ሸንቁጥ አየለ
-መንግስት በምግብ እራሳችንን ችለናል እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች: አለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አፋችሁን ያዙ : ከፈለጋችሁም ጨርቃችሁን ጠቅልላችሁ ዉጡ እያለ በየመድረኩ ዘለፋና ስድብ ከጀመረ አመታት አለፉ::
-በሴፍቲኔት እና በልዩ ልዩ የእርዳታ መልክ ባላቸዉ ፕሮግራሞች በየአመቱ ከ17 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዉያን በእርዳታ ጥገኝነት በየአመቱ እንደኖሩ መንግስት እያወቀ አጉል እብሪት ዉስጥ ገብቶ ለጋሾቹን ሁሉ ያንጓጥጥ ገባ::
-ብዙ ሚሊዮን ብሮች እየባከኑ በየአመቱ በርካታ መንግስታዊ: መንግስታዊ ያልሆኑን እና አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሳተፉበት አመታዊ የምግብ ዋስትና ጥናት እየተካሄደ የሚራበዉ ህዝብ 6 ሚሊዮን ነዉ ወይም ሰባት ሚሊዮን ይሆናል እያለ ጥናታዊ ሰነድ ሲቀርብላቸዉ የመንግስት ባለስልጣናት ግን ባለሞያዎችን እያንጓጠጡ እና እየተሳደቡ ጥናቱን ዉድቅ በማድረግ የጥናቱ ዉጤት ከሚያሳዬዉ በግማሽ እና በሶስት እጅ እየቀነሱ የተራበዉ ህዝብ 4 ሚሊዮን ነዉ አንዳንዴም ሁለት ሚሊዮን ነዉ ሲሉ እረዥም አመታት አሳለፉ::
-አለም አቀፍ የእርዳታ ህግ እንደሚያዘዉ የምግ ዋስትና ሲደረግ ሊረዳ የሚገባዉ ሰዉ መቆጠር ያለበት እንደግለሰብ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ መንግስት ግን አስርም : አምስትም የቤተሰብ አባላት ያለዉን አንድ ቤተሰብ እንደ አንድ ሰዉ ይቆጥራና ለአስር የቤተሰብ አባላት እርዳታ ማድረግ ሲኖርበት የአንድ ሰዉ እርዳታ ይመድባል:: ይሄን አሰራር በመቃወም የምግብ ዋስታና ባለሞያዎች በየመድረኩ ይጮሃሉ:: ባለስልጣናቱን ለማስረዳት ይደክማሉ:: በተለይም አመታዊ ጥናት ሲደረግ በርካታ ደፋር የሆኑ እንዲሁም የብዙ አመታት ልምድ ያላቸዉ የምግብ ዋስትና ባለሞያዎች ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችም: መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችም እንዲሁም ከመንግስት መስሪያ ቤትም ተሰባስበዉ ስለሚገናኙ ጉልበታቸዉን አሰባስበዉ እንደ ባለሞያ ብዙ ለመምከርና ለማስረዳት ይሞክራሉ:: ግን የሚሰማቸዉ የለም:: ብዙ ጌዜ በእርዳታ ጠባቂነትና ፈላጊነት ይተቻሉ::
-ከፌደራል እና ከክልል ባለስልጣናት በየወረዳዉ ላሉ ትንንሽ ባለስልጣናት የሚሰጠዉ መመሪያ ደግሞ ሰዉ እየተሰደደ እየተፈናቀለ እና እየሞተ እንኳን እርሃብተኛ የለም ብላችሁ መልሱ የሚል ነዉ:: በጣም ብዙ ድርጅቶች እርዳታ ይዘዉ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ:: ብዙዎቹም ያመጡትን እርዳታ ተረጅ የለም በሚል መጨረሻ ወደ ሌላ ሀገር ያስተላልፋሉ:: ለዚህ ጥሩ ማስረጃ የሚሆነዉ እኔ የምሰራበት ፕሮግራም ነዉ:: የዛሬ አራት አመት 1.5 ሚሊዮን ህዝብ መርዳት ያስፈልጋል የሚል ጥናት አጥንተን በቂ እህል ከዉጭ በፕሮግራሙ ታዘዘ:: ብኋላ ግን ፕሮግራሙ ሊረዳ የሚችለዉ አምስት መቶ ሽህ ህዝብ ብቻ ነዉ ብሎ መንግስት ስለወሰነ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የታዘዘዉ እህል በዚያዉ ቀረ:: ልብ በሉ ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ህዝብ በአንድ ፕሮግራም ብቻ ሊረዳ ሲችል : በቂ እርዳታ እህልም ከአሜሪካ መንግስት ተገኝቶ ሳለ : እኛም ያጠናነዉ ጥናት ተጨባጭ ሆኖ ሳለ ነዉ መንግስት ተረጅ እያለ ተረጅ የለም በማለት አምስት መቶ ሽህ ህዝብ ብቻ እርዱ ያለዉ:: በየወረዳዉ በርካታ እርዳታ ፈላጊ ህዝብ የእርዳታ ያለህ እያለ ይጮህ እንደነበረ እኛም መንግስትም እናቃለን::
-አንዳንዴ ፈረንጆቹ የሚጠይቁት ጥያቄ ፈገግ ያደርጋል:: “መንግስት ግን እንዲህ የሚያደርገዉ ለምንድን ነዉ ?” ይላሉ:: መልሱን እኔም ሆንኩ በርካታ ኢትዮጵያዊ አያዉቀዉም:: የመንግስትን ልብ በመብላት ተቋዳሽ ነን የሚሉ ወይም እራሱ የመንግስት ልብ ነን የሚሉ ሰዎች እራሳቸዉ ያዉቁትም እንደሆነ አላቅም:: ግን ፖለቲካ ነዉ ይሉታል:: ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ሳይንስ ሳይሆን ስሜት: ሆድ : ጥላቻ መሰረት ላይ የቆመ እይታ: ጠላትን በመደባዊ ትግል ለመደምሰስ ሁሉንም ጠጠር ህዝብ ላይ የመወርወር አመለካከትና የፍርሃትን ጎዳናን መከተል እንደሆነ ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ጎርጁ ገብቶ የተነተነ ሰዉ ያዉቀዋል::
-በተለይ አዳዲስ የዉጭ ሀገር ሀላፊዎች ተሾመዉ ሲመጡ የኢትዮጵያ መንግስት ባህሪ እስኪገባቸዉ ብዙ ጥያቄ ይጠይቃሉ:: የመንግስት ባለስልጣናት ሲፈልጋቸዉ ተረጅ የለም ይላሉ:: አንዳንድ መድረክ ላይ ደግሞ ለርዳታ የሚሆን እህል ስለሌለን የተረጅ ቁጥር ቀንሱ እያሉ ወረዳዎች ላይ ይጮሁባቸዋል:: እንዲያዉም የተረጅ ቁጥር ከፍ
ካደረግን ለእርዳታ የሚሆን እህል ስለማናገኝ ነዉ ተረጅ የምንቀንሰዉ ሲሉ ለአንዳንድ ትልልቅ የአለም አቀፍና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሀላፊዎች ይናገራሉ::እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በርከት ያለ እርዳታ ለመስጠት በቂ ጥናት አድርገዉ ሲመጡ ደግሞ ያመጡትን እህልና ቁሳቁስ እንዲመልሱ መንግስት ያዛል:: ከዚህ የባሰ ምን ዉስብስብ ነገረ አለ?
-ከዛሬ አራት አመት በፊት የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት ሀላፊዎች በተለያዩ ክልልሎች ዉስጥ ባሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ያለዉን ችግር ማሰስ ጀመሩ:: የወረዳ ሀላፊዎች በስብሰባ ላይ ተረጅ የለም ሲሉ ይናገራሉ:: እሻይ ላይ ወይም የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት ሃላፊዎቹን ለብቻቸዉ ሲያገኟቸዉ ግን ህዝቡ እየሞተ ነዉ እርሃብ ሰዉን ጎዳዉ ሲሉ ይናገራሉ:: በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ይሆናሉ::
-እንዴዉም አንድ ቆፍጣ የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት ሀላፊ የኢትዮጵያ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሞያዎችን ይተች ነበር:: እንዲህ ሲል:: “እናንተ ምን ያስፈራችኋል :የምታመጡት ጥናት እዉነታዉን አያረጋግጥም:: መሬት ላይ ያለዉ ችግር ብዙ ነዉ:: የእናንተ ጥናት ግን የሚናገረዉ ሌላ ነዉ:: ” ሰዉዬዉ በሙሉ የሀገሪቱን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ሲተች ደፋር ነበር:: አንዳንድ ባለሞያዎች ታዲያ የችግሩን ምንጭ ሊያስይስረዱት ቢሞክሩም አይሰማቸዉም ነበር::
-በተግባር እመሬት ላይ ወርዶ ችግሩን ካዬዉ ብኋላ ግን የኢትዮጵያ መንግስት እንዴት ዉስብስብ ባህሪ እንዳለዉ ገባዉ መሰለኝ ዝም አለ:: ነገሩ እንዲህ ነዉ:: ሰቆጣ ወረዳ አማራ ክልል ላይ ሰዎች እየሞቱና በብዛት ወደ ልዩ ልዩ ቦታም እየተሰደዱ ባለበት ወቅት ይሄዉ ቆፍጣና ሰዉ ወደ ወረዳዉ ጉብኝት አደረገ:: መሬት ላይ ያለዉን የወረዳዉን ችግር በደንብ መዝግቦ ለስብሰባ ከወረዳ ባለስልጣናት ጋር ቁጭ አለ:: ሆኖም ከወረዳ ባለስልጣናት ጋር ሲቀመጥ ሽምጥጥ አድርገዉ ካዱት:: “አንድም ችግረኛ የለም : የተራበም የለም : የተሰደደም የለም” ሲሉ ካድ አደረጉት:: ቆፍጣናዉ ሰዉዬ ተናደደ:: መረጃዎቹን አቀረበ:: እናም የወረዳዉ ባለስልጣናት እንዲህ አሉ:: “በርግጥ ጥቂት ወደት ትግራይና ወደ ጎዳም እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ የተሰደዱ ጥቂት የወረዳዉ ሰዎች አሉ:: ከዚያ ዉጭ ግን በወረዳችን የተራበ የለም::” ይሄ ቆፍጣና ሰዉ ጥሏቸውዉ ብድግ ብሎ እቃዉን ሰብስቦ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ:: በተመሳሳይ ወደ ወላይታ ሶዶም ደቡብ ክልል ሄዶ ተመሳሳይ ገጠመኝ ገጠመዉ:: ብዙ ወረዳዎች ዉስጥ በተመላለሰና እዉነታዉን እና የወረዳ ባለስልጣናት : የክክልል ባለስልጣናት እንዲሁም የፌደራል ባለስልጣናት የሚናገሩትን እያነጻጸረ ካስተዋለ ብኋላ ነገሩ ሲገባዉ ዝም አለ:: እዉነቱን ነዉ:: ምን ያድርግ? እርሱ ኢትዮጵያ ያለዉ መንግስት እርዳታ ሲፈልግ ለማገዝ እንጅ አስገድዶ ለመርዳት አይደለም:: ከዚያ ጊዜ ብኋላ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ላይ መበሳጨቱን አቆመ::
-እንዴዉም የወረዳ ባለስልጣናት ከላይ ከፌደራል መንግስት እና ከክልል ባለስልጣናት በሚደርስባቸዉ ጫና ግራ እስከመጋባት እና የሚናገሩትን እስካለማወቅ ይደርሳሉ:: አንዳንዴ እነዚህን ትንንሽ ባለስልጣናት መተቸት ነዉር ሆኖ የሚሰማኝ ጊዜ አለ:: ግን እዳዉና መከራዉ ሁል ጊዜም የሚያርፈዉ እነሱ ላይ ነዉ::በተለይ የደቡብ እና የአማራ ክልል ወረዳ ባለስልጣናት ከህሊናቸዉ ጋር ሁሌ እንደተሟገቱ ነዉ:: ያለፉት ሁለትና ሶስት አመታታን ደቡብ ክልል በየወረዳዉ ስንት ችግረኛ እያለ አንድም ተረጅ የለኝም ወደማለት ሄዶ ነበር:: አማራ ክልል 100 የሚረዱ ሰዎችን አስቀምጦ አንድ ተረጅ ብቻ ነዉ ያለኝ ወደ ማለት ተራምዶ ነበር::
-አንዳንዴም የወረዳና የክክልል ባለስልጣናትን አንዳንድ ደፋር የምግብ ዋስትና ባለሞያ አንቆ ሲይዛቸዉ ሰዉ እስካልሞተ ድረስ እርዳታ አንፈልግም: ቢራብም ያለዉን ከብት ሸጦ ይብላ ሲሉ ይቆጣሉ:: በተወሰነ ደረጃ የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ጥቂት ምክናያታዊ ለመሆን ይሞክራሉ:: የኦሮምያ ባለስልጣናት እኔ እንዳዬሁት ደፍረዉ ለመወሰን ቢፈሩም ቢያንስ እንዲህ ይሁን ብሎ ደፍሮ የሚወስንላቸዉና ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚጮህ ባለሞያ ሲያገኙ ከመሳደብ ይቆጠባሉ:: የአማራ ክልል ባለስልጣናት ባለሞያዎችን ማንጓጠጥ ይቀናቸዋል:: በተለይም መንግስታዊ ያልሆኑና አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያቀርቡትን ሀሳብ ለማጣጣል ወሳኝ ናቸዉ:: ህዝባቸዉ እያለቀ ጠላት የሞተ ሳይመስላቸዉ አይቀርም:: ሌሎቹ ክልሎችም እንዲሁ የተለያዬ ባህሪ አላቸዉ:: አጠቃላይ የኢትዮጵያ ክልልሎች ባለስልጣናት የጋራ መገለጫ ግን ሁል ጊዜ ዉሳኔን በፖለቲካ መነጽር መቃኘት እና እዉሳኔአቸዉ ላይ ሀስት እና ማስመሰል መጨመራቸዉ ነዉ:: ለባለሞያ ንቀት እሁሉም ክልልሎች ጋ አለ:: ፌደራል ላይ ባለሞያን በለበጣ እና በሾርኔ የማዬት ካንሰር የሆነ እይታ አለ:: የምግብ ዋስትና ባለሞያዎች ፈጽሞ የሞያ ነጻነት የላቸዉም::
-ከሁሉም የሚያሳዝነዉ ነገር አንዳንድ ባለሞያዎች አሉ መንግስት የሚወስነዉ ዉሳኔ ሀሰትና ዉሸት እንደሆነ ሲያዉቁ ሁል ጊዜ በምግብ ዋስትና ላይ እዉነት የሚናገሩ ባለሞያዎችን እየሰለሉና እያጣጣሉ ለመንግስት ባለስልጣናት
የሚያቀርቡት አካሄድ ነዉ:: በተለይ በአመታዊ የምግብ ዋስትና ጥናት ወቅት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚመጡ ቁርጠኛ ባለሞያዎች ይሄን ተናገሩ ; ይሄን አሉ : መንግስት በምግብ ዋስትና እና በእርዳታ ላይ ያለዉን ፖሊሲ ተቹ እየተባሉ የሚደርስባቸዉ ስለላ : ጉንተላ: ማሽሟጠጥና ስድብ ለጉድ ነዉ::
-የምግብ ዋስትና ባለሞያዎች ደጋግመዉ ደጋግምዉ ያስረዳሉ:: የሚሰማ የለም:: አንድ አመት የሚከስት የምግብ ዋስትና ጉዳት በተለይም የአንድ ቤተሰብ እሴት መሟጠጥ ለሃያ አምስት አመታታ አያገግምም ሲሉ መረጃ አጣቅሰዉ ተያያዥ ጥናቶችን ድርድረዉ ያስረዳሉ:: ስለዚህ ማህበረሰቡ እሴቱን እና ጥሪቱን ከመብላቱ በፊት ድጋፍ እና እርዳታ ያስፈልገዋል ይላሉ:: ማህበረሰቡ እሴቱን እና ጥሪቱን (ከብቱን : የቤት እቃዉን እና ሌሎች ቁሳቁሶቹን ) አንዴ መሸጥና መብላት ከጀመረ የሚደርሰዉ ጉዳት ለሃያ አምስት አመታት አያገግምም:: በተለይም በሚቀጥለዉ አመት ጥቂት የምግብ ዋስትና ችግር ከገጠመው ላንዴና ለመጨራሻ ግዜ ተሰባብሮ ይወድቃል እያሉ ያስረዳሉ:: ምክንያቱም የሚቋቋምበትን ጥሪትና እሴት ሸጦ በልቷልና::
-እናም የሆነዉ ይሄዉ ነዉ::ለባለፉት ብዙ አመታት ማህበረሰቡ ያለዉን እሴትና ጥሪት እየሸጠ ሲበላ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አዲስ አበባ ላይ ቤት ስለገነቡ ; በርካታ ኢንቨስትመንትን እየተሞዳሞዱ በማከናወን ሼር ካምፓኒዎች ዉስጥ እጃቸዉን ስላስገቡ ህዝቡ በሙሉ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፉ ዉስጥ የገባ የመሰላቸዉ ባለስልጣናት ተረጅ የለም እርዳታ አንፈልግም እያሉ ሲያዉጁ ነበር:: ይባስ ብሎም ህዝቡ ያለዉን እየሸጠ ይብላ እንጅ እርዳታ ከንግዲህ ኢትዮጵያ አያስፈልጋትም ሲሉ ነበር:: ምክንያታቸዉም ሀገሪቱ በምግብ እራሷን ችላለች ሲሉ ነበር::
-በተታያያዥም የሚያስከፋዉ ደግሞ በርካታ የምርምር: የግብርና : የምግብ ዋስታና ባለሞያዎች መሬት ላይ ያለዉን ደረቅ እዉነት እያወቁት በስራቸዉ ዉስጥ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ቻለች የሚል ሀረግና ሀሳብ እንዲለጥፉ ሲገደዱ የሚያሳዩት የንዴት ስሜት ብሎም የማዘን ስሜት ልብ ይሰብራል::
-በየአመቱ በሴፍቲ ኔት የሚረዳዉ 17 ሚሊዮን ህዝብ እራሱ የምግብ ዋስትና ተረጅ መሆኑን ባለስልጣናቱ ሆዳቸዉ እያወቀ ቢክዱትም በርካታ ባለሞያዎች ችግርና ድርቅ ሲመጣ ይሄ የሴፍቲ ኔት ተረጅ ዋነኛዉ የምግብ ዋስትና ተጠቂ እንደሚሆን ሲያስረዱ ነበር:: መንግስት ግን ሆን ብሎ ሴፍቲ ኔት በምግብ እራስን የመቻል ማሳያ ነዉ የሚል አይነት ግዴለሽ አይሉት የተንኮል አቋም በመያዝ ነገሩ አሁን እደረሰበት ላይ እንዲደርስ ሆኗል::
-ለብዙ አመታታ በቂ ድጋፍ ሳይደረለት ጥሪቱን እና እሴቱን እየባለ የኖረ ማህበረሰብ ቅስሙ የተሰበረ ማህበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ጥቂት ችግር ሲመጣ ይንገዳገዳል ብቻ ሳይሆን ይሰባበራል:: ህዝቡ እንዲህ በአንዴ ወደ ከፋ የረሃብ አዘቅት ዉስጥ ተወርዉሮ አልገባም:: በሂደት እንጂ:: መንግስት ግን ልክ ርሃቡ ዛሬ እንደተከሰት ተነስቶ ያዉጃል:: ለዚያዉም ፖለቲካዊ አዋጅ::ርሃቡ ትናንትም ነበር:: መንግስት ግን የርሃብ እና የምግብ ዋስትና ችግር መኖርን ሽምጥጥ አድርጎ ክዶ ነበር:: ህዝቡን በመርዳት አጋዥ የሆኑትንም ሀይላት አታስፈልጉም እያለ በመድረክ ላይ እየወረፈ ነበር::
-በዚህ ሂደት ዉስጥ የአለም የምግብ ፕሮግራም እንዲሁም በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ፕሮግራሞች የእርዳታ ፕሮግራማቸዉን ማጠፍ : ወደሌላ ሀገር ማስተላለፍ ሲያከናዉኑ ነበር:: ይሄ እንዲከናወን ደግሞ መንግስት ያዉቅ ነበር::
-አሁን መንግስት በትክክል ለተጎዳዉ ህዝብ መፍተሄ መፈለግ ካለበት እስከዛሬ የሄደባቸዉን አካሄዶች መተዉ አለበት:: በዋናነት እስከዛሬ የሰራቸዉን ስህተቶች ማመንና እዉነታዉን ቁልጭ አድርጎ መቀበል ይገባል:: ከአለም አቀፉን የእርዳታ ሰጭ ሀይል ጀርባ የቆመዉን የአለም አቀፍ ማህበረሰብም ይቅርታ መጠዬቅ ወሳኝ ነዉ:: ምክንያቱም ብዙ ወሳኝ የሆኑ የአለም አቀፍ እርዳታ ዉስጥ የሚሰሩ ሀይሎች የኢትዮጵያ መንግስት ትናንት እየተሳደብ ሲያንጓጥጣቸዉ የነበሩ ወገኖችን ዛሬ እርዱኝ የሚለዉን ጥሪ ሲያቀርብ እንደ ቀልድ ሊወስዱት ይችላሉና:: እንዲሁም ይሄዉ የአለም አቀፉ እርዳታ አድራጊ ሀይል በቂ ዉሳኔ ማሳለፍ የሚችልበትን እድል መስጠት ተገቢ ነዉ:: በወረዳ ደረጃ ያሉ ባለስልጣናት እና የመንግስት ባለሞያዎች ያለመሸማቀቅ የሞያ ግዴታቸዉን እንዲወጡ በክልል እና በፌደራል ደረጃ ያሉ ቱባ ባለስልጣናት ጣልቃ እየገቡ ከመፈትፈት መታቀብ: እንዲሁም እርዳታዉን ከፖለቲካዉ ነጥሎ ማዬት ተገቢ ነዉ::
-አሁንም ቢሆን ሀያ ሚሊዮን ተራበ : አስራ አምስት ሚሊዮን ተራበ የሚለዉን ዉሳኔ የመንግስት ባለስልታናት እጓዳቸዉ ተደብቀዉ መወሰን የለባቸዉም:: ይሄን ጥያቄ ባደባባይ ሲጠየቁ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሚመልሱት መልስ አስቂኝ ነዉ:: እኔ ባንድ ስብሰባ ላይ እንዲህ ስል ጠይቄ ነበር:: “ጥናት ስናጠና የተባበሩት መንግስታ ቢሮዎችም: እኛ መንግስታዊ ያልሆንን ድርጅቶችም እንዲሁም መንግስትም አብረን እናጠናለን:: በጥናቱ መሰረት የሚወሰነዉን የተረጅ ቁጥር ስትወስኑ ግን በመንግስት ባለስልጣናት ቢሮ ለብዙ ወራት መረጃዉን አስቀምጣችሁ ስታበቁ በተቆለፈ ቢሮ ዉስጥ ብቻችሁን ቁጭ ብላችሁ ትወስናላችሁ:: ይሄ ለምን ይሆናል:: ጥናቱ እንዳለቀ ወዲያዉኑ የጥናት ቡድኑ እንደተሰበሰብ የተረጅዉ ቁጥር መወሰን አለበት እንጅ የምን ዙሪያ ጥምጥም ነዉ? እተረጅዉ ቁጥር ላይ እስካልተሳተፍን ድረስ ለምንድ ጥናቱ ላይ መሳተፋችን ምን ትቅም አለዉ?”:: ባለስልጣኑ ነገሩ ገብቶታል :: እናም ሳቅ ብሎ እንዲህ መለሰልኝ:: “የተረጅ ቁጥር የመወሰን ጉዳይ የሀገር ልኡዋላዊነት ጉዳይ ነዉ::” ብሎኝ ቁጭ::
በተለያዬ ሰዓት ይሄን ጥያቄ በርካታ ባለሞያዎች የመንግስት ባለስልጣናትን ፊት ለፊት እያፋጠጡ እንደጠዬቁ ያደባባይ ሚስጥር ነዉ:: ግን የመንግስት አቋም ሁሉም የሚሆነዉ “የተረጅ ቁጥር የመወሰን ጉዳይ የሀገር ልኡዋላዊነት ጉዳይ ነዉ::” የሚል ነዉ::
-እኛም ሆንን መንግስት ግን እዉነታዉን ያዉቀዋል:: የተረጅ ቁጥር የመወሰን ጉዳይ የሀገር ልኡዋላዊነት ጉዳይ ሆኖባችሁ ሳይሆን የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖባችሁ ነዉ:: የተረጅን ቁጥር የመወሰን ጉዳይ ፖለቲካዊ ነዉ ማለት ደግሞ የሚሞተዉን ህዝብ ቁጥር በፖለቲካዊ ዉሳኔ እንደ መወሰን ማለት ነዉ:: ስለሆነም እርዳታዉ ከፖለቲካዊ ዉሳኔ ሳይላቀቅ ምንም ዉጤታማ ስራ መስራት አይቻልም:: እንግዲህ ህዝቡን ለማዳን ከፈለጋችሁ እርዳታዉን ከፖለቲካዊ ዉሳኔ አላቁ : አጋራችሁ የሆነዉንም የአለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ሀይልም ይቅርታ ጠይቁ:: እነዚህን ስህተቶቻችሁን አርማችሁ በእዉነት ስለ እዉነት ህቡን ለማዳን ትችሉ ዘንድ ወደ ስራ መግባት ይጠበቅባችኋል:: እስኪ ፖለቲካዊ መነጽራችሁን ለጥቂት ጊዜ እንኳን ህዝቡን ለማዳን አዉልቃችሁ አስቀምጡት::
ከሰማችሁኝ ብዬ ያወቅሁትን በጥቂቱ አካፈልኳችሁ:: ከኔ የበለጠ እጅግ ብዙ የሚያዉቁ ባለሞያዎች አጠገባችሁ አሉላችሁ:: ሳታሸማቅቁ እህ ብላችሁ አድምጧቸዉ:: ባለሞያዎቹን ካደመጣችሁ ህዝቡን ማዳን ትችላላችሁ:: አለዚያ ግን ያዉ ዉሃ ወቀጣ ነዉ::
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48204#sthash.hcRmrAdW.dpuf
No comments:
Post a Comment