Sunday, November 15, 2015

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ) ረሃብና ፖለቲካ ====================================================


አገራችን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ዛሬ በምጣኔ ሀብቷ፣ በፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገቷ ከዓለም አገሮች በጠቅላላ ወደ ኋላ የቀረች ብትሆንም ቅሉ ጀማሪና ልዩ የሚያደርጓት ብዙ ታሪካዊ እሴቶችና የተፈጥሮ ችሮታዎች አሏት፡፡ የሰው ዘር መገኛና ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች መሆኗ ልዩ ከሚያደርጓት ታሪካዊ እሴቶቿ መካከል ጎልተው የሚጠቀሱና ዓለም ሁሉ የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ ቀደምት ህዝቧ ትቶት ያለፈው የኪነ-ህንፃ ረቂቅ ጥበብ እትም አሻራም ስሟን በውዳሴ እያስጠራ ዘመናትን አሻግሯታል፡፡
ኢትዮጵያ የናይል ሸለቆ ስልጣኔን ቀድማ በመጀመርና ለሌሎች በማስፋፋት የምጥቀትን ጮራ ለዓለም የፈነጠቀች የራሷ የቀን አቆጣጠር ያላት ብቸኛዋ አገር ናት፡፡ የተለያየ ቋንቋ ኃይማኖት፣ ወግና ልማድ ያለው ህዝቧ ተቻችሎና አንድነቱን ጠብቆ የሚኖርባት ጥበብ ምስጢርም በዓለም ህዝብ ዘንድ የሚያስወድሳት ነው፡፡ የአየር ንብረቷ ለሰዎች ኑሮና ለእፅዋት እድገት እጅግ ተስማሚ፤ መሬቷ ለምና ሰፊ፤ ጅረቶቿ ዕልፍና ረጃጅም፤ ሀይቆቿ ታላላቆች ናቸው፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ ከኒጀር ቀጥላ ሁለተኛዋ የዓለማችን መናጢ ድሃ አገር በመሆን ስሟ በጥቁሩ የጉስቁልና እና የውርደት መዝገብ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ህዝቧ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ዳር ድንበሯን ጠብቆና ሉአላዊነቷን አስከብሮ የአፍሪካ የነፃነት ፋና ወጊ፣ የጥቁር ህዝቦች አርነት ተምሳሌት ቢያደርጋትም እስካሁን ድረስ ውስጣዊ ነፃነቱን ሊጎናፀፍ ሳይችል ቀርቶ በገዛ ወገኞቹ እንደባሪያ ተቀጥቅጦ እየተገዛ ይገኛል፡፡
በተለይም ደግሞ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የህዝቧን ተቻችሎ የመኖር ጥበብ የሚሰልብ የአንድነት ቀበኛ የሆነ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በእጭር ታጥቆ ቀን ከሌሊት የሚተጋ አገዛዝ ጥሎባታል፡፡
ይህ ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዚያት የተጣባት የፖለቲካ አደገኛ ደዌ ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ መጥቶ ዛሬ ላይ ህመሙ ጠንቶባት የአልጋ ቁራኛ አድርጓታል፡፡ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ የገቡበት የፖለቲካ አዙሪት የእድቷ ዋነኛ ማነቆ ሆኖ አገሪቱ ከኮንጎ ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ እየተገኘችና "የአፍሪካ የውሃ ማማ" ተብላ እየተጠራች በተደጋጋሚ ድርቅ ተመትታ ህዝቧ እንደ ቅጠል እንዲረግፍና የዓለማችን የችጋር ምሳሌና የለየላት ለማኝ እንድትሆን ጋብዟታል፡፡
ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የተጀመረው በሰውና እንስሳት ጉልበት የሚካሄደው ኋላ ቀር የአስተራረስ ብሎም የማዝመርና የማምረት ባህል እስካሁን ድረስ ምንም ሳይቀየር ወይንም ሳይሻሻል ሙሉ በሙሉ እንዳለ በመቀጠል ዛሬ ላይ የደረሰው በአገሪቱ ብልሹ ፖለቲካ ደንዳና ጀርባ ታዝሎ ነው፡፡ አገሩ የአፍሪካ የውሃ ማማ እየተባለች የምትጠራው የኢትዮጵያ ገበሬ ለዘመናት ሰማይ ሰማዩን እያንጋጠጠ ሲያይ መኖሩ ህልውናው በደመና ላይ መመስረቱና ጠብታ ዝናብ እስትንፋሱ መሆኑ ደግሞ በዓለም አደባባይ ቅስማችንን እየሰበረ የሚገኝ ሌላኛው የብልሹው ፖለቲካ መጥፎ ገፅታ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዝናብ እጥረት በተደጋጋሚ ድርቅ ተደቁሳ ህዝቧ በረሃብ ሲረግፍ ግብፅ ከኢትዮጵያ እምብርት ፈልቆ የሚሄደውን የአባይ ውሃ ከኢትዮጵያ ድንግል መሬት እየተጠረገ የሚጓዘውን የለም አፈር ደለል እየተጠቀመች በምግብ ራሷን ከመቻል አልፋ መበልፀግ መቻሏ የብልሹ ፖለቲካው እንጂ የአገራችን ገበሬ ድክመት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬማ ከቁራሽ መሬቱ ላይ የዕለት ጉርሱን ለማምረት ለዓንድ ዓመት ብቻ የሚያፈሰው የትየለሌ ጉልበት በዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂና ዕውቀት ቢደገፍ የትና የት በደረስን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ የውሃ ችግር የለበትም፤ የኢትዮጵያ ገበሬ የእርሻ መሬት ጥበት የለበትም፤ የኢትዮጵያ ገበሬ ዕውቀት ያለመቀበል የአቅም ችግር የለበትም፤ የኢትዮጵያ ገበሬ ኋላ ቀር ሆኖ አልተፈጠረም፣ የኢትዮጵያ ገበሬ ዘመናዊነትን አልሻም አላለም፤ የኢትዮጵያ ገበሬ ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂን አልጠቀምም አላለም ወይንም ለመጠቀም የሚያስችል አቅም አያንሰውም፤ እሱማ ተፈጥሮ የሚባል የማይጋፋው ክፉ ባላጋራ ጥሎበት በረሃብ ይሞታል፣ እትብቱ ከተቀበረበት ቀዬው ተፈናቅሎ ይሰደዳል እንጂ ከአባቶቹ በወረሳት ባለችው ባህላዊ ዕውቀት አርሶ አንደፋርሶ ነጭና ቀይ አምርቶ እየጫነ ብቻውን ኢትዮጵያን እስከ ዛሬ ድረስ አቆይቷታል፡፡ የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንዲሉ ችግሩ ያለው ከላይ ከመሪዎቹ ከብልሹው ፖለቲካ ዘዋሪዎቹ ከአንጋቾቹ ነው፡፡
ዘዋሪዎች ወይንም አንጋቾች ብልሹውን ፖለቲካ ችግር አስወልደው ችግሩ የፈጠረውንና የብልሹው ፖለቲካ የልጅ ልጅ የሆነውን ድርቅና ረሃብ መልሰው ለፖለቲካ ማምረቻ ፋብሪካቸው በግብአትነት ይጠቀሙበታል፡፡ በረሃቡ የረገፈውን ህዝብ ሬሳ በመቀጣጠል እንደመሰላል ተጠቅመው የስልጣን ማማ ላይ ቁብ ይላሉ፡፡ ለዚህ ሁለቱ አንጋቾች ደርግና ህወሓት ጥሩ አብነቶች ናቸው፡፡
1965 እና 66 ዓ.ም የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በድርቅ ወጀብ ክፉኛ ተመትቶ ልክ እንደ ዛሬው ህዝብ በረሃብ የተሸመደመደበት ክፉ ዘመን ነበር፡፡ በእርግጥ በተራበው ህዝብ ቁጥር ደረጃ ከተመለከትነው የዛሬው ይልቃል፡፡ በመሆኑም 4ኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተወልዶ በእነ ሻለቃ አጥናፉ አባተና ሻለቃ መንግስቱ ኃይለ ማርያም የሚመራውና ራሱን ደርግ ብሎ የጠራው ሻለቃና ከሻለቃ በታች የሆኑ ዝቅተኛ መኮንኖች የተሰባሰቡበት የወታደሮች ቡድን ወይንም ኮሚቴ ስልጣን ላይ ለመውጣት አድፍጦ እያደባ የሚገኝበት ወቅት ስለነበር አጋጣሚውን ተጠቀመበት፡፡ በወቅቱ 225ኛው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩትን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴን በቁጥጥሩ ስር አውሎ በጆናታን ድምቢልቢ ተቀርፆ የተቀነባበረውን በረሃብ እያለቀ የሚገኘውን ህዝብ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል የዘመን መለወጫ ዋዜማ ዕለት ምሽት በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለህዝብ አሰራጨው፡፡ የ1967 ዓመተ ምህረትን አዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ ለመቀበል ሽርጉድ ይል የነበረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድንገት በቴሌቪዥን መስኮት በተመለከተው የወገኖቹ አሳዛኝ ዕልቂትና መከራ ልቡ ተሰብሮ ለአፍታ ተስፋው ካጠገቡ ሸሸው፡፡ ንጉሰ ነገስቱንም አምርሮ ጠልቷቸው ዓይናቸውን ለአፈር አላቸው፡፡ ለሺህዎች ዓመታት የዘለቀው የዘውድ ስርዓት በ225ኛው ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ተደምድሞ ዳግመኛ ላናየው ግብአተ መሬቱ ተፈፀመ፡፡
1977 ዓ.ም አንጋቾች ዙፋን ላይ ከወጡ ከ10 እና ከ11 ዓመታት በኋላ ድርቁና ረሃቡ አድማሱን አስፍቶ በአደገኛ ሁኔታ ተመልሶ መጣ፡፡ ይህ ዘመን ኢትዮጵያ ከአራቱም ማዕዘን በተቀሰቀሰ የእርስበርስ ጦርነት እየታመሰችና ምጣኔ ሀብቷ ክፉኛ እየተሽመደመደ የሚገኝበት ስለነበር ድርቁንና ረሃቡን ፈፅሞ ትከሻዋ መሸከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር፡፡
በመሆኑም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ስጋቸውን በቁማቸው ጨርሰው በአፅማቸው ብቻ እየቀሩ አሸለቡ፡፡ ሁኔታው የዓለምን ህዝብ በጠቅላላ አስደነገጠ፤ አሳዘነም፡፡ ነገር ግን ጫካ ለነበረው ህወሓት ሰርግና ምላሽ ሆነለት፡፡ ደርግ ዘውዳዊ ስርዓቱን በሰፈረበት ቁና ተሰፈረ፡፡ 
በትግራይ ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚኖርባቸው አካባቢዎች በድርቁ በመጠቃታቸው በተፈጠረው አደገኛ ጠኔ ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ነገሰ፡፡ አንጋቹና ጠባብ ብሄርተኛው የህወሓት ቡድን ባንድ ወገን የጀመረውን ማባሪያ የሌለውና ለረጅም ጊዜ የቆየ ጦርነት በመቀጠል በሌላ ወገን ደግሞ ለተጎጂዎች የተለገሰውን ገንዘብ ባቋራጭ እየነጠቀ የጦር መሳሪያ በመግዛትና ለሰራዊቱ ቀለብ መግዣ በማዋል የህዝቡን መከራ በእጅጉ አበርትቶ ከሞት ላይ ሞት ደራርቦ እንዲሞት አደረገው፡፡ ቀያቸውን እየለቀቁ ነብሳቸውን ለማሰንበት ከረሃቡ የሚሸሹትን ተፈናቃዮች ጠብመንጃ በማስታጠቅ ለጦርነት አሰለፋቸው፡፡ በረሃቡ ምክንያት ከአቅሙ በላይ የሆነ የሰው ኃይል መመልመልና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ መታጠቅ ቻለ፡፡ ህወሓት በለስ ቀናው፤ በኢትዮጵያዊያን መከራ ወታደራዊ ጡንቻውን አፈረጠመ፡፡

ደርግ ሶሻሊስት በመሆኑ ምክንያት ምዕራባዊያን መንግስታት ለረሃብ አደጋው ፈጥነው እጃቸውን ሊዘረጉ ባለመቻላቸው ረሃቡ የበለጠ ተስፋፋ፤ አስደንጋጭ ዕልቂትንም አስከተለ፡፡ 
አየርላንዳዊዩ ድምፃዊ ቦብ ጊልዶፍ ለነብስ አድን እርዳታ የሚውል ገንዘብ በአፋጣኝ የሚሰበስብ "ባንድ ኤይድ" የሚል መጠሪያ ያለው የሙዚቃ ቡድን አቋቋመ፡፡ ከዚያም የሙዚቃ ቡድኑ የለቀቀው "Do they know it's chiristmas?" ነጠላ ዜማ በምድረ እንግሊዝ ብቻ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከ3 ሚሊዮን ቅጂ በላይ ለመሸጥ በቃ፡፡ እሱን ተከትሎ የወጣው "We are the world" ነብስ አድን ነጠላ ዜማ ደግሞ ከ20 ሚሊዮን ቅጂ በላይ በመላው ዓለም ተቸበቸበ፡፡

ማርቲን ፕሎውት የተባለ የቢ.ቢ.ሲ ጋዜጠኛ በረሃብ ለተጎዳው የትግራይ ህዝብ የተለገሰውን ከፍተኛ ገንዘብ ህወሓት ዘርፎ ለጦር መሳሪያ መግዣ እንዳዋለው ሲ.አይ.ኤን በመረጃ ምንጭነት በመጥቀስ እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ባደረገው ዘገባው አጋልጧል፡፡ ጋዜጠኛው ፕሎውት ህወሓት 95 ሚሊዮን ዶላር የተራበ ህዝብ ምፅዋት ዘርፎ ለጦርነት እንዳዋለው በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል፡፡
ህወሓት ከሁለት እስከ ተሰነጠቀበት 1993 ዓ.ም ድረስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረውና የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ሆኖ የሰራው ገብሩ አስራት በ2006 ዓ.ም ባሳተመው "ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ" የሚል ርዕስ ባለው መፅሐፉ ህወሓት የምፅዋቱን ገንዘብ ዘርፎ ለጦርነት ማዋሉን በተመለከተ እንዲህ አድበስብሶት ለማለፍ ሞክሯል፡፡
"...በአሁኑ ጊዜ አከራካሪ ሆኖ የሚገኘው ህወሓት ሰብዓዊ እርዳታን ለወታደራዊ ጥቅም አውሏል የሚለው ጉዳይ በወቅቱ ከነበረው ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ አኳያ ሲታይ ምንም ትርጉም አልነበረውም፡፡ ህወሓትና ማሌሊት በተለይም ደግሞ ህወሓት በትግራይ ነፃ መሬት የመንግስት ሚና የሚጫወት ድርጅት እንደነበር መታወስ አለበት፡፡ በተለይም ከ1977 ዓ.ም ድርቅና ረሃብ መከሰት በኋላ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶችና መንግስታት ቁጥራቸው እየጨመረ ሄዶ ነበር፡፡ እርዳታ የሚሰጡንም በሰብዓዊ እርዳታ ሽፋን ስለነበር የሚሰጠው የሰብዓዊና ሌላው እርዳታ ባንድ ቋት የተካተተ ነበር፡፡ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውለውንና ለሰራዊቱ የሚውለውን በጀትም የሚወስነው የድርጅቱ /የህወሓት/ አመራር ነበር..."

‘ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር’ የሚባለው መላ አገሪቱን በነፍጥ ተቆጣጥሮ በጉልበቱ ስልጣን ላይ ወጥቶ በሚገኘው ህወሓት ደርሶበት ዛሬም የኢትዮጵያን ህዝብ በድህነት እንዲማቅቅ፣ በችጋር አበሳውን እንዲያይና በረሃብ እንዲያልቅ እያደረገው ይገኛል፡፡ በአንጋቾች የሚዘወረው ብልሹ ፖለቲካም እጅግ በጣም ብሶበት አገራችንን ስሟን በዓለም የድህነት መዝገብ ላይ እንዲሰፍር እና ህዝቧን ለከፋ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ውድቀት ዳርጎት ይገኛል፡፡
በህወሓት ቡድን የአገዛዝ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅና ረሃብ ሲነግስ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም፤ ከ1992-95 ዓ.ም ድረስ ከስምንት ሚሊዮን ህዝብ በላይ በረሃብ የተጎዳበት ወቅት ነበር፡፡ አሁን ተከስቶ መላ አገሪቱን በረሃብ ያዳረሰው ድርቅ በ60 ዓመታት ውስጥ እጅግ በጣም አደገኛውና አስከፊው እንደሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት ደጋግመው በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡ በአፋር፣ ሱማሌ፣ ሐረርጌ፣ ኦሮምያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ትግራይ... የቀረ የለም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች አደገኛ ረሃብ ገብቷል፡፡ ገበሬው ቀዬውን እየለቀቀ ወደ ከተሞችና ይሻላሉ ብሎ ወደገመታቸው ገጠራማ አካባቢዎች በመሰደድ ላይ ነው፡፡ የወሎ ገበሬ ዛሬም መከራ መጥቶበታል፣ ወንዶች ለቀን ስራ ወደ መተማ ሁመራና ሱዳን ሴቶች ህፃናት ልጆቻቸውን በጀርባቸው አዝለውና በደረታቸው ታቅፈው ለልመና ወደ ከተሞች አየጎረፉ ነው፡፡ የገበሬው የህልውና መሰረት የሆኑት ዕልፍ አዕላፍ ከብቶች በውሃና በመኖ እጦት እየረገፉ በድናቸው በየማሳው እየተዘራ ነው፡፡ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ረሃባቸውን ለማስታገስ ጫት ብቻ ሲያመነዥኩ ውለው ያድራሉ፡፡ እሱም ሲገኝ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ አንድ አርብቶ አደር ብቻ ከ30 ከብቶች በላይ ሞተውበታል፡፡ የአፋርና የሱማሌ በረሃማ መሬቶች በፍየሎች ጥንብ ተሞልተዋል፡፡ ድርቁ በጎዳቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ የከብቶች ዋጋ በእጅጉ በመውረዱ ገበሬው ከሞት የተረፉትን የመነቆዱ ከብቶቹን ሸጦ በእፍኝ ጥሬ እንኳን ህይወቱን ማሰንበት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ወደ 300,000 የሚጠጉ ህፃናት በምግብ እጥረት በአደገኛ ሁኔታ ስለተጎዱ አስቸኳይ እርዳታ ካልተደረገላቸው ለህልፈት ሊዳረጉ እንደሚችሉ "UNCEF" በጥብቅ አሳስቧል፡፡ በፈረንጆቹ 2016 ዓ.ም ማለትም ከሁለት ወራት በኋላ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው 15 ሚሊዮን የተራበ ህዝብ እንደሚኖር የተባበሩት መንግስታት በጥናቱ አረጋግጧል፡፡ በተለይም ደግሞ 2.3 ሚሊዮን ህዝብ ጊዜ በማይሰጥ አጣዳፊ ረሃብ ውስጥ ስለሚገኝ አፋጣኝ እርዳታ ካልተደረገለት የከፋ ዕልቂት ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ጨምሮ አሳስቧል፡፡
መንግስት ነኝ የሚለው አንጋቹ የህወሓት ቡድን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የደረሰውን የድርቅና ረሃብ አደጋ መጀመሪያ ዓይኖቹን በጨው አጥቦ ሙልጭ አድርጎ ክዶ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ አብዛኞቹ ባለስልጣናትና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ተብየዎች በአንድነት "ኢትዮጵያ በልፅጋለች፤ ጥጋብ እንጂ ድርቅና ረሃብ የሚባል ፈፅሞ የለም፤ የጠላት ወሬ ነው፡፡" ሲሉ ያፈጠጠውን ዕውነት ለማስተባበል ሞከሩ፡፡ ይህ የህወሓት ቡድን የሚሊዮኖችን ረሃብ ለመሸሸግ የሰጠው ማስተባበያ የችግሩ መንስኤ ያለው ከእነሱ ከዘዋሪዎቹ ከብልሹ ፖለቲካቸው መሆኑን ለመገንዘብ በጣም ትንሹ ማስረጃ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያንዣበበው የረሃብ አደጋ በዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን መዘገብና መጋለጥ በእጅጉ ያንገበገበው አንጋቹ የህወሓት ቡድን ትንሽ ቆይቶ ደግሞ "አዎ ድርቅ አለ፤ ጠኔም ገብቷል፤ ቢሆንም ግን የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሁለት ድጅት አሃዝ ስለተመነደገ እርዳታ አያስፈልገንም በምግብ ራሳችንን ችለናል፡፡" ሲል የማስተባበል አዝማሚያ ባደላበት አነጋገር መንተፍረቱን አመነ፡፡
ነገር ግን በዚህ መካከል በርካታ ኢትዮጵያዊያን እስካሁን ማንም ሳይደርስላቸው በረሃብ አለንጋ ሲገረፉ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ችግሩ ያለው የሁሉም ውድቀታችን ምንጭ ከሆነው ከብልሹው ፖለቲካ ዘዋሪዎች ከላይ ከአንጋቾቹ ነው፡፡
አንጋቾች ምንጊዜም ቢሆን ወንበራቸውን እንጂ የህዝብን ሰቆቃ የሚመለከቱበት ዓይን የላቸውም፤ አንጋቾች ምንጊዜም ቢሆን የግል ጥቅምና ክብራቸውን እንጂ ስለብዙኃን ደህንነት የሚጨነቁበት ህሊና የላቸውም፤ አንጋቾች ድክመታቸውን ለመሸፋፈን አዘውትረው ይዋሻሉ፤ ድክመታቸው አገርን ይጎዳል፤ ቅጥፈታቸው ደግሞ አገርን ጨርሶ ያጠፋል፡፡
አንጋቾች በነሀሴ ወር 4.55 ሚሊዮን ህዝብ በረሃብ እንደተጠቃ አምነው ነበር፤ በቅርቡ ደግሞ በጥቅምት ወር የረሃብተኛው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ከ4.55 ሚሊዮን ወደ 8.2 ሚሊዮን በፍጥነት አንዳሻቀበ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እነሱ ያመኑት ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ማደጉ ብቻ የአደጋውን ቅፅበታዊ ተስፋፊነትና ተለዋዋጭነት ያመለክታል፡፡ ስለዚህ የረሀብተኞች ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ ወደ 15 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል የተባበሩት መንግስታት ይፋ ያደረገው ጥናት በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን እዚህ ላይ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በእርግጥ ህወሓቶች ካመኑት 8.2 ሚሊዮን ቁጥሩ በእጅጉ የሚልቅ ኢትዮጵያዊ በረሃብ እየተሰቃየ እንደሚገኝና ውሎ አድሮም መጠኑ ከያቅጣጫው አየተጠቀሱ ገሚገኙት አኃዞች ሊጨምር እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለም፡፡
ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወቱን የሚገፋው እጅግ ኋላቀር በሆነው ግብርና ነው፡፡ ይህ ገበሬ ህዝብ ደግሞ ኢትዮጵያን ከዚህ ያደረሳት ከጥንት ከጠዋት ከአባቶቹ በወረሳት ባህላዊ የእርሻ ዕውቀትና ጉልበቱን ከተገቢው በላይ አንጠፍጥፎ እያፈሰሰ ነው፡፡ ሰማይ ሰማዩን አንጋጦ ከማየትና በበሬ ከማረስ ሊያላቀው የሚችለው የኔ የሚለው መንግስት እስካሁን ድረስ አላገኘም፡፡ እንዴውም ይባስ ብሎ እንደ ህወሓት አይነቱ ዘረኛ አገዛዝ መሬቱን እየተነጠቀ ከቀዬው እንዲፈናቀል፣ ዓመት ሙሉ የለፋበትን ምርቱን ጎተራውን አሟጦ ሸጦ ለማዳበሪያና ለዘር ዕዳ በመክፈል ምንም ጥሪት ሳይቋጥር ውልቁን እንዲቀር እያደረገው፤ በፖለቲካዊ አመለካከቱ ምክንያት አድሎና ጭቆና እያደረሰበት ይገኛል፡፡
አንጋቹ የህወሓት ቡድን በየመንደሩ ያሰራጫቸውን የግብርና እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ገበሬው በሙሉ ልቡ ሊቀበላቸው አልቻለም:: በጎም ይሁን መልካም ምክራቸውን ሊሰማቸው ሰምቶም ተግባራዊ ለማድረግ ሙሉ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአገዛዙን ብልሹ ፖለቲካዊ ተልዕኮ በዋነኝነት አንግበው ወደ ቀየው ብቅ እንዳሉ ብልሁ ገበሬ ልባቸውን መርምሮ ደርሶባቸዋልና፡፡ ስለሆነም ከተራ ካድሬነት በዘለለ ሞያቸው ለእሱ አይታየውም፡፡ አብዛኞቹ የግብርና ባለሙያዎች በበጋው ወራት ብልሹውን የአንጋቾች ፖለቲካ በየዋሁና በምስኪኑ የኢትዮጵያ ገበሬ ላይ ሲያስፈፅሙ ይባጁና ገበሬው የእነሱን ሙያዊ ድጋፍ በሚሻበትና ዘር በሚወድቅበት የክረምት ወቅት ወደ ከተሞች ለኮሌጅ ትምህርት ርቀው ይጓዛሉ፡፡ ለካድሬነታቸው ከአገዛዙ የሚቸራቸው ገፀ-በረከት መሆኑ ነው፡፡ ምንም እንኳን በትምህርት ስርዓቱ መውደቅ ምክንያት ውጤታማ የሆነ ተግባራዊ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ተመጣጣኝ የሆነ ዕውቀት ባይኖራቸውም ከድሃው ገበሬ ጎን ቆመው የእሱ ህይወት እንዲለወጥ የሚፍጨረጨሩና ለመብቱ የሚከራከሩ የግብርና ባለሙያዎች ቢኖሩ በገበሬው መንደር ላንድም ቀን ውለው እንዲያድሩ አንጋቹ የህወሓት ቡድን ፈፅሞ አይሻም፡፡

ህወሓት ከፍተኛ እርዳታ እያጋበሰበት በሚገኘው የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ገበሬውን ጠርንፎ የእሱ ተገዥ እያደረገው ነው፡፡ ብልሹውን ፖለቲካ ከልቡ ያልተቀበለ እንድም የኢትዮጵያ ገበሬ በፕሮግራሙ እንዲታቀፍ ህወሓት ፈፅሞ እይፈቅድም፡፡ ህወሓት ገበሬውን በአንድ ለአምስት ጥርነፋ ተቀፍድዶ ተይዞ የእሱ ተገዥ ብቻ እንዲሆን እያመቻቸው ነው፡፡ ኑሮውም እያደር ቁልቁል ሆነ እንጂ ህወሓት እንደሚያወራው ገበሬ ከሚለው መጠሪያው በስተቀር ፈፅሞ የተለወጠለት ነገር የለም፡፡ እስካሁንም ድረስ ጥቂትም ቢሆን በከተሞች የተስፋፋው ዘመናዊነት በገበሬው መንደር ፈፅሞ አይታወቅም፡፡ የኤሌክትሪክ መብራት፣ ህክምና፣ ንፅህናው የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ፣ አንድ ገበሬ ተወልዶ አድጎ አርጅቶ እስኪሞት ድረስ ፈፅሞ በዓይኖቹ ከማማያያቸው በርካታ ስልጣኔዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ እንደ አስተራረሱ ሁሉ ከአመጋገቡ እስከ አለባበሱና የቤት አኗኗሩ ድረስ ዛሬም የጥንቱ እንዳለ ነው፡፡ ህወሓት በቴሌቪዥን የሚያሳየንን ሚሊየነር ገበሬዎችን በጋህዱ የገበሬው ዓለም ውስጥ ፈፅሞ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ ህይወቱ ከእጅ ወዳፍ ከመሆን ስላልተላቀቀ ምንም ጥሪት መያዝ አልችል ብሎ ነው በድርቁ ምክንያት ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ገበሬ ወደ 20 በመቶ የሚጠጋው የሚልሰው የሚቀምሰው አጥቶ ከሞት አፋፍ ላይ የተገኘው፡፡
አንጋቹ የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ የገባውን ድርቅና ረሃብ "በአሜሪካ ካሊፎርኒያም ገብቷል" እያለ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ውስጥ የደረሰውን አደጋ ለማለዘብ ሲሞክር በተደጋጋሚ ተደምጧል፡፡ ከዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ትችቱ እየተነሳ ያለው በኢትዮጵያ ድርቅ ለምን ተከሰተ በሚል አኳኋን አይደለም፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዴት ይራባል ነው፡፡ ህወሓት እንዳለው አሜሪካ ካሊፎርኒያ ውስጥ ድርቅ ገብቶ ሊሆን ይችላል፡፡ የተራበ ግን አንድም ሰው የለም፡፡ ኢትዮጵያ አድጋለች ተመንድጋለች ከተባለ እነሱ ባመኑት እንኳን ብቻ ብንሄድ 8.2 ሚሊዮን ህዝብ ለምን ሚልሰው ሚቀምሰው ያጣል?
አዎ እውነት ነው የጥቂት ህወሓታዊያን አንጋቾችና ተከታዮቻቸው ኑሮ ከመሻሻልም አልፎ የቅንጦት ሆኗል፡፡ ነገር ግን አሁንም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በከፋ የድህነት ህይወት ውስጥ ነው ያለው፡፡
የዓለም ባንክና የተባበሩት መንግስታት ያወጡትን ሪፖርት እንኳን ብቻ ብንመለከት ከ1.25 ዶላር ያነሰ ገቢ ስላላቸው 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖሩና ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 44 በመቶ የአገሪቱ ህጻናት የከፋ የምግብ እጥረት ሰለባ እንደሆኑ በተለይም ደግሞ 28 በመቶዎቹ ክብደታቸው ከሚፈለገው መጠን በታች በእጅጉ የወረደ መሆኑን ያስረዳል፡፡
አንጋቹ የህወሓት ቡድን 25 ዓመታት ሙሉ ስልጣኑን ለማደላደል ተግቶ ሲሰራ የህዝብ ሀብት እየመዘበረ ራሱንና ተከታዮቹን ብቻ ለይቶ ሲያበለፅግ ኖረ እንጂ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት፣ ካለፉት ዘመናት በጣም በተሻለ ሁኔታ ያገኘችውን አንፃራዊ ሰላም፣ መጠነ ሰፊ የሰው ጉልበትና እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የውጭ እርዳታና ብድር ተጠቅሞ ለውጥ ለማምጣት ፈፅሞ የሞከረበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይነሳብኛል ብሎ የሚሰጋውን ህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ለማርገብና የእርዳታ ሰጭዎችንና የአበዳሪዎችን ዓይን ለመመለስ ያለዕቅድ ከዚህም ከዚያም እየጀማመረ ከሚያሳያቸው ወይንም በጥድፊያ ተሰርተው በጥድፊያ ከሚፈራርሱት አንዳንድ መሰረተ ልማት ተብየዎች በስተቀር የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት እንድ ስንዝር እንኳን ወደ ፊት ፈቀቅ ሊያደርግ የሚችል ጠብ የሚል የልማት ስራ አላከናወነም፡፡ በአገሪቱ ላይ ለዘመናት የነገሰውን ብልሹ ፖለቲካም የበለጠ አጨመላልቆ በዘረኝነት መርዝ ለውሶ አውሰበሰበው እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠውን ሰፊ እድል ተጠቅሞ ፈፅሞ ለማሻሻል አልሞከረም፡፡ ህወሓት በተለይም ደግሞ በተሳሳተ የትምህርት ፖሊሲውና ሆነ ብሎ በሚሰራቸው ሸፍጦቹ የትውልዱን የመንፈስ ዕድገት በማቀጨጩ ይቅር ልንለው የማንችለው የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በማህበራዊና ስነ-ልቦና እንዲወድቅ ዕቅድ ነድፎ ሲሰራ ለሩብ ምዕተ ዓመት ኖሯል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ በመንፈስ ጨርሳ ጠፍታለች፡፡ መንፈሱ የሞተ ህዝብ ደግሞ ህይወት እንደሌለው ግዑዝ አካል ይቆጠራል፡፡
ባጠቃላይ ከበቂ በላይ የሆነ የተፈጥሮ ውሃ አለን፤ ከበቂ በላይ የሆነ የሰው ኃይል አለን፤ ሰፊ አገር ሰፊና ለም መሬት አለን፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ያጣነው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ የእኔ የምንለው የእኔ የሚለን መንግስት፡፡ ችግሩ ያለው ከብልሹው ፖለቲካ ላይ ነው፤ ለፖለቲካው ብልሹነት መንስኤዎቹ ደግሞ አንጋቾች ናቸው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ኢትዮጵያችን ለእድገት እና ለለውጥ ፀር የሆነ ብልሹ ፖለቲካ በሚዘውሩ አንጋቾች በጠብመንጃ መገዛቷ ማብቃት አለበት፡፡ ነፃ አገር፣ ነፃ ህዝብ፣ ነፃ መንግስት ባፋጣኝ መመስረት ያሻናል፡፡ አሳውን ለማጥፋት ተባብረን ባህሩን እናድርቅ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
(አ.ታ ኦሮማይ)

No comments:

Post a Comment