Friday, November 20, 2015

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ) በጎንደር ወገራ ወረዳ ንዑስ ወረዳ ገደብዬ በረሃቡ ለተጎዱ ህፃናት ከለጋሾች የተሰጠው አልሚ ምግብ በአግባቡ እየተከፋፈለ እንዳልሆነ በዛሬው ዕለት ከቦታው የደረሰን መረጃ አጋልጧል፡፡ ====================================================


ከለጋሾች የተቸረው የህፃናት አልሚ ምግብ ከቦታው መድረሱን ያረጋገጡት የሰባት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጎስቋላ ገበሬ እናቶች ልጆቻቸውን አንዱን በጀርባቸው አዝለው ሌላኛውን በደረታቸው ታቅፈው በዛሬው ዕለት ከየቀዬዎቻቸው ወደ ገደብዬ ከተማ ሲጎርፉ የዋሉ ሲሆን በጣት ከሚቆጠሩት እጅግ በጣም ጥቂት እድለኞች በስተቀር ሁሉም ለማለት በሚቻል ሁኔታ አልሚ ምግቡ ሳይሰጣቸው ከረሃብና ከችጋራቸው በላይ መንገድ ብቻ ተመትተው ተመልሰዋል፡፡
አልሚ ምግቡን እንዲያከፋፍሉ የተመደቡት የህወሓት-ብአዴን ካድሬዎች በዓይኖቻቸው ብቻ በመመልከት "ህፃናቱ ስላልተራቡ አልሚ ምግቡ በፍፁም አያስፈልጋቸውም" እያሉ ወላጆችን በቁጣ ጭምር በመገሰፅ ባዶ እጃቸውን እንደመለሷቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን አልሚ ምግቡን ለመቀበል በመጡ እናቶች ጀርባ ላይ ተጨባብጠው ይታዩ የነበሩት ህፃናት በሙሉ በረሃብ ጠውልገው አካላቸው የከሳና ዓይኖቻቸው የጎደጎዱ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከባለፀጋዎች በምፅዋት የሚገኙትን አልሚ ምግቦች በተለይም ደግሞ "ፕላምፕኔት" ሸጦ ገንዘቡን ለግል ጥቅም ማዋል በወረዳው የህወሓት-ኢህአዴግ ካድሬዎች ዘንድ የተለመደ እጅግ በጣም አሳፋሪ ተግባር እንደሆነ እና አሁንም ተከማችቶ የሚገኘው አልሚ ምግብ ለተራቡ ህፃናት የተነፈገበት ዋና ምክንያት ሸጦ የግል ኪስን ከማድለብ በማለም እንደማይዘል ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የህወሓት-ብአዴን ካድሬዎች ለተለያዩ የፖለቲካ ተልዕኮዎች ወደ ገጠር ሲላኩ ለድሆች በምፅዋት የተገኘውን "ፕላምፕኔት" ስንቅ ቋጥረው አዘውትረው ሲመገቡት መመልከታቸውን በድርቁ የተጎዱ ገበሬዎች መስክረዋል፡፡
በወገራና በዳባት ወረዳዎች 9 ቀበሌዎች ለከፋ ድርቅና ረሃብ መጋለጣቸውን በቅርቡ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

No comments:

Post a Comment