Tuesday, November 24, 2015

ይድረስ ለሆዳችሁ ብቻ ለምታስቡ! (ህሊና ስጦታው)

በህሊና ስጦታው
ይድረስ፥
1. በጥንቃቄ ተመርጣችሁ፣ ለሆዳችሁና ለኪሳችሁ ብቻ የምታስቡ በመሆናችሁ የተለያየ ስልጣን ተሰጥቷችሁ፣ አገርንና ሕዝብን ዘርፋችሁ፣ ፎቅ እንድትሰሩና ሚሊየኔር እንድት ሆኑ ተፈቅዶላችሁ፣ እነዚህ መቶ የማይሞሉ ባለጌዎች ታዛዥ በመሆን አገርንና ወገንን የምትበድሉ የሲቪል ባለስልጣኖች፥
2. በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በሕዝብ ተመረጣችሁ ተብሎ ከየቦታው የተጠራቀማችሁ ሥራችሁም የነርሱ ብልሹ ምግባር ሕጋዊ እንዲሆን በትዕዛዝ እጃችሁን እያወጣችሁ የምታስወስኑ ብልሹ ዜጋዎች፥
3. የአገርና የወገን መመኪያ መከታ ነኝ ብለህ ቃል በመግባት መለዮ አድርገህ፣ መሣሪያ ታጥቀህ፣ በሰራዊት ውስጥ ሆነህ የምታገለግለው፣ እነዚህ የባለጌ ጥርቅምና ሌቦች በልማት ስም አገርህን ለእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሲሻሟት፣ አንተ ኮንዶሚኒየም ስለሚሰራልህ፣ የወርቅ ማዐድኗም በአላሙዲን ስም እየተጫነ በዓለም ዙሪያ ሂሳባቸው እያስገቡ የወደፊት ቤታቸውን ሲሰሩና ፋብሪካዎች እየከፈቱ ሲነግዱ የሚቃወሙትን እየደበደብክና እየገደልክ እንደጀግና ትጎርራለህ። እናንተንም በዘር በመከፋፈል፣ ለግዳጅ ስትላኩ ወደ ተለያየ ጎሳ በመላክ ያንዳችሁን ጎሳ ሌላው በጭካኔ እንዲገለው አንዲደበድበው ያድርጋል። ግን እናንተን ምን ያህል ዝቅ አድርጎ ቢገምቷችሁ ነው ገበሬውን ለዘመናት ከሚያርስበት ቦታ በልማት ስም ተፈናቅሎ ለምን ብሎ ሲጥይቅ በናንት በጀግኖቹ ይደበደባል፣ ይገደላል። አዛዦቻችሁ በጣም የሚያሳዝኑም የሚያሳፍሩም ናቸው። ጌቶቻችሁ በዶላር ለሚያሸሹት ገንዘብ ዘብ ቆመው፣ የሰራዊቱን በጀት መበዝበዝ ስለተፈቀደላቸው እናንተን ጃስ እያሉ ወገንን ያስነክሳሉ። ለመሆኑ ታሪክ ትቶ ማለፍ ምን ያህል እንደሚያኮራና በቢሊዮን ከተዘረፈ ሐብት በላይ መሆኑ ይገባቸዋል? ለአገራቸውና ለወገናቸው በሚሠሩት መልካም ሥራ፣ ወላጆቻቸውም ልጆቻቸውም በወገን ምን ያህል ፍቅር እንደሚያድርባችውና እንደሚያኮራቸው ያውቃሉ? አይመስለኝም!
በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው በዚሁ ባልታደለ የአፊሪካ ምድር እንድነዚ እንደኛዎቹ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ በታሪክ ተፈጥሮ አያውቅም። ነገር ግን 99% የአፍሪካ መሪዎች ሌቦችና አልጠግብ ባዮች ናቸው። ይህንንም የሚያመጣው በመጥፎ ድህነት ውስጥ ማደግ ነው። ግን የሌብነት ዕድሜን ለማራዘም ሲል የትኛውም የአፍሪካ አገር መሪ ፓርቲና ወገነንን በዘር ከፋፍሎ አያውቅም። በየትኛውም መልኩ መከፋፈል ዕድገት አምጥቶ አያውቅም። እርግጥ ሕዝብን አንድ ላይ እንዳይቆምና መብቱን እንዳይጠይቅ ያደርገዋል። የማይፈለገውም እርሱ ነው። መለዮ ለባሹ በአረቡ ዓለም እንደታየው፣ ማለት በግብጽ፣ በሊቢያ በየመን፣ መሪዎቹን በቃ፣ ለሌቦች ዘብ አንቆምም፣ የአገርና የወገን እንጂ የአረመኔዎችና የሌቦች ስብስብ፣ በዘር የሚያስቡ ሆዳሞች አገልጋዮች አይደለንም ብላችሁ የመሣሪችሁን አፈሙዝ ወደ ሌቦቹ መንደር በማዞር ስልጣኑን ለወገናችሁ አስረክቡ።

ለመሆኑ እናንተን ምን ያህል ዝቅ አድርገው ቢያዩአችሁ እንደሁ አይገባኝም። እናንት ግዳጃችሁን አለማወቃችሁ በጣም የሚያሳዝንም የሚያሳፍርም ነው። የቀደምት ነገስቶቻችንንና አባቶቻችንን አያቶቻችንን አንድነት ኃይል መሆኑን በመረዳት፣ የጎሳ ንጉሶችን በማጥፋት ሕዝቡ አንድ በማድረጋቸው በቅኝ ሊገዛን የሠለጠኑ 500,000 የጦር ሰራዊት ከጊዜው ሙሉ ትጥቅ ጋር ያመጣውን የጣልያን መንግስት፣ ባላቸው ውስን መሣሪያዎች እጅ ለእጅ በመያያዝ፣ ኃይላችወ አንድነት ስለነበር፣ ጠላትን እረፍት ነስተው አገራችንን በነጻነት አስረከቡን።
ጉድ እያደር ነው እንዲሉ፣ እነዚህ ደካሞች የትግራይ ተወላጅ ነን ሲሉ የማያፍሩ፣ ደግሞም አልፈው የንጉሱ የአጼ ዮሐንስ ዘሮች ነን ማለታቸው፣ የተከበሩት ንጉስ ለሐገራቸው ዳር ድንበር ሕይወታቸውን የሰውትን ንጉስ አስከሬን ከመቃብሩ አውጥቶ እንደመጣል ይቆጠራል። እነዚህ ሆድ አደሮች አያት ቅድመ አያቶቻችሁ በነጻነት አስከብረው ያቆያችሁትን አገር በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሥር እያደረጓት ነው። ንጉሰ ነገስቶቻችን በአንድነታችን ያጎናጸፉንን ነጻነትና በነጩ ዓለም የተሰጣትን የክብር ስም ማለትም ነጭን ያዋረደ ጥቁር ስም የሚለውን ክብሬን ለኪሳቸውና ለሆዳቸው ለሚለቅሙት ጥቅም በመሸጥ፣ አገርና ክብርን ያዋረደ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን የመጀመሪያዎቹ ናቸው። ድሮም ሆዳም አገርና ወገን አያውቅም ይባላል። እነዚህ አረመኔዎችና ከሃዲዎች ወላጆቻቸውም ሆኑ የትግራይ ሕዝብ፣ ከሌላው ወገኑ ጋር በመሆን ሊያጠፋቸው ይገባል። ወላጆቻቸውም እነዚህን ማፈሪያዎች ሊክዷቸው ይገባል።
ከሁሉም በላይ በጣም የሚያሳዝነው፣ ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ቀንደኛ ሌባና የአገር ወገን ጠላት ሞተ ብለው ለአገርና ለወገን የሠራ በማስመሰል ሕዝብ አዝኖ ያለቀሰ ማስመሰላቸው ነው። ይህ ሲፈጠር እራሱ ድኩም የማኬቬሊን ጽንሰ ሃሳብ የራሱ በማስመሰል በኢትዮጵያ ላይ ሲተገብር፣ ዓላማውን አይቶ እግዜር ዐድሜ ነሳው እንጂ፣ ዐድሜ ልኩን ትቷቸው ከሄደው የሌቦች ስብስብ ጋር አገርንና ወገንን ሲዘርፍ ሊኖር ነበር። ትሻልን ሰድጄ ትብስን አገባሁ ይሏችል ይሄ ነው። ያ ሙት በሬዲዮ ሲለፍፍ እኛን ደግፋች ሁን በድል ከገባን አገሪቷ በዴሞክራሲ ትመራለች፣ የሕግ የበላይነት ይኖራል፣ የተወረሰ ንብረታችሁ ይመለሳል ነበር። ግን እድገቱና ትውልዱ ብልሹ ሰው ምን ቃል አለው! የኢትዮጵያን ሕዝብ የገጠመው የአህዮች እድል ነው። አህዮች የጅቡን ድምጽ ሲሰሙት ወደውት፣ክጅቡን ፍለጋ ዞረው ማግኘት አቃታቸው። ከዚያ ጅብ የሚኖረው እግዚአብሔር ዘንድ መሆኑ ተነገራቸውና ወደ ምድር እንዲላክላቸው ጌታን መማጸን ጀመሩ። የለመኑትን የማይነሳው አምላክ ወደ ምድር ላከላቸውና፣ ድምጹን እየተከተሉ መፈለጉን ተያያዙት። ድካማቸውንም ቆጥሮ አምላክ አገናኛቸውና አህዮቹ ሲጠጉት አንጀታቸውን እየዘረገፈ መብላት ተያያዘው። አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአህዮቹ እድል ነው የገጠመው። የዚያን የሌባ ልፍለፋ ሰምቶ እውነት መስሎት፣ በሕዝቡም በሠራዊቱም፣ በመንግስትም እርዳታ ሰተት ብለው ገብተው እንደጅቡ አንጀት አንጀቱን ዘረገፉት።
አይገርማችሁም፣ እነዚህ አንዳቸው ከአንዳቸው የማይሻሉና፣ ከሆዳቸውና ከኪሳቸው አርቀው የማያስቡ መሆናቸው እንጂ፣ ትክክለኛ አዕምሮ ያላቸው እንደ ጨዋ ሰው የሚያስቡ ቢሆኑ ኖሮ፣ ይህ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ስቃይ በኛና በቤተሰባችን ቢሆን ብለው ባሰቡ ነበር። ግን የዛ የባለጌ ቅን አገልጋዮች ስለሆኑ፣ ሞቶም አገርና ሕዝብ የማጥፋት እቅዱን ለማስፈጸም ቀና ደፋ ይላሉ።
አረ ለመሆኑ እነዚህ ከንቱዎች ከጌታቸው ሞት በኃላም ሞት መኖሩን አልተገነዘቡም እንዴ? ፕሬዘዳንት ማንዴላ እንደናንተ ላለው ደንቆሮ የፖለቲካ ሰዎች ነን ባዮች ንግ ግር ሲያደርጉ፣ “የፖለቲካ ስልጣን ይዛችሁ አመራር ወንበር ላይ የተቀመጣችሁ በሙሉ ለወገናችሁና ለአገራችሁ የምትሠሩትን መልካም ሥራ ሁሉ ለራሳችሁ እንደምሰሩት ቁጠሩት። ወደጎን የምናስቀምጠው ቢሊዮን ዶላር መጨረሻ ላይ ምንም አይፈይድም። ጥለነው እንሄዳለን። በመልካም ሥራችን የምናተርፈው የወገን ፍቅር ግን ስማችንን ከመቃብር በላይ ያውለዋል። ዘር ማንዘራችን የወገንን ክብር ያተርፋል” ነበር ያሉት። እንደርሳቸው የምታስቡ መስሏቸው ዛሬ በዓለም ዙሪያ የፕሬዘዳንት ማንዴላ ስም ትልቅ ክብር አለው። የናንት ግን ወላጆቻች ሁም ሆኑ ልጆቻችሁ ሲያፍሩና ሲዋረዱ ይኖራሉ።
በመሃላችሁ፣ ከሥልጣን አልወርድም የሚል ስብስብ ሌባ ብቻ ነው። ጨዋውማ ለራሱ ጊዜ ስለሚያስፈልገው ለተረኛ አስረክቦ ሕይወቱን መኖር ጀምሯል። ግን የናንት ዓይነቱ ካልተዋረደ እንደጨዋ ክብሩንና ታሪኩን አስከብሮ አይለቅም። በመጨረሿ ልነግራችሁ የምፈልገው የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ኢትዮጵያዊ ነው። እናንተ ግን ከዚያም አልተፈጠራችሁም። ሌላው የንጉሳችን የአጼ ዮሐንስና የጀግናው የአሉላ አባነጋ ዘር ነን አትበሉ። እነዚህ ሰዎች ለአገራቸውና ለወገናቸው ክብር ሲሉ ሞቱ እንጂ እንደናንተ አገር አሳልፈው ሲሰጡ፣ አገርን ዘርፈው የማይበሉትን ብር ሲሰበስቡ፣ የሌብነት እድሜ ለማራዘም ሲከፋፍሉ አልታዩም። እባካችሁ እንደናንተ አይነት ምግባረ ብልሹ ከነዚህ ከተከበሩ ሰዎች ጎን አትሰለፉ።
በነገራችን ላይ ደርግ ለሕዝቡ የአገሩን መሬት በነጻ አደለው፣ እናንተ ግን በልማት ስም መሬት ወርሳችሁ ለባለቤቱ ለሕዝቡ በመሸጥ ገንዘብ ሰብስባችሁ ፎቅ ሠራችሁ። በጣም ያሳፍራልም ያሳዝናልም። ገበሬው ሳይቀር ለዘመናት ሲያርስ ከነበረበት መሬቱ ተነቅሎ ለቅኝ ገዢዎች ተሸጠ። ለዚያውም ዓለምን ባስደነቀ ዋጋ 1 ዶላር በሄክታር። ጉድ ነው! ልዩነቱ በናንተ ስም ውጪ ይከፈላል። እንደሌላው ዓለም ሁሉ ፕሬዘዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና፣ ሚኒስትሮች አሉን፣ ግን ስሙን ተሸከሙት እንጂ ከሮቦት የተሻሉ አይደሉም። ሁሉም የተሰጣቸውን የሚያስቡ፣ የተባሉትን የሚፈጽሙ ተራ አገልጋዮች ናቸው። ሕሊናማ ቢኖራቸው የተሻለ የትምሕርት ደረጃ ያላቸው ነበሩ። እንቢ ለአገሬና ለወገኔ ማለት ነበረባቸው። ነገር ግን ለኪሳቸውና ለሆዳቸው ቅድሚያ ሰጡ። ታሪክ በነርሱና በናንተ ዘንድ ቦታ የለውም።
ወገኖቼ የትግራይን ሕዝብ ከነርሱ አትቀላቅሏቸው። አብረን የምንኖር ኢትዮጵያውያን ናቸው።
እናነት በየጎሳችሁ ላይ የተሾማችሁ ለጊዜያዊ ጥቅም ወገኖቻች ሁን የምትጎዱ፣ ግዳጃችሁን ስትጨርሱ በግምገማ ስም ለእስር የምትዳረጉ፣ ንብረታችሁ በሙስና ተፈቅዶላችሁ ባፈራችሁት ንብረት ላይ ውርስ የሚፈጸምባችሁ፣ ብታስቡ ይሻላችኃል! ለዚህ ዋናው ምሳሌ ቀኑን የሚጠብቀው ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ነው። በባንዳው በመለስ ትዕዛዝ የፈጃቸው የሲዳማ ገበሬዎች ቀን ነው የሚጠብቁት። ከአሁኑ ማሰብ ጀምሩ። ግለሰቦች ያልፋሉ፣ ስልጣንም ያከትማል። ሕዝብና አገር ግን ይኖራሉ። ከአሁኑ ማሰብ ይበጃል።
በዓለም የመጨረሻ ድሃ ከሚባሉትና ከፍተኛ የረሃብረኛ ቁጥር ካላት ኢትዮጵያ፣ ብልሁ የሕዋሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ኢኮኖሚያዋን ያሳደገው በፎቆችና በአስፋልት ሆነ። ከሌላው ዓለም ዕድገት በተለየ መንገድ ታዲያ፣ አሁን ዝናብ ጠፋና ርሃብ ገባ ብሎ ምን ልመና መዞር አስፈለገ? ፎቅና አስፋልቱን ማጉረስ ነው እንጂ! በነገራችን ላይ የናንተ ዕድገት ጠኔ የያዘውና የወደቀን ሰው በማብላት ፋንታ ሱፍ አልብሶ ግድግዳ አስደግፎ እንደማቆም ነው። ይህ ማለት ለተመልካች አይን ብቻ የታሰበ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ እነዚህ መቶ በማይሞሉ ምግባረ ብልሹዎች አገርና ወገን ሲጠፋ ዝም ብላችሁ አትዩ። በሲቪል ሥራም ሆነ በሠራዊት ውስጥ ሆኖ አገርና ወገኑን ለሆዱ ሲል የከዳውን ቤተሰባችሁን በመምከር ከወገንና ከአገር ጋር በመቆም ታሪክ እንዲሰራ ንገሩት። እናንተም ትኮራላችሁ፣ እነርሱም ታሪክ ሲያነሳቸው ይኖራል። እግዚአብሔር በልቦናችሁ አድሮ ለታሪክ ባለቤትነት ያብቃችሁ፣ አሜን!

No comments:

Post a Comment