ ከቀጠለች ብርቱ ፈተና እንደሚገጥማት በየጊዜው የሚያወጡት መረጃዎች ብዛት እና አይነት የውጭ ወዳጆችንም ጭምር ለትዝብት መዳረጉ አሳሳቢ ሆኗል።
በመሰረቱ እነኝህ ወያኔ በጥናት ደረስኩባቸው ያላቸው አፀያፊ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ለህዝብ እንግዳ አይደሉም። ጥናቱ የጠቃቀሳቸው ናሙና የሙስና ድርጊቶች ህዝቡ ዕለት ተለት ሲታዘባቸው ሀያ ሶስት ዓመታት የቆዩ ፀሀይ የሞቃቸው ነገሮች ናቸው። አንድ መንግስት ዘቅጦ እዚህ ደረጃ የሚደርሰው ስርዓቱ አንዳችም የተጠያቂነት ሆነ ግልፅነት ባህሪ የሌለው መሆኑን ጭምር ያረጋግጣል። ጥናት አስፈላጊ የሚሆነው እንቆቅለሽ ለመፍታት እንጂ አደባባይ የወጣን ጉዳይ በሰነድ ከሽኖ ለማቅረብ አይደለም። የአዋጁን በጆሮ ሹክ ሊሉን አሰፍስፈው ሸንጎ መቀመጣቸው ምን ያህል አፍረተ ቢስ መሆናቸውን ይመሰክራል።
ራሱ ወያኔ በዘረጋው የዘር እና ጎጥ ፖለቲካዊ ፖሊሲ የተነሳ እንዲህ አይነቱ ለጆሮ የሚቀፍ ዝቅጠት መከተሉ ግልፅ ነው። ከነኝህና መሰል ፈተናወች ጋር ፊት ለፊት የገጠመው ወያኔ ውጥረቱን ማስተንፈሻ ፣ ማዘናጊያ እና ማደናገሪያ ስልት መቀየስ አስፈልጎታል – የሹማምንቱ አፈርሰታ የተጠራው ለዚህ ነው።
እንደ ቆየው ወግ እና ልማድ ከሆነ አፈርሳታ የሚጠራው በህግ አክባሪዎች መንደር ድንገት አንዳች ወንጀል ተፈፅሞ ግን ወንጀል ፈፃሚውን ነጥሎ መያዝ ሲቸግር መንግስት ለነዋሪው የሚያቀርበው ተማፅኖ ነው… ‘ተሰብሰቡና ምከሩ ፣ ወንጀለኛው ከመካከላችሁ ስለሆነ አውጥታችሁ ስጡን’ ሲል መንግስት ህዝቡን ይሰበስባል። ብዙሀኑ ህግ አክባሪ ፣ በህግ ጥላ ስር እየኖረ ባለበት አገር አንድ ወይንም ጥቂቶች በስውር ህግ መጣሳቸው ሲታወቅ እነኛን የተደበቁ ህገወጥ ግለሰቦች ህብረተሰቡ ከመካከሉ ነቅሶ ያወጣል።
ጥናት የተባለው ሪፖርት ሆነ ተሳታፊው የተፈፀሙ ሀጢያቶችን እንጂ ሀጥአኑን አልነገሩንም።
በወያኔ አገዛዝ ዘመን ባልስላጣናት ድንገት የፈፀሙት ወንጀል ፣ ሙስና ወይንም ኪራይ ሰብሳቢነት የለም። ዘረፋው አስተዳደር በደሉ ፣ ግፉ እና እስሩ በተቀነባበረ ስልት በተደራጁ ዘረኞች አዝማችነት ሲፈፀም የኖረ ዛሬም ተባብሶ የቀጠለ ጉዳይ ነው። ከወያኔ ሹማምንት ጨዋ ቢኖር እሱ ማነው የሚለውን ለመንቀስ አፈርሳታ ያስፈልግ እንደሁ እንጂ ሌብነትማ ፣ ህገወጥነትማ የስርዓቱ መገለጫ አይደለምን? ማነው ሌባ ከሚሉን ይልቅ ማን ነው ጨዋ የሚል አፈርሳታ ቢጠሩ ትርጉም ያለው ተግባር መፈፀም ይቻላል። ከመካከላቸው አንድ ጨዋ ፈልጎ ለማግኘት ከተቻለ እኛም ትብብር የማድረግ ግዴታ ይኖርብናል።
‘ሰርቃለሁ ምን ታመጣላችሁ ፣ ሰርቋል ምን ይጠበስ ትላላችሁ…’ ሲባል ሀያ ሶስት ዓመታት የዘለቀ ዘረኛ ስርዓት ዛሬ ድንገት ብንን ብሎ ሌቦችን እንመንጥር የሚል አፈርሳታ ቢጠራ አስቂኝ ተውኔት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም። ገና በወያኔ መጀመሪያ ያገዛዝ ዘመን የኦዲተር ፅ/ቤት በየክልሉ እየደረሰ ያለውን የአገር ሀብት ብክነት እና ዘረፋ አስመልክቶ ስጋቱን ለወያኔው ፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርብ የያኔው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‘ክልሎች ሲሻቸው በጀታቸውን ማቃጠል ይችላሉ’ የሚል ተራ/ተርታ ምላሽ መስጠቱን ህዝብ የዘነጋ አይመስለኝም። ወያኔ ስለ ሙስና ለመተቸት የሞራል ብቃት የለውም።
አፈርሳታ የተቀመጡት የወያኔ ቱባ ሹማምንት በሙስና ነቀርሳ ሳቢያ ስለደረሱ ለጆሮ የሚቀፉ ጉዳዮች ቢያወሱም እንደዚህ አይነቱ ዝቅጠት ፣ የስርዓት መሻገት ከምን ይመጣል – የፖለቲካ ስልጣኑ መሰረት ምን ድርሻ አበርክቷል በሚለው ላይ አንዳችም ነጥብ ሲጠቅሱ አልሰማንም። ዘር በዘር ኔት ወርክ የተጣላለፈው እና በፖለቲካ ድርጅት ስም የተዋቀረው የማፊያ ሀይል ለበደሉ መከሰት ዋነኛ ምክንያት እሱ ራሱ መሆኑ ከማን ይሰወራል? መፍትሔው ደግሞ ፍትሀዊ ስርዓት እንዲመጣ ማስቻል ብቻ ነው – የታህሳሱ የነ መንግስቱ ነዋይ መፍንቅለ መንግስት ያስከተለው ደም መፍሰስ ሆነ ስድሳዎቹ የአፄ ሀይለስላሴ ሹማምንት ጅምላዊ እልቂት ትምህርት ሊሆነን ይገባል። የነቀዘ ስርዓት በውዴታ እና በወግ ቦታውን ካልለቀቀ ህዝባዊ አመፅ ጠራርጎ ወደ ታሪክ ትቢያ መጣያ ያጉረዋል። ይህ ሲሆን በኛ እድሜ አይተናል።
በዋለታ ዩቱብ ዘገባ እንዳስተዋልነው ከሆነ ጥናታዊ ሪፖርቱን ለማዳመጥ አፈርሳታ የተቀመጡት በሙስና ታሪካቸው እስከ አነገታቸው ድረስ የተዘፈቁት The usual suspects ናቸው። ሪፖርት አቅራቢም ፣ ገምጋሚም ህዝብ ለዘመናት ሲጠቃቀስባቸው የቆዩ ፣ ተፈጸሙ የተባሉ ጉዳዮችም ፀሀይ የሞቃቸው ያገጠጡ የዘረፋ ድርጊቶች ናቸው። በደል እየተፈፀመበት ካለው ህዝብ የተደበቀ ሙሰኛ ሆነ ሙስና የለም።
አፈርሳታው እንዳመለከተው የዘረፋ እና አስተዳደር በደል ወይንም ኢፍተሀዊነት በናሙና መልክ እየተጠቀሰ ሰነድ እንዲይዝ ከመደረጉ ሌላ አንድ ሰው ወይንም ተቋም እንኳ ደፍረው በስም ሊጠቅሱ አልቻሉም። ምክንያቱም የሌቦች አፈርሳታ ሌባን አያጋልጥም። ባጭሩ አፍርሳታው ላይ የታየው የሌቦች ፍሬከርስኪ ጉንጭ የማልፋት ተውኔት የሌባ አይነ ደረቅ… አይነት ነበር ማለት ይቻላል።
ይህ ሌቦች ብቻ ተጠራርተው አፈርሳታ ቢቀመጡ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው ማለት ይችላል። የትኛው ሌባ የትኛውን ያጋልጣል? መሆኑን ሌብነት በተውኔታዊ አፈርሳታ ይወገዳል ብሎ የሚገምት ጤነኛ ዜጋ ይኖራል?
ምናልባትም ተውኔቱ የተቀነባበረው ለ IMF እና World Bank ሊሆን ይችላል። ‘በሰጣችሁን recommendation መሰረት እነሆ ምግባረ ብልሹነትን ለማስወገድ ስብሰባ ጠርተናል’ ብሎ ፈረንጆቹን ለመሸወድ።
ህግ አክባሪ ሹሞች ፣ በህግ የበላይነት ጥላ ስር አገር የሚመሩ ባለስልጣኖች ከህግ አግባብ ያፈነገጠን ሹም ነቅሰው ለማውጣት መቸገር ፣ አፈርሳታ መቀመጥም አያስፈልጋቸውም። የህግ በላይነት ሰፍኖ ባለበት አገር እና ስርዓት ህጉ እንጂ ሰው አይጠይቅህም። ለዚያ ደግሞ በተቋም ደረጃ በበጀት ተደራጅቶ የስራ ሀላፊነቱን መወጣት የሚገባው ክፍል አለ። ያኔ ጉዳዩ የግለሰብ ሳይሆን የህግ ጥያቄ ይሆናል። ህግ የበላይ በሆነበት ፣ በሚከበርበት ስርዓት ውስጥ አፈንግጦ ህግ አላከብር ያለ ቡድን ወይንም ግለሰብ ባህር ውስጥ እንደ ሞተ አሳ ከላይ ሲንሳፈፍ ይገኛል። ህጉ ራሱ አጋልጦ ፣ ነጥሎ ቁልጭ አድርጎ ያጋልጠዋል ፣ ራቁቱን ያቆመዋል። የህግ የበላይነት በሌለበት ፣ ሌቦች በነገሱበት አገር ግን የሹሞች አፈርሳታ ሲጠራ ፣ መፈክር ሲዥጎደጎድ ፣ በዘመቻ እዚህ እና እዚያ ጥቂት ጅቦችን ለታይታ ሲያስር ከማየት የዘለለ ነገር አይኖርም። በሙስና የተዘፈቀ ስርዓት የበሽታውን ምልክቶች እንጂ በሽታውን ከስሩ ነቅሎ ማጥፋት አይችልም።
የህግ ዋስትና ከሰፈነ ህግ እንጂ ግለሰብ አይዳኝህም። የህግ በላይነት ሲጠፋ ዜጎች የሚያድሩት በባለስልጣን በጎ ፈቃድ ብቻ ይሆናል። በቀጭን ትዕዛዝ እሰረው ፣ ግረፈው ፣ ፍታው ፣ ሹመው ፣ ሻረው ፣ ገሽልጠው ፣ አፈናቅለው… እየተባለ ስንት ዘመን በተቆጠረበት አገር… ራስ ምታት ሲይዛቸው በቱጃሮች ልገሳ ደቡብ አፍሪቃ በልዩ አውሮፕላን የተመላለሱ ‘ታጋይ’ ሹማምንት ዛሬ እነሱ ሌባ አጋላጭ ፣ ኪራይ ሰብሳቢ ጠቋሚ ሊሆኑ ነው ቢባል ማን ይቀበለዋል?
ሌባ የሚሰርቀው ሌብነት በህግም ፣ በባህልም ፣ በሞራልም ድጋፍ እንደሌለው ጠፍቶት አይደለም። ገራገሩ ጠ/ሚኒስትር ነገሩ አዲስ እንደሆነባቸው ሁሉ ስለ ደላላ እና ዘረፋ ጉዳይ እንደተገረሙ ገልፀዋል። ይልቅ የሚገርመው እሳቸው ስልጣን ከያዙ ጀምሮ አገሪቱ አላንዳች እንከን ወደፊት እየገሰገሰች መሆኑን ሲወተውቱ መቆየታቸው ይመስለኛል። ስለሚመሩት ስርዓት በቂ እውቀት እና መረጃ ከሌላቸው ደግሞ እሳቸው አሻንጉሊት እንጂ መሪ አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥ ይሆናል። በራሳቸው ላይ ለሰጡት ምስክርነት ሊመሰገኑ ይገባል ማለት ቢቻልም እየደረሰ ላለው ግፍ ግን ከተጠያቂነት አያመልጡም።
የወያኔው ዋልታ ስለ አፈርስታው ሰዓታት የፈጀ ቪዲዮ ቢለቅም አንድ ሰው እንኳ እገሌ ይህን አድርጓል የሚል ጭብጥ ያዘለ ጉዳይ አልነገረንም። አፈርሰታ የሌባውን ስም ከናባቱ እንዲነግር ግድ ይላል። የወያኔው አፈርሳታ ግን ‘የሌቦች ዘመቻ በሌቦች አዝማችነት ሊጀመር ስለሆነ ሌቦች ሁሉ ጥግ ጥግ ያዙ’ የሚል የማስጠንቀቂያ ደወል አስተጋብቷል። መቀመጫችንን ለመሸፋፈን እንዘጋጅ የሚል በኮድ የተጠናቀረ መልዕክት ይመስላል። ለ አይኤምኤፍ እና አለም ባንክ ፍጆታ የተዘጋጀ ተውኔት!!
የትኛው ሌባ ደፍሮ ባለ ፎቅ ፣ ባለ ታላላቅ የንግድ ተቋም ባለቤት ያደረገውን ስርዓት ያፈርሳል? ኪራይ ሰብሳቢነትን የህግ በላይነት እንጂ የሌባ ሹማምንት አፈርሳታ አይገታውም።
መሆኑን ማነው ሌባው? ስም የለውም? አድራሻ የለውም? ህዝብስ አያውቀውም?!
በቤት ካርታ ቁማር የሚጫወቱት የወያኔ ጀነራሎችስ? ስም የላቸውም?
የወያኔ አፈርሳታ ይህን ሰነድ አደባባይ ማውጣትስ እንዴት ይቻለዋል?
የመሬት ዘረፋው በሹማምንቱ ውድድር እንደ ፋሺን አደባባይ በወጣበት አገር ፣ ባንድ ጀምበር ሚሊየነር መሆኑ ፣ የተከራዩትን የቀበሌ (የህዝብ) ቤት መቸብቸቡ ፀሀይ የሞቀው ስግብግበነት እና ፀረ አገር ዘመቻ መሆኑን ህዝብ ጠንቅቆ በተገነዘበበት እና በመሰከረበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሌባውን ለማፈላለግ አፈርሳታ መጥራት ተደናብሮ ለማደናበር መከጀል ነው።
የባለስልጣናቱ ስብሰባ ስማርት ሌቦች በቀጣዩ ዘመን ዘረፋቸውን ለማቀላጠፍ የመከሩበት ስልታዊ ዝግጅት ነው ቢባል ነገሩን ይበልጥ እውነት ያደርገዋል። ግርግር ፈጥሮ ሌላ ዙር የዘረፋ ዘመቻ ለመክፈት የሚደረግ ስልት ቅየሳም ነው። ‘ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ እንዝመት’ እያሉ ለገላጋይ አስቸጋሪ የሚመስል ተውኔት መስራት ትርጉሙ ይኸው ነው።
የህግ በላይነት በማያሻማ ረገድ በሌለበት አገር እንኳን ሙስና እና የስልጣን ብልግና ሌላ ሌላም ጉድ ይታያል። ወያኔ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ከላይ እስከ ታች በዘር መለኪያ የተኮለኮሉ ስግብግብ ሹማምንት የሚመሩት ያገጠጠ እና በኔት ወርክ የተንሰራፋው ዘረፋ ይቀጥላል።
እኔ በበኩሌ የኢትዮሚዲያን የድሮ መፈክር አንግቤ ቆሜያለሁ TPLF cannot be reformed; like apartheid, it should be dismantled” “ህወሓት በጥገናዊ ለውጥ ሊቃና አይችልም። እንደ አፓርታይድ ከሥሩ ነቅሎ መጣል እንጂ” እያልኩ።
የዚህ ፅሁፍ የመጀመሪያ ረቂቅ ‘ህወሀት እንደ ነቀርሳ…’ በሚል ቀርቦ የነበረው ‘እንደ አፓርታይድ…’ በሚል ተተክቷል። እርማት እንዲደረግ ትብብር ላደረገልኝ የኢትዮሚዲያ ኢዲተር ምስጋና አቀርባለሁ።
No comments:
Post a Comment