Saturday, November 7, 2015

የኢትዮጵያ ወጣቶች ክልል፣ ቋንቋም ሆነ ሀይማኖት ሳይገድባቸው በጋራ ይቁሙ! November 5, 2015


ከ1950ዎቹ ጀምሮ የተደረጉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች በሙሉ የተጠነሰሱትና የተመሩት እድሜያቸው ከሠላሳ አምስት ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ነው። የ1997 ምርጫ ታሪካዊ እንዲሆን ያደረጉ፤ የሚያዝያ 30 ቀን 1997ን ታላቅ ሰልፍ ያደራጁ፤ ሕዝብን አደፈፍረው ለምርጫ በማሰለፍ ግንቦት 7 ቀን 1997 ታሪካዊ ዕለት እንድትሆን ያደረጉ፤ በኋላም “ድምፃችንን አናስነጥቅም” በማለት የአግዓዚ ፋሽስቶችን በድንጋይና ዱላ የገጠሙ የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው። በዚህ ትግል ሽብሬ ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን ሰውተዋል፤ በቁጥር የበዙት ደግሞ አካሎቻቸውን አጥተዋል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አሁንም በአገዛዙ እስር ቤቶች ሰቆቃ እየተፈፀመባቸው ነው። ጥቃቱ ቢበዛም ትግሉ ደግሞ የዚያኑ ያህል ተጠናክሮ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ወጣት ጥቃትን አሜን ብሎ አይቀበልም።

ህወሓትና ህወሓት የፈጠራቸው አድርባይ ድርጅቶች የዛሬው ወጣት ወኔው የላሸቀ፤ ኑሮው የተጎሳቆለ፤ የነገ ተስፋውም የጨለመ እንዲሆን ፓሊሲ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው። ህወሓት “መብት ተነፈግን” ብለው ብረት ባነሱ ወጣቶች መቋቋሙን ረስቶ የዛሬ ወጣቶች መብቶቻቸውን ተጠቅመው ሕይወታቸውን መምራት ቀርቶ መብቶቻቸው ምን እንደሆኑ እንዲጠይቁ እንኳን አይፈቅድላቸውም። በህወሓት አገዛዝ የትምህርት ተቋማት የሚሰጡት ትምህርት ጥራት እጅግ የወረደ በመሆኑ ወጣቶች የሕይወትን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ክህሎት ሳይዙ እንዲመረቁ እየተደረገ የተመራቂ ሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል። ለወጣቱ የሥራ እድሎችን የመክፈት ጉዳይ አገዛዙን የሚያስጨንቀው አይደለም። ለም መሬታችን ለባዕዳን በመሸጡ የገጠሩ ወጣት የሚያርሰው ቁራሽ መሬት እያጣ መሰደድ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በሀገር ውስጥ ተስፋ በመታጣቱ በገጠርም በከተማም የሚገኙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ወደ ደቡብ አፍሪቃና አረብ አገራት ለመሄድ በረሃ ማቋረጥ፤ ባህርን በታንኳ መሻገር የጀመሩት በዚሁ የግፍ አገዛዝ ዘመን ነው። ዘመናዊ ትምህርት ያገኘው ወጣትም በተማረው ትምህርት አገሩንና ወገኑን የማገልገል ህልሙ ተጨናግፎ ስደት እጣ ፈንታው የሆነው በዚሁ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ነው። በጫትና ሌሎች ሱሶች አዕምሮው የደነዘዘው ወጣት ቁጥርም አስደንጋጭ ነው።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ወጣቱን በዘር በማደራጀት እርስ በርሱ እንዲጣላ መደረጉ ነው። በየጊዜው በሚፈለፈሉ “የወጣቶች ፎረሞች” አማካይነት የወጣቱ ወኔ ተሰልቦ አድርባይነትን እንዲለማመድ ተደርጓል። የጎንደሩ ወጣት ለአሰላው፣ የመቀሌው ለባህርዳሩ፣ የጅማው ለአዋሳው ባዕድ እንዲሆን፤ በጥርጣሬም እንዲጠባበቅ፤ በሰበብ አስባቡም እንዲቆራቆስ ተደርጓል። ህወሓት ወጣቶችን በወጣቶች ላይ የሚያዘምት እርኩስ ኃይል ነው።
አገዛዙ ይኸ ሁሉ ቢያደርግም ዛሬም የኢትዮጵያ ወጣት፣ የነብር ጣት መሆኑን እያስመሰከረ ነው። አገሩን ከህወሓት ፋሽስቶች ለማዳን ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በመቀላቀል ላይ ያለው የወጣት ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፤ በያለበት ከተማና መንደር ሆኖ በመደራጀት ላይ ያለው ወጣት ቁጥር ደግሞ በጣም አበረታች ነው። ከዚህም በላይ የቴፒ፣ አርባምንጭ፣ ባህርዳርና ጎንደር ወጣቶች እያደረጉት እንዳለው በተደራጀ መንገድ አምባገነኑን ሥርዓት መጋፈጥ ጀምሯል። ጊዜው የአርበኖች ግንቦት 7ቱ አርበኛ አምሳሉ ተሾመን የመሰሉ ለጠላት እጅ ከመስጠት በራስ ላይ እርምጃ መውሰድን የሚመርጡ ቆራጦችን ፈጥሯል።
በእንዲህ ዓይነት ወቅት ክልልን፣ ቋንቋን፣ ዘርንና ሀይማኖትን የተሻገረ የወጣቶች ኅብረት መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በቴፒ ወጣቶች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ሊቆጭና ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል። የአርባምንጭ ወጣቶች ሲሳደዱ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በለቀምት ወጣቶች በደል ሲደርስ በመላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ የደረሰ ጥቃት ነውና ሁሉም ሊያመውና ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። በባህርዳርና ጎንደር ወጣቶች ላይ በደል ሲደርስ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል።
የህወወሓት “ወጣቱን ከፋፍለህ፣ አዳክመህ ግዛ” ፓሊሲ በራሱ በወጣቱ ቁርጠኝነትና የጋራ ስሜት ሊከሽፍ ይገባል። ህወሓትን ወደ መቃብሩ የሚገፋው በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ተወልዶ ያደገ ወጣት መሆኑ የአገዛዙ ኋላቀርነትና የመጪው ጊዜ ብሩህነት ማረጋገጫ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የወደፊቷ ኢትዮጵያ ለወጣቱ ምቹ አገር መሆን አለባት፤ መገንባት የሚኖርባትም በወጣቱ ትውልድ ነው ብሎ ያምናል። በዚህም የኢትዮጵያ ወጣቶች ክልል፣ ዘር፣ ቋንቋም ሆነ ሀይማኖት ሳይገድባቸው ለጋራ መብቶቻቸው በጋራ እንዲቆሙ፤ በአንድ አካባቢ ወጣቶች ለሚደርስ ጥቃት የሌላ አካባቢ ወጣቶች አፀፋዊ ምላሽ እንዲሰጡ ያበረታታል። ኢትዮጵያ በወጣቶቿ ያላሰለሰ ትግል ከወያኔ አምባገናዊ አገዛዝ ነፃ ትወጣለች።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!








No comments:

Post a Comment