Friday, November 27, 2015

ወያኔ ሰራሽ የርስበርስ ግጭት ደግሶችን እናምክን!!! ==============================


Nov 27, 2015 Editorial

የወያኔ ስርዓት ኢትዮጵያ የተዋቀረችው በህዝብ ታሪካዊ አብሮነትና ተዛምዶ ላይ ሳይሆን የብሔር ብሔረሰብ ልዩነቶችን በማጥበቅና ልዩነትንም የርስበርስ ጥርጣሬና ግጭት ምንጭ እንዲሆን በማለም ነው። ልዩነት የግጭትና የጠብ ምንጭ እንዲሆን ተደርጎ ነው የተዋቀረውና ብፖለቲካ ደረጃ የተገፋው። አንዱ ብሔረሰብ ሌላው ብሔረሰብ ክልል ውስጥ ሲሆን ባዕድነት እንዲሰማውና እንዲሰጋ አንዱ አንዱን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ተደርጎ ነው ሀያ አራት አመት ሙሉ የተገፋውና እየተገፋ ያለው።
ይህም ሆኖ በዘመነ ወያኔ በየቦታው የተከሰቱ የብሔር ሌብሔርሰብ ግጭቶች በሙሉ የተቀሰቀሱት በራሱ በመንግስት ባለስልጣኖች እንጂ መቼም ህዝብ ለሕዝብ ሆኖ አያውቅም። በተለያዩ የደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች አማሮችን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ለማባረር የተወሰዱት ርምጃዎች ራሳቸው ሰለባዎቹ እንደሚናገሩት ለስቃይ የዳረጋቸው ነዋሪው ሕዝብ ሳይሆን ባለስልጣናቱ መሆናቸውን በግልጽ ሲናገሩ ሰምተናል።
በቤኒሻጉልና ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሰሞኑን ይፋ መሆኑ የተነገረው በአስቃቂ ሁኔታ ተገድለው ተቀብረው የተገኙ አማሮች አስከሬን መገኘቱ ታውቋል። ይህም ወያኔ ባስለጠናቸውና ባዘዛቸው ካድሬዎችና ባለስልጣኖች የተከወነ እንጂ በሕዝብ ተነሳሽነት የተፈጸመ አለመሆኑ የታወቀ ነው። ቀደም ሲል በመንግስት ደረጃ የተቀነባበረ አማሮችን የማፈናቀል ዘመቻ ተከታይ ስራ መሆኑን ለማወቅ ብዙ አዳጋች አይደለም። በወገኖቻችን ላይ በሚዘገንን መንገድ የተፈጸመው ግፍ ዘልቆ ይሰማናል:: ሊሰማንም የገባል። ቁጭታችንና ሀዘናችን ግን ወያኔ ወደሚፈልገው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ምክንያት እንዳይሆን ከፍተኛ ትዕግስትና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።
ሰሞኑን በታሪክ ሊዘገብ ከሚችል ልዩነት ውጭ ባኗኗር በባህልና ቋንቋ የማይለያዩትን የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች ቅማንትና አማራ በሚል ለማጋጨት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ ሰይጣናዊ አካሔድ በወያኔ የፖለቲካ ተንኮል እየተመራ እንዳለ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉም ካላንዳች መድሎና ልዩነት ሀገሪቱ ላይ መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ሁሉም በየበኩላቸው የሚያደርጉትን ጥረትና ትግል እንደግፋለን። በህዝባችን መካከል ያሉት ግንኙነቶች ሊሆን የሚችለው እንዱ አንዱን የማገዝ እንጂ ርስበርስ የመጋጨትም ሆነ የመናቆር አይደለም።
ኢትዮጵያውያን ብሄርና ዘር ሳንለይ ይህንን የወያኔ ተንኮል ችግሩ ወደባሰ ደረጃ ሳይሄድ መቋቋምና ማክሸፍ ይጠበቅብናል። ይህ ታሪክነታችንና ታላቅ ሕዝብነታችንን የማይመጥን አሳፋሪ የወያኔ ፖለቲካ እንደሀገር እንዳያጠፋን ሁላችንም በንቃትና በቁርጠኝነት መቋቋም ይኖርብናል።
አርበኞች ግንቦት ፯ ልዩነት ጌጥ እንጂ የጠብና የግጭት ምክንያት የማይሆንባት ሀገር ፥ የየብሔረሰቡ መብት ሁሉ የይስሙላ ሳይሆን በተግባር የተረጋገጠባት ሀገር ፥ ከነልዩነታችን በጋራ ራዕይ የምንተሳሰርባትና የምንገነባት ሀገር እንድትኖረን የሚያደርገውን ትግል ይቀጥላል። የቻልክ በአካል ተቀላቀለን። ያልቻልክ በያለህበት የወያኔ ዘራፊዎች ያሰቡትን የተንኮል ጉንጉን በመበጣጠስ ተሳተፍ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

No comments:

Post a Comment